ልዩ ዘገባ ከሞሮኮ | የዋልያዎቹ ጉዞ ዝርዝር

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአዲስ አበባ ተነስቶ ካዛብላንካ የደረሰበትን ጉዞ በተመለከተ ተከታዩን ዘገባ አዘጋጅተናል።

\"\"

በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የ2023 አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የአህጉራችን ብሔራዊ ቡድኖች በአስራ ሁለት ምድቦች ተከፋፍለው የማጣሪያ ፍልሚያቸውን እያከናወኑ የሚገኝ ሲሆን ከቀናት በኋላም የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታቸውን ሊከወኑ ቀጠሮ ይዘዋል። በምድብ አራት ከጊኒ፣ ግብፅ እና ማላዊ ጋር ተደልድሎ ምድቡን በአንደንነት እየመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም መጋቢት 15 እና 18 ሞሮኮ በሚገኙ ገለልተኛ ስታዲየሞች ከጊኒ አቻው ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ያደርጋል።

ለእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ከመጋቢት 6 ጀምሮ ዝግጅቱን ሲያደርግ የነበረው ቡድኑ አራት የልምምድ መርሐ-ግብሮችን እና አንድ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሀገሩ ላይ ካከናወነ በኋላ ትናንት ምሽት ወደ ሞሮኮ ጉዞ ጀምሯል። በዚህ ጉዞ ላይ ከ22 ተጫዋቾች እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላት በተጨማሪ የልዑኩ መሪ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳኛቸው ንግሩ እና ዋና ሥራ-አስፈፃሚው አቶ ባህሩ ጥላሁን ይገኛሉ።

ከኢትዮጵያ ሞሮኮ ቀጥታ የዐየር በረራ አለመኖሩን ተከትሎ በቅድሚያ ቡድኑ በኢትዮጵያ ዐየር መንገድ ከምሽቱ 4:15 ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ግብፅ ካይሮ የተጓዘ ሲሆን ከ4 ሰዓታት በራራ በኋላ ስፍራው ደርሶ ለ5 ሰዓታት ገደማ የትራንዚት ቆይታ አድርጎ ረፋድ 3:15 ሲል በግብፅ ዐየር መንገድ ከካይሮ ወደ ሞሮኮ ካዛብላንካ ይጓዛል ቢባልም ነገሮች በታሰበው መልኩ አልሄዱም። በዚህም ቀድሞ በታቀደው መሰረት ረፋድ 3:15 ቡድኑ ከካይሮ እንዳይነሳ ተሳፋሪዎችን ይዞ የሚበረው የግብፅ አውሮፕላን በመዘግየቱ ሁለት ጊዜ የሰዓት ሽግሽጎች (በቅድሚያ ወደ 4:30 ከዛም ወደ 5:30) ተደርገው በካይሮ ኤርፖርት ለተጨማሪ ሰዓታት ቆይታ ለማድረግ ተገዷል።

ቀትር 6 ሰዓት ሲል ግን በረራው ተጀምሮ ለአምስት ሰዓታት ጉዞ ተደርጎ ከሰዓታት በፊት እንደገለፅነው በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 11:15 ላይ የልዑካን ቡድኑ ሞሮኮ ካዛብላንካ መሐመድ 5ኛ ዐየር ማረፊያ ደርሷል። ልዑኩም በኤዶ አንፋ ሆቴል ማረፊያውን ያደርጋል። የቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ምሽት 5 ሰዓት (በሞሮኮ ሰዓት አቆጣጠር 2 ሰዓት) ተጫዋቾችን ቀለል ያለ ልምምድ እንደሚያሰሩ ተጠቁሟል።

\"\"

ለዘገባ ሞሮኮ የምትገኘው ሶከር ኢትዮጵያ ቡድኑ በካዛብላንካ እና ራባት በሚያደርገው ቆይታ ላይ የሚኖሩ አዳዲስ ጉዳዮችን እየተከታተለች እንደምታቀርብ ከወዲሁ መግለፅ ትወዳለች።

* ምሽት 2 ሰዓት ላይ ልምምድ ይደረጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በጉዞ ምክንያት በመጣ ጫና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለተጫዋቾቻቸው እረፍት በመስጠታቸው የምሽቱ ልምምድ ተሰርዟል።