“…ይህን ማሳካት የሚያስችል ቁመና አለን” – አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

በካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሀ የተደለደለችው ኢትዮጵያ በመድረኩ በሚኖራት ቆይታ ዕቅዷ ምን እንደሆነ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተናግረዋል።

በኤሊሊ ሆቴል ብሔራዊ ቡድኑ ከቀናት በፊት ውድድሩ ወደሚዘጋጅበት ካሜሩን ከማቅናቱ በፊት በስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ጠቃሚ ሀሳቦችን በግብአትነት ለመውሰድ ከደቂቃዎች በፊት የፓናል ውይይቱ መጀመሩን ገልፀን ነበር። በመድረኩ ብሔራዊ ቡድኑ የዓለም ዋንጫ እና የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞን አስመልክተው ሰፊ ማንራሪያ የሰጡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በካሜሩን በሚኖራቸው ቆይታ ምን እንዳቀዱ እና ማሳካት ስለሚፈልጉት ግባቸው ተከታዩን ሀሳብ አጋርተዋል።

” ሁለት ዕቅዶችን ይዘን ተነስተን ነበር። አንደኛው በዓለም ዋንጫው ማጣርያው ከአፍሪካ አስር ሀገራት አንዱ መሆንን አስበን ነበር። ይህም ማሳካት አልቻልንም። ሁለተኛው ያአቀድ ነው የአፍሪካ ዋንጫ መግባት ነበር አሳክተናል። የአፍሪካ ዋንጫ ካለፍንስ በኃላ ምን ማድረግ አለብን ስንል እንደሚታወቀው የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ሀገር ነን፤ ሆኖም ግን ለውድድሩ ሩቅ ነን። ባለፈው በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ዘመን ከ31 ዓመት በኋላ ነው ያለፍነው። አሁን ደግሞ ከስምንት ዓመት በኋላ ነው ያለፍነው። ከዚህ በኋላ በየሁለት ዓመቱ የሚያልፍ ቡድን መገንባት ይቻላል። ግን የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን ብዙ የቤት ሥራ የሚጠይቅ ነው። አሁን ካለው አጭር ጊዜ አንፃር ምን ማቀድ አለብን ስንል አውርተናል ቢያንስ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ በቀጣይ ዓመት መሳተፍ የሚችል ስነ ልቦና ሊገነባ የሚችል ቡድን ይዘን ለመቅረብ ነው አቅደን እየሰራን ያለነው። ይህን ለማሳካት ደግሞ ቢያንስ በዚህኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏችን ከምድባችን ማለፍ አለብን የሚል ግብ አስቀምጠናል። ይህን ማሳካት የሚችል ቁመና አለን ብለን እናስባለን።”