ዜና እረፍት | ዶ/ር ሲራክ ሀብተማርያም አረፉ

ኢትዮጵያ አለኝ ከምትላቸው የካፍ ኢንስትራክተሮች መካከል አንዱ የነበሩት ዶ/ር ሲራክ ሀብተማርያም በድንገተኛ ህመም ህይወታቸው አልፏል፡፡

እግር ኳስን በተጫዋችነት የጀመሩት እና ኃላ ላይም ወደ ስልጠናው አለም በመግባት የጅማ ከተማ አሰልጣኝ በመሆን በ90ዎቹ መጀመሪያ ላይ መስራት የቻሉ ሲሆን ያለፉትን አመታት በአንፃሩ በካፍ ኢንስተራክተርነት ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ነበሩ። ከእግር ኳሱ በዘለለ በጅማ ዩኒቨርሲቲ በመምህርት እና በስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሀላፊነት በተጨማሪም የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ለአራት ዓመታት ዳይሬክተር በመሆን ተቋሙ ዛሬ ለደረሰበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ሆነው የሰሩ ሲሆን ፌድሬሽኑ እና ስፖርት ኮሚሽን በሚያዘጋጃቸው ጥናቶች ቡድን መሪ ሆነውም ሰርተዋል፡፡ካሜሮን ያውንዴ በ2009 በተሰጠው የኢንስትራክተሮች ስልጠና ላይ ተካፍለው በማለፍ ያለፉትን አምስት ዓመታት የካፍ ኢንስትራክተር በመሆን እየሰሩ ነበር፡፡ የካፍ ላይሰንስ ማንዋልንም በማዘጋጀት ላይ ነበሩ።

ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በስፖርት ሳይንስ በሩሲያ ሞስኮ ዩኒቨርሲቲ የሰሩት ዶ/ር ሲራክ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ዲን ሆነው በመስራት ላይ የነበሩ ሲሆን በድንገተኛ ህመም ዛሬ ህይወታቸው አልፏል። ነገ 9፡00 በቀራኒዮ መድሃኔዓለም ቤተ-ክርስቲያን የቀብር ስነ-ስርዓታቸው እንደሚፈፀምም ታውቋል።

ሶከር ኢትዮጵያ በዶ/ር ሲራክ ህልፈት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቦቻቸው ለሙያ አጋሮቻቸው እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ትመኛለች፡፡