ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በ9ኛ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች የሦስተኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 የአደጋ ጊዜ አሰልጣኙ…

አዲስ አበባ ከተማ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ሲገጥም በግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ እየተመራ መቅረቡ ሲያነጋግር የነበረ ጉዳይ እንደሆነ ተመልክተናል።

የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱን በኮቪድ-19 መጠቃታቸውን ተከትሎ ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን ለገጠመበት ጨዋታ በሜዳው መገኘት ባለመቻላቸው በአሰልጣኝነት ቡድኑን የመራው ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ነበር።

በጨዋታው ወቅት ከአሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ ጋር ተደጋጋሚ የሥልክ ልውውጦችን (ከሰባት ጊዜ በላይ) በማድረግ ቡድኑን በሜዳው ጠርዝ ሆኖ የመራው ዳንኤል በመጀመሪያው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ ቀዝቀዝ ብሎ ብንመለከተውም በሁለተኛው አጋማሽ ግን ይበልጥ በተነቃቃ ስሜት ውስጥ ሆኖ ቡድኑን ሲመራ ተመልክተነዋል።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ስለተሰጠው ኃላፊነት በሰጠው አስተያያት “ከባድ ኃላፊነት ነው። ኃላፊነቱን የምትሸሸው አይደለም።…..”ቢልም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ግን በተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት መካከል ስላለው ልዩነት ሲጠየቅ “ከመቶ መቶ አንድ ተጫዋችነት ይሻላል። አሰልጣኝነት በጣም ከባድ ነው። ኳስ ሳቆም አሰልጣኝነትን እንዳላስብ ነው ያደረገኝ። ከዳኛ ጋር ያለውንም ነገር ስታይ አሰልጣኝነት ከባድ ነው። ብዙ ጊዜ 25 ተጫዋች ይዘህ ሜዳ ውስጥ የሚገባው ደግሞ 11 ነው። ተቃውሞ የሚያነሳም አለ ፤ አሰልጣኝነት በጣም ከባድ ነው።” ሲል ስለ ኃላፊነቱ ክብደት ሲናገር ተደምጧል።

👉 ብዙ ቦታ የማይሰጣቸው አዕምሯዊ ጉዳዮች

የጨዋታ ሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በነበረው እና ፋሲል ከነማ መከላከያን በያሬድ ባየህ ብቸኛ ግብ ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ በጨዋታ ዕለት የተጠቀሙባቸውን ወጣት ተጫዋቾች የሥነልቦና ዝግጁነት ደረጃ ላይ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን ሲዘነዝሩ አድምጠናል።

“በእኔ ግምት የሥነልቦና ችግር አይቻለሁ ብዬ ነው የማምነው።
……የሥነ ልቦና ችግር ነው በወጣቶቹ ላይ ያየሁት።

እኛ የነገርናቸው በተቃራኒው ነበር። አንደኛ ከሆነ ቡድን ፣ አምስት ስድስት አፍሪካ ዋንጫ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ካሉበት ቡድን ፣ ያለፈው ዓመት ቻምፒዮን ከሆነ ቡድን ጋር ወጥታችሁ ራሳችሁን አሳዩ ነበር ያልናቸው። የሥነ ልቦና ችግር ነው ያየነው፤ ያ መሻሻል የሚችል ነው።

……ሦስት ነጥብ ተወስዶብናል ፤ በጨዋታ ደረጃ ስመለከተው ግን የእኛ ወጣት የመሆናቸው ችግር ነው ብዬ ነው የማምነው።

…..በእኔ ግምት ተጫዋቾች እንዲህ ዓይነት ዕድል ሲያገኙ ደስተኛ መሆን ነው የነበረባቸው ፤ ራሳቸውን ለማሳየት። ዕድሉን አግኝተው ካልተጠቀሙበት ግን በሌላ ነው ማለት ነው።

……ከልምድ ጋር ደግሞ ውጤቶች መጥፋት የለባቸውም። ልምድ እሰጣለሁ ብለህ ውጤት ሊጠፋ አይገባም። አሁን ያየሁት በመጫወት መበለጥ አይደለም። ሳትጫወት ባላጋራን አግዝፈህ ማየትን ነው። ሜዳ ላይ ያለኸው ግን አንተ ነህ። ማድረግ የሚገቡህን ነገሮች ትተህ በስሜት እና በሌሉ ነገሮች ተውጠህ መጫወት በሚገባህ መልኩ ሳትጫወት የመዘናጋት ነገር ሲኖር ነው።” – በጨዋታው ክፉኛ የተበሳጩ የሚመስሉት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ በድህረ ጨዋታ ቃለመጠይቅ ካነሷቸው ሀሳቦች በጥቂቱ የተወሰዱ ናቸው።

የእግርኳስ ሥልጠና መሰረታዊ ምሰሶዎች ተደርገው የሚወሰዱት አካላዊ ዝግጁነት ፣ ቴክኒክ ፣ ታክቲክ እንዲሁም አዕምሯዊ ጉዳዮች እንደሆኑ ይታወቃል። በአዕምሯዊ ጉዳዮች ውስጥም ተጫዋቾች በእግርኳስ ህይወታቸው በጣም ቁልፍ የሆኑትን ትኩረት ፣ በራስ መተማመን እና ውሳኔ አሰጣጥ የመሳሰሉ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ይሰራል።

በሀገራችን እግርኳስ ግን በንፅፅር ለሦስቱ ሥልጠናዎች ከሚሰጠው ትኩረት አንፃር አዕምሯዊ ጉዳዮች የተዘነጋው ምሰሶ ነው ብንል ለስህተት አይዳርገንም። የሰለጠኑት ሀገራት ከእነዚህ አራት ምሰሶዎች ባለፈ ማህበራዊ ክህሎቶችን እንደተጨማሪ ምሰሶ በመውሰድ ሥራዎችን መስራት በጀመሩበት በዚህ ዘመን በሀገራችን ግን ያለው ልምምድ በጣም ደካማ በሚባል ደረጃ መቀመጥ የሚችል ነው።

በዚህ ረገድ በወጣት ተጫዋቾች ዕድገት ውስጥ በአዕምሯዊ ጉዳዮች ላይ በቂ የሚባሉ ሥራዎችን መስራት አለመቻላችን በከፍተኛው የፉክክር እግርኳስ ደረጃ ላይ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። በዚህ ሂደት መሰረታዊው የአዕምሮ ክህሎት ብለን ከላይ ከተቀስናቸው ጉዳዮች መካከል በተለይ በራስ መተማመን ረገድ አሰልጣኝ ዮሐንስ እንዳነሷቸው ዓይነት ክፍተቶች በስፋት እንመለከታለን።

በፕሪምየር ሊግ ደረጃ በመጫወት ላይ የሚገኙ ወጣት ተጫዋቾች እምቅ የሆነ የቴክኒክ ክህሎት እና ፍጥነት የታደሉ እንደሆኑ ይታመናል። ነገር ግን ይህ ክህሎት ብቻ በራሱ የበቃ ተጫዋቾች አያደርጋቸውም። ወጣት ተጫዋቾች በተለይም ከኳስ ጋር ሲሆኑ ምቾት ተሰምቷቸው የፈለጉትን ማድረግ ቢችሉም በተቃራኒው ቡድናቸው ከኳስ ውጪ በሚሆንበት ጊዜ በመከላከሉ ረገድ ተሳትፎ ከማድረግ አንፃር ከሚነሳባቸው የተነሳሽነት ችግር አንስቶ በርካታ በሂደት ሊያሻሽሏቸው የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ ቢታመንም ትዕግስት በተሞላበት መንገድ እነዚህን ተጫዋቾች ለማሻሻል ከመጣር ይልቅ በአንድ ጀንበር የበቁ ተጫዋቾች እንዲሆኑ የመጠበቅ ዝንባሌ በስፋት ይስተዋላል።

በሀገራችን እግርኳስ ባለው ደካማ አረዳድ መነሻነት ለውጤታማነት አንዱ መሰረታዊ ከሆኑ ነገሮች መካከል ስፖርቱን ሊደግፉ ከሚችሉ ተዛማጅ የሙያ መስኮች ጋር በጋራ የመስራት ነገር ብዙም የተለመደ አይደለም። ከእነዚህም መካከል የስፖርት ሳይኮሎጂ ለእግርኳሱ ያለው አበርክቶ በቀላሉ የሚታይ ባይሆንም ይህን የሙያ መስክ ክለቦቻችን እምብዛም ሲጠቀሙበት አይስተዋልም።

የስፖርት ስይኮሎጂ መሰረታዊ እሳቤው የስፖርተኞችን የአዕምሮ ዝግጅት ደረጃ ጫናን ከመቋቋምምሆነ ወደ ኃላ ከሚጎትቱ በአዕምሮ የሚፈጠሩ አስተሳሰቦችን ተገዳድረው ስፖርተኞች የተሻለ ግልጋሎት እንዲሰጡ የማስቻል ሂደት ነው።

በመሰረታዊነት በትልቅ ደረጃ የበቃ ስፖርተኛ ለመሆን ተጫዋቾች በግልፅ የተቀመጡ ግቦችን በማስቀመጥ ተነሳሽ መሆን ፣ ልምዶችን በመቅሰም ሆነ አዎንታዊ ግብረመልሶችን በማጎልበት የራስ መተማመናቸውን ማሳደግ ፣ አዕምሮን ውጤታማ እንዲሆን ሊያግዙ የሚችሉ በጎ ልማዶችን በማዳበር ፣ አዕምሯዊ ውጥረቶችን ለማለዘብ የሚረዱ ልማዶችን በማዳር እና ሁሉን አቀፍ መረዳት (ስፖርቱን ሆነ ተጋጣሚን) እንዲፈጥሩ በማድረግ የበቃ አሸናፊ ስፖርተኛ የልቦና ውቅር እንዲኖራቸው ለማድረግ አሰልጣኞችም ሆኑ ሌሎች ባለሙያዎች በጋራ መሰራት ይኖርባቸዋል።

በዚህ ሂደት በሚፈለገው ልክ አዕምሯዊ ጥንካሬን እንዲያዳብር በተጫዋቾች ላይ በቂ ሥራ ባልተሰራበት ሁኔታ ተጫዋቾች በከፍተኛው ደረጃ ወደ መጫወት ከተሸጋገሩ በኋላ በጥቂት ጊዜ ውስጥ እነዚህን አዕምሯዊ ክህሎቶችን አላደበሩም በሚል ወቀሳ ማቅረብ በጉዳዩ ላይ ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ተጫዋቾችን ይበልጥ ጫና ውስጥ በመክተት በሚፈለገው ልክ ውጤታማ እንዳይሆኑ ሊያደርግ ስለሚችል አሰልጣኞች በተጫዋቾች (በተለይም ወጣት ተጫዋቾች) ላይ የሚሰጧቸው አስተያየቶች በአስተውሎት ሊሆኑ ይገባል።

👉 የጳውሎስ ጌታቸው የፀጉር ቁርጥ

በቀደሙት ጊዜያት ፀጉራቸውን ሙሉ በሙሉ በማስነሳት ኮፍያ በመልበስ የምናውቃቸው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ከሰሞኑ በአዲስ ፀጉር ቁርጥ ብቅ እላለው ባሉት መሰረት ቃላቸውን ጠብቀው በአዲስ የፀጉር ቁርጥ ብቅ ብለዋል።

ቡድናቸው ወልቂጤ ከተማ ሰበታ ከተማን 3-2 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በጭንቅላተቸው የመሀከለኛው ክፍል ላይ የሚገኘውን ፀጉራቸውን አሳድገው ብቅ ያሉት አሰልጣኙ በተጫዋችነት ዘመናቸው በሚታወቁበት የፀጉር የመጡ ሲሆን “መላጣ ነው ለሚሉኝ ምላሽ ይሁንልኝ” የሚል ይዘት ያለው አስቂኝ አስተያየት ሲሰጡ ተደምጠዋል።

👉 ከጫና ተንፈስ ያሉት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ

በውጤት ማጣት ከፍተኛ ጫና ውስጥ የቆዩት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቡድናቸው ወላይታ ድቻን ፍፁም ከሆነ የጨዋታ የበላይነት ጋር በማሸነፉ የዕረፍት ጊዜውን በተሻለ መረጋጋት ሊያሳልፉ የሚችሉበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

ወላይታ ድቻን ከተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጋር ማሸነፍ የቻለው ቡድናቸው ይህ ድል በቀጣይ የቡድኑን የውድድር ዘመን ይቀይር ይሆን የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ ቢሆንም ቡድኑ በተሻለ መነሳሳት የዕረፍት ጊዜውን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።