ኢትዮጵያ ቡና አንድ ተጫዋቹን አሰናብቷል

ኢትዮጵያ ቡና ካስቀመጠው የተጫዋቾች መመርያ ውጭ የሥነ ምግባር ግድፈት ፈፅሟል ያለውን ተጫዋች አሰናብቷል።

ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ በነበረው ቆይታ ካደረጋቸው ጨዋታዎች መካከል ከአንዱ ጨዋታ አስቀድሞ በስፖርታዊ ውርርድ ኢትዮጵያ ቡና ይሸነፋል በማለት አንድ ተጫዋች መወዳደሩ ታውቋል። ይህ አድርጊት ፈፅሟል የተባለው ተጫዋች ናትናኤል በርሔ ሲሆን በቡድን መሪው እና አሰልጣኞቹ አማካኝነት ድርጊቱን ስለመፈፀሙ የሰነድ ማረጋገጫ ከመቅረቡ ባሻገር እራሱ ተጫዋቹ ሁኔታውን አምኖ የእምነት ቃሉን ሰጥቷል።

በዚህም መሠረት ክለቡ ካስቀመጠው የተጫዋቾች የሥነ ምግባር መመርያ ውጭ እምነት አጉድሏል በማለት ቀሪ ኮንትራት እያለው ክለቡ ተጫዋቹን አሰናብቶታል። ከዚህም ተጨማሪም የኢትዮጵያ እግርኳስ የበላይ አካል በሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፒሊን መመርያ መሠረት አድርጊቱ ለሁለት ዓመት ከማንኛውም እግረኳሳዊ እንቅስቃሴ የሚያሳግደው በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ህጉን ተግባራዊ እንዲያደርግ ክለቡ በደብዳቤ መጠየቁን ሰምተናል።

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በክለቦች እና በተጫዋቾች መካከል ከሚፈጠሩ አለመግባባቶች አኳያ ይህ የቅጣት ውሳኔ ብዙ ያልተለመደ መሆኑ ሁኔታውን አስገራሚ አድርጎታል።