የዳኞች ኮሚቴ በርካታ የፕሪምየር ሊጉ ዳኞች ላይ ውሳኔ አስተላልፏል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ጥፋት ሰርተዋል ባላቸው ዋና እና ረዳት ዳኞች እንዲሁም ኮሚሽነሮች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

የ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር የዘጠኝ ሳምንታት ጉዞን በሀዋሳ ካከናወነ በኋላ ለብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ዝግጅት ባሳለፍነው ሳምንት መቋረጡ ይታወሳል። ለጨዋታዎቹ ዳኞችን የሚመድበው የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴም ጥፋት አጥፍተዋል ያላቸውን በርካታ ዳኞች ከሰዓታት በፊት እንደቀጣ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ቅጣት የተላለፈበት የመጀመሪያው የመሐል ዳኛ ምስጋናው መላኩ ነው። በአራተኛ የጨዋታ ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማን ያጫወተው ምስጋናው በዕለቱ ህግን በትክክል አልተረጎመም በሚል 6ወር ማንኛውንም ውድድሮች እንዳይመራ እና ከ6 ወር በኋላም ከፕሪምየር ሊጉ ወርዶ እንዲያጫውት ተወስኗል። በዕለቱ ኮሚሽነር የነበሩት መኮንን አስረስ ደግሞ 6 ወር ማንኛውንም ውድድሮች እንዳይመሩ ተደርጓል።

በአምስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ የሆነውን የድሬዳዋ እና ወልቂጤ ከተማን ፍልሚያ በመሐል አልቢትርነት የመሩት ብርሃኑ መኩሪያ እና ረዳቱ የነበሩት አንድነት ዳኛቸውም በተመሳሳይ 6ወር ማንኛውንም ውድድሮች እንዳይመሩ እና ከ6 ወር በኋላም ከፕሪምየር ሊጉ ወርደው እንዲያጫውት ተወስኗል። በስምንተኛ ሳምንት አምስት ግቦች የተቆጠሩበትን የሀዲያ ሆሳዕና እና ድሬዳዋ ከተማን ጨዋታ የመሩት አለማየሁ ለገሠ ደግሞ ለ6 ወራት ከማንኛውም ውድድር እንዲታገዱ ተደርጓል።

በተጨማሪም በስምንተኛ ሳምንት አርባምንጭ እና አዳማ ከተማ ሲጫወቱ ረዳት ዳኛ የነበረው ኤሊያስ አበበ 6ወር ማንኛውንም ውድድሮች እንዳይመራ እና ከ6 ወር በኋላም ከፕሪምየር ሊጉ ወርዶ እንዲያጫውት እንደተወሰነበት አረጋግጠናል።

ሊጉ በሀዋሳ በነበረው ቆይታ የመጨረሻ ሳምንት ላይ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ ረዳት ዳኛ የነበረው መሐመድ ሁሴን ውሳኔ እንደተወሰነባቸው አብዛኞቹ ዳኞች የ6 ወር እገዳ እና ከዛም ከሊጉ ወርዶ እንዲያጫውት ተበይኖበታል። የጨዋታው የመሐል ዳኛ የነበረችው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ደግሞ በጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንድትታለፍ ተደርጓል። እንደ ሊዲያ ሁሉ የኢትዮጵያ ቡና እና መከላከያን ጨዋታ የመራው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩም የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው ተደርጓል።

ከላይ እንደጠቀስነው መኮንን አስረስ ለ6 ወር ከማንኛውም ውድድሮች የታገዱ ሲሆን ኮሚሽነር ሰላሙ በቀለ እና ሰርካለም ከበደ ደግሞ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው እንደተወሰነ አውቀናል።