የከፍተኛ ሊግ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ውሎ

አምስተኛ ሳምንት የደረሰው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በሦስት ከተሞች መካሄዱን ቀጥሎ የተለያዩ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ሰበታ በሚካሄደው የምድብ ለ ጨዋታዎች ትናትና እና ዛሬ ሲካሄዱ ሶከር ኢትዮጵያ ዛሬ በተመለከተችው ሁለት ጨዋታዎች ተንተርሳ አጠቃለይ የጨዋታዎቹን ሪፖርት እንዲህ አሰናድታ አቅርባዋለች።

ዛሬ ጠዋት በተካሄደው ጨዋታ አንድም ጨዋታ ባለመሸነፍ እስካሁን መዝለቅ የቻለው ቡራዩ ከተማ ከጨዋታ ብለጫ ጋር ከንባታ ሺንሺቾን ሁለት ለምንም አሸንፎ ሊወጣ ችሏል። በጨዋታው ጅማሬ በፈጣን ማጠቃት አደጋ የሚፈጥሩት ቡራዩዎች ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ቶሉማ ንጉሴ እና በጫላ በንቲ አማካኝነት ለጎል የቀረበ ግልፅ አጋጣሚ ቢያገኙም ግብጠባቂው ያዳነባቸው በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች የፈጠሩት አደጋ ነበር። ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ቡራዩዎች በ16ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ ለቀኝ መሰመር ያደላን ኳስ ሲሳይ ዋጆ ኳሷን በእግሩ ጫፍ ቆርጦ ግሩም ጎል በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

በክፍት ሜዳ የጎል ዕድል መፍጠር የተቸገሩት ከንባታዎች ከቆመ ኳስ የተገኘውን ቅጣት ምት አንበሉ ኤፍሬም ታምራት የመታውን የግቡ አግዳሚ የመለሰበት በጨዋታው የተመለከትነው ብቸኛው የጎል ሙከራ ነው። የመከላከል አደረጃጀታቸው ጥሩ ያልሆኑት ከንባታዎች በቅብብሎሽ መሀል በሚፈጥሩት ስህተት በሚገኝ ክፍት ሜዳ ቡራዩወ ች ወደ ፊት በመሄድ የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር አመቺ የነበረ ቢሆንም ከውሳኔ ችግር ተጨማሪ ጎል ሳያስቆጥሩ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል። ከእረፍት መልስ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ የወሰዱት ቡራዩዎች ተጨማሪ ጎል በማስቆጠር ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረታቸው ተሳክቶላቸው በ66ኛው ደቂቃ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ቴዎድሮስ ታደሰ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል።

በቀሩት ደቂቃዎች ለቡራዩ ከተማ የጎል መጠኑን ማሳደግ የመሚችልበትን አጋጣሚዎች ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት ሲቀሩ ከንባታዎች በመጀመርያ አጋማሽ የነበረባቸው ድክመት ሳያርሙ በረጃጅም ኳሶች ወደ ጎል ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ አደጋ ሳይፈጥሩ በጨዋታውን ተሸንፈው ሊወጡ ችለዋል። ቡራዩዎች የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ምድባቸውን መምራታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

ዘጠኝ ሰዓት በቀጠለው የዛሬው ሁለተኛ ጨዋታ ቤንች ማጂ ቡናን ከስልጤ ወራቤ አገናኝቶ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ምንም እንኳን በጨዋታው ጎልአይቆጠርበት እንጂ በሁለቱም በኩል ጥሩ ፉክክር መመልከት ችለናል። በቤንች ማጂ ቡና በኩል አብይ ቡልቲ ከተከላካይ ጀርባ አፈትልኮ በመግባት ነፃ ኳስ አግኝቶ ያልተጠቀመበት እንዲሁም ጥላሁን በቀለ ከግራ መስመር ተሻግሮለት አምስት ከሀምሳ ውስጥ ያመከነው በቤንች ማጂ ቡና በኩል የሚያስቆጭ ዕድሎች ነበሩ።

በጨዋታው ሦስት ነጥብ ፍለጋ እስከ ጨዋታው መጠናቀቂያ ድረስ ሲታትሩ የተመለከትናቸው ስልጤ ወራቤዎች ሳዲቅ ሴቾ ለጎሉ በቅርብ ርቀት ለማመን የሚከብድ ኳስ ያመከነው አማካዩቹ ከድር አዩብ እና ፀጋአብ ዮሴፍ አንድ ሁለት ተቀባብለው በስተመጨረሻም ከድር ከሳጥን ውጭ አክሮ የመታው ግብጠባቂው እንደምንም ያወጣበት በመጀመርያው አጋማሽ በስልጤ ወራቤ በኩል የተፈጠረ ሙከራዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመርያው አጋማሽ የጠራ የጎል ሙከራ ባንመለከትም ስልጤ ወራቤዎች በተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። አጥቂዎቹ ሳዲቅ ሶቾ እና በሀይሉ ወገኔ እንዲሁም ስልጤ ወራቤ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል ተጫዋቹ ይገባኛል በማለት ሲወዛገቡበት ቆይተው በዛሬው ዕለት ለስልጤ ወራቤን ተቀላቅሎ የመጀመርያ ጨዋታውን ያደረገው የግራ መስመሩ አቤኔዘር አቴ ወደ ፊት እየሄደ ይፈጥረው የነበረው አደጋ ስልጤ ወራቤዎች ወደ ጎል በመቅረብ የተሻሉ እንደነበረ ማሳያ ነው። አልፎ አልፎ ወደ ፊት በመሄድ ከመጣር ውጭ በአመዛኙ በቁጥር በዝተው መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉት ቤንቺ ማጂ ቡናዎች የስልጤዎችን ጎል ሳይፈትሹ ወጥተዋል። በመጨረሻም ጨዋታው ብዙም የተለየ ነገር ሳይኖረው ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ትናንት በዚሁ ምድብ በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ጅማሮውን አድርጎ ሰንዳፋ በኬ ለገጣፎ እና ኮልፌ ቀራንዩ በተመሳሳይ ውጤት ተጋጣሚያቸውን አንድ ለምንም አሸንፈዋል።

ከሽንፈት የመጣው ሰንዳፋ በኬ በውድድሩ ላይ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነውን ቂርቆስን ጠዋት አግኝተው ከእረፍት በኃላ በ68ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው ታምሩ ባልቻ አማካኝነት ባስቆጠረው ብቸኛ ጎል አሸንፎ ሊወጣ ችለዋል። ረፋድ በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ ለገጣፎ ከተማን ከከፋ ቡና አገናኝቶ ለገጣፎዎች በ78ኛው ደቂቃ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት ቀለመወርቅ ወደ ጎልነት ቀይሮ ለገጣፎ ደረጃውን ከመሪው በአራት ነጥብ ዝቅ ብለው ሁለተኛ ደረጃ እንዲቀመጥ አስችሏቸዋል።

የትናንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የኮልፌ ቀራንዩ እና የቡታጅራ ከተማ ጨዋታ ድራማዊ ትዕይንት አስተናግዶ በኮልፌ አሸናፊነት ተጠናቋል። ጨዋታው ጅማሮ ላይ የኮልፌ ቀራንዩው ግብጠባቂ ከግብ ክልሉ ውጭ ኳስ በእጅ በመንካቱ በዕለቱ ዳኛ በቀጥታ በቀይ ካርድ መውጣቱን ተከትሎ ሰባ ደቂቃ የተጫዋች ቁጥር አንሶባቸው የቆዩት ኮልፌዎች የጨዋታው መጠናቀቂያ አምስት ደቂቃ ሲቀረው እሱባለው ሙልጌታ ባስቆጠረው ብቸኛ ጎል ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ይዘው በመውጣት ደረጃቸውን አሻሽለዋል።