የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከአራተኛ ሳምንት በኋላ ተቋርጦ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ይጀምራል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ለኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከታንዛኒያ ጋር ለሚያደርገው የማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅት ከታህሳስ 30 በኋላ ይቋረጣል፡፡

ኮስታሪካ በምታስናግደው የ2022 የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በአፍሪካ አህጉር የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ እየተካፈለ ወደ መጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታዎቹ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከታንዛኒያ ጋር በቀጣዩ ወር አጋማሽ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን እንደሚያከናውን ካፍ አሳውቋል፡፡ ለዚህ ውድድር ሲባል በሀዋሳ እየተደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድር ነገ ታህሳስ 28 እና 29 የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከተደረጉ በኋላ ለብሔራዊ ቡድኑ በቂ ዝግጅት ሲባል ይቋረጣል፡፡

በአሰልጣኝ ፍሬው ሀይለገብርኤል የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ጠንካራ ተሳትፎን በማጣሪያው በማድረግ ሶስት ሀገራት በማሸነፍ አራተኛ ጨዋታው ላይ የደረሰ ሲሆን በእኛ አቆጣጠር ከጥር 13-15 የመጀመሪያ የማጣሪያ መርሀግብሩን ከታንዛኒያ ጋር ከሜዳው ውጪ ዳሬሰላም ላይ የሚያደርግ ሲሆን የመልሱን ጨዋታም ከሳምንት በኋላ በአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚከውን ሶከር ኢትየዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡


የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከነገ ነገ አልያም ከነገ በስቲያ ለተጫዋቾቹ ጥሪ ካደረገ በኋላ ዝግጅቱን ታህሳስ 30 ዕለተ ቅዳሜ አዲስ አበባ ላይ ይጀምራል፡፡