”… ካሜሩን እንዲህ ነው ብሎ ጫና ማብዛትም ተገቢ አይደለም” አሠልጣኝ ውበቱ አባተ

👉🏼 ” በጊዜ ቀይ መምጣቱ ዕቅዳችንን አበላሽቶታል”

👉🏼 ” በአስር ተጫዋች የሚያጠቃ ቡድን ዓለም ላይ የለም”

👉🏼 ” አንድም ተጫዋች የVAR ልምድ የለውም”

👉🏼 ” ዕምነታችን ተጫዋቾቻችን ላይ ነው”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ከደቂቃዎች በፊት ከሀገራችን ጋዜጠኞች ጋር በትናንቱ ጨዋታ ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቡድን በካሜሩን አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው የአህጉራችን ትልቁ ውድድር ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። በትናንትናው ዕለትም የምድቡን የመጀመሪያ ጨዋታ ከኬፕ ቨርድ አቻው ጋር አከናውኖ አንድ ለምንም በሆነ ውጤት ተሸንፏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በውድድሩ አዘጋጅ ካፍ አማካኝነት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ የድህረ-ጨዋታ አስተያየት መስጠታቸው የሚታወቅ ሲሆን ዛሬ ምሽት ደግሞ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመቻችነት በበይነመረብ አማካኝነት አሠልጣኙ ከሀገራችን የብዙሃን መገናኛ አባላት ጋር ቆይታ አድርገዋል። በቅድሚያም አሠልጣኙ ተከታዩን ገለፃ አድርገው በዙም የተደረገው መግለጫ ተጀምሯል።

“ትናንት የመጀመሪያ ጨዋታችንን ከኬፕ ቨርድ ጋር አድርገናል። ከጨዋታው በፊት በጥሩ ሁኔታ ለመዘጋጀት ሞክረናል። ከሁለት ተጫዋቾች ውጪም ጉዳት አልነበረብንም። ወደ ጨዋታው የገባነውም ካለን አቅም አንፃር በማጣቃት ላይ የተመሰረተ ነገርግን ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ ለመጫወት ነበር። እንዳያችሁት ከ10 ደቂቃ በኋላ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ተገደናል። ይህንን ተከትሎም በተገቢው ደረጃ ተጫውተናል ብዬ አላስብም። ግን ባለው ነገር ጨዋታው ለመቆጣጠር ሞክረናል። 80 ደቂቃ ብዙ ነው። ይህንን ያህል ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋች ተጫውቶ በጠባብ ውጤት መሸነፍ መጥፎ አደለም ፤ የሽንፈት ጥሩ ባይኖርም። የሆነው ሆኖ ከጨዋታው በኋላ ዛሬ ወደ መደበኛ ልምምዳችን ተመልሰናል።” በማለት ገለፃ አድርገዋል። በመቀጠል ደግሞ ከጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ መሰጠት ተጀምሯል።

በቀይ ካርዱ በኋላ ስለነበራቸው ዕቅድ ?

ቡድናችን ከኳስ ጋር የሚያሳልፍ ነው። ኳስ ዋና መሳሪያችን ነው። ቁጥሮቹም የሚያሳዩት ይህንን ነው። በተሸነፍንባቸውም ጨዋታዎች እንኳን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ነበረን። ትናንትም ተደጋጋሚ ኳሶች ወደ እኛ ግብ ክልል ይመጡ ነበር። የእነዛ ሙከራዎች መነሻ ራሱ እኛ ኳሱን በደንብ ስላልተቆጣጠርን እና ለእነሱ በሚመች መልኩ ስለተጫወትን ነበር። እኛ የበለጥናቸው ቀይ ካርድ በማየት ብቻ ነው። እነሱ የተሻሉ ነበሩ። ኬፕ ቨርድ ከዚህ በፊት ከገጠምናቸው ቡድኖች ጠንካራው ነው ብዬ መናገር አልችልም። ግን ይህ የአፍሪካ ዋንጫ ነው። ይህንን መረዳት ያስፈልጋል። ትልቅ ልምድ ይፈልጋል። በጊዜ ቀይ መምጣቱ ዕቅዳችንን አበላሽቶታል። ተገደን ነው ወደዛ መንገድ የገባነው። የተጫዋቾችንም የራስ መተማመን ያወረደው ለዛ ነው። ረጃጅም ኳሶችም በዝተው ነበር። ይህም እነሱን ተጠቃሚ አድርጓል።

ከፊት ያለው ጊዜ ረጅም ነው። እስከ እረፍት ገፍተን ከዛ ወደ ሌላ ዕቅድ እንገባለን የሚል ነገር ነበር ያሰብነው። ከእነሱ ጥቃቶች ቢኖሩም ያንን ተቆጣጥረናል። ጎሉን ካየህ ከእኛው እግር የተነሳ ኳስ ነው። እርጋታ ስላልነበረን ነው። ቢያንስ ሰዓቱን ታሳቢ ማረግ እንችል ነበር። ዕረፍት መድረስ አልቻልንም ፤ ጎል ገባብን። ያለው ብልጫ እንዳይታይ ማድረግ ይጠበቅብን ነበር።

የዕረፍት ሰዓት ስለተወያዩት ነገር?

በአስር ተጫዋች የሚያጠቃ ቡድን ዓለም ላይ የለም። በአስር ሰው ግን መከላከል ይቻላል። ይህንንም ነግረናቸዋል። ከዕረፍት በኋላ ያን ያህል መጥፎ አልነበርንም። እንደ ከዚህ ቀደሙ አንጫወት እንጂ ውጤቱ የሚያዋርድ አይደለም። የጎል ናዳ አለማስተናገዳችንም ተጫዋቾቹን ማድነቅ አለብን።

ከቀይ ካርዱ በኋላ ስላደረጉት የተጫዋች ለውጥ?

ጌታነህን አሶጥቶ አቡበከርን ወደ ፊት አድርጎ ምኞትን ማስገባት ይቻል ነበር። ግን ሜዳ ላይ ከሚቀሩት አራቱ አማካኞች የመስመር አማካይ ሆኖ የሚጫወት የለም። ስለዚህ ጌታነህ ኳስ ይዞ ብዙ ባይረዳን እንኳን ከኳስ ውጪ ያግዘናል ብለን ነበር። ይህንንም በሚገባ ተወጥቶታል። እስከወጣበት ሰዓትም ረድቶናል። እንደተባለው አማካይ ማስገባት ይቻል ነበር። ግን ይህንን አልመረጥንም። ተጋጣሚያችን ደግሞ የሚጫወተው በመስመር አጨዋወት ነው። በክፍት ጨዋታም ሆነ በቆመ ኳስ በቀኝ እየሄዱ ወደ ግራ ቋሚ ያሻሙ ነበር። ይህንን ልምምድ ላይ ሰርተን ነበር። ይህንንም በደንብ ዘግተናል። ሁለቱ የመስመር ተጫዋቾችን ያልነካነውም ወደ ኋላ እየመጡ እንዲያግዙ ነው።

በሥነ ልቦና ረገድ ስለነበራቸው ዝግጁነት ?

እየሄድንበት ያለው መንገድ ጥሩ እንደሆነ ይሰማኛል። ይህ ግን ገና ጅማሮ ነው። ሁሉም የቡድኑ አባል ይህ ይሰማቸዋል። ቡድኑ ገና አልበሰለም። ሁሉም በዕኩል ሥነ ልቦና ላይ ናቸው ብሎ መናገር ይከብዳል። በየአፍሪካ ዋንጫው የሚሳተፍ ቡድን ቢሆን እሺ። ግን ይህ አደለም። የሥነ ልቦና ባለሙያ አለን። ተጫዋቾቹን እየረዳ ነው። በራስ መተማመን ግን ስለተወራ ብቻ አይመጣም። በብዙ ነገር ሊመጣ ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ ያለህ ነገር ይሰበራል ወይ የሚለውን መፈተን አለበት። ቀዩ ሁላችንንም አስደንግጦናል። በዛ ላይ ያሬድን ነው ያጣነው። እሱ ቡድኑ በጣም የሚፈልገው ተጫዋች ነው። ሁላችንም በእነደዚህ ዓይነት ውድድር ላይ ልምድ ስለሌለን ብዙ ማለት አይቻልም።

ስለ ተጫዋቾች እንቅስቃሴ ?

ከልምድ ጋር የሚያያዝም ሊሆን ይችላል። በቃል ከመግባባት ባለፈ ተያይቶ መግባባት ጋር አለመድረሳችን የጎዳን ይመስለኛል።

ወደ አፍሪካ ዋንጫው ሲያመሩ ስላስቀመጡት ግብ ?

መካፈላችን ብቻ በቂ ነው። እኔም ከተጣለብኝ ኃላፊነት አንፃር በቂ ነው ማለት ይቻላል። ግን ቡድኑ እያሳየ ካለው ብቃት አንፃር እና ምርጥ ሦስተኛ ቡድንም የማለፉ ዕድል ስላለ ዕምነቱን አመጣን። ይህ ጫና ተጫዋቾቹ ላይ ይፈጥራል ወይ ማለት አይቻልም። ይህን ካላደረጋችሁ ብለን አናስጨንቅም። ይህንን ለማሳካት ደግሞ ይዘነው በመጣነው ነገር መንጠልጠል እንዳለብን አምነናል። እንደ ፌዴሬሽን ፍላጎቱ አለ። ይሳካል የሚልም ዕምነት አላቸው። ይህንን ማሳካት ቀላል አይደለም። አሁንም ክፍት ነው ፤ ዕድሉ አለ። ይህንን በማለታችንም የደረሰብን ነገር የለም።

በውድድሮች ቀይ ካርዶች ስለመብዛታቸው?

ትናንት ቫር ባይኖር ያሬድ አይወጣም ነበር። አንድም ተጫዋች የቫር ልምድ የለውም። ካርድ መደጋገሙ አጋጣሚ ይመስለኛል። አብዛኞቹ ተጫዋቾች በሀገር ውስጥ የተጫወቱ ናቸው። የምንገጥማቸው ደግሞ ከየት እንደመጡ እናውቃለን። በሊጉ የምናየውን ነገር ትናንት አላየንም። ዳኛ ከበባ ምናምን አልነበረም። ከቀዩ በኋላም ጥፋት የተሰሩብን አጋጣሚዎች ነበሩ። ግን ከበባውን አላደረጉም። ይህ ተጫዋቾቹን የሚያስደንቅ ነው። እግርኳስ ድንገት ብዙ ነገር ይፈጠርበታል። ያጋጥማል። ባለፉት ጨዋታዎች ቀይ አላየንም። ከብዙ ጨዋታዎች በኋላ ነው ቀይ ያየነው። ቢጫም ትንሹ የተመዘገበበት ነው። ልምምድ ላይም ቀይ ይፈጠራል ብለን ሳይሆን ብልጫ ቢወሰድብን ብለን የምንሰራቸው ሥራዎች ነበሩ።

ቀጣይ ጨዋታ?

ዕምነታችን ተጫዋቾቹ ላይ ነው። የአሠልጣኙ ልበ ሙሉ መሆን የሚሰጠው ነገር አለ። ግን እነሱ ከውስጣቸው መጫወት አለባቸው። ካሜሩን እንዲህ ነው ብሎ ጫና ማብዛትም ተገቢ አይደለም። ካሜሩን ጠንካራ ቡድን ነው። ከአራት ቀን በኋላ ስለሚጫወቱ የሪከቨሪ ጉዳይ ላይ እናስባለን። ከትናንቱ ጨዋታ በፊትም ይህንን ታሳቢ አድርገን ስንዘጋጅ ነበር። የ2013ቱንም እንደ ተሞክሮ እንወስዳለን።

ስለጌታነህ ለውጥ ?

ጌታነህን ቀድመን ማስወጣት እንችል ነበር። ግን እንዳልኩት እስከ ዕረፍት ዜሮ ለዜሮ ብንሄድ ከዛ በኋላ ኳሱን ተቆጣጥረን ለመጫወት አስበን ነበር። አስገዳጁን ለውጥ ካደረግን በኋላ ቀድመን ጌታነህን ብንቀይር የሚቀረን የለውጥ ጊዜ አንድ ብቻ ነበር። ጉዳት ምናምን ቢኖር እንኳን ከባድ ነበር። ለዛ ነው ለውጡን ያዘገየነው።

ተጫዋቾቹ ጋር የነበረው ስሜት ?

እስከ ጨዋታው መጀመሪያ ድረስ ወይም ቀዩ ድረስ ፍራቻ ወይም የተለየ ነገር አላየሁም። ሁሉም ጋር የነበረው ስሜት ከዚህ ቀደም የነበረውም ነገር ለማስቀጠል እና አንድ ነገር ለማምጣት የነበረ ፍላጎት ነው። እንደውም ፍላጎታቸው ቅጥ አጥቶ እንዳይሄድ ነበር ጥረታችን። ከቀዩ በኋላ ያየነው ግን ተቃራኒ ነው። ዕረፍት ላይ ግን የቻልነውን አድርገን ለማስተካከል ሞክረናል። ካለቀ በኋላ ደግሞ ተጫዋቾቹ ሽንፈቱን ጠልተውታል። ይህ ጥሩ ነው። ግን የተጋነነ ጭንቀት ውስጥ እንደዳይገቡ አድርገናል። ብዙ ወጣት ተጫዋቾች አሉ። እነዚህ ተጫዋቾች ከዚህ በኋላም በአፍሪካ ዋንጫው እንዲሳተፉ ነው የምመኘው። ይህን ለማስቀጠልም ጥሩ መንገድ ላይ ናቸው። ዛሬ ግን ሁሉም ተመልሷል። ስለቀጣዩ ጨዋታ ነው የምናስበው።