የአፍሪካ ዋንጫ ልዩ ዘገባ ከካሜሩን | የዳዋ ሆቴሳ እና ፋሲል ገብረሚካኤል አሁናዊ ሁኔታ

ከሰዓታት በፊት ባቀረብነው ዘገባ የሽመልስ በቀለን የጉዳት ሁኔታ አስመልክቶ መረጃ መድረሳችን ሲታወቅ በማስከተል ዳዋ ሆቴሳ እና ፋሲል ገ/ሚካኤል በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የተጠናቀረ ዘገባ በቀጣይ እናቀርባለን።

አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ መጠነኛ የቁርጭምጭሚት ጉዳት አጋጥሞት ከልምምድ ከመራቁ ባሻገር ከትናንትናው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ይታወሳል። በዛሬው ዕለት ሙሉ ለሙሉ ከጉዳቱ በማገገሙ የመጀመርያውን ልምምዱን በሚገባ ከቡድን አጋሮችን ሲያከናውን ተመልክተነዋል። ይህን ተከትሎ ለቀጣይ ጨዋታ ዝግጁ እንደሆነ ተረድተናል።

ሌላኛው መጠነኛ የትከሻ ጉዳት እንዳጋጠመው እና ከትናንትናው ጨዋታ ውጪ እንደነበረ የተገለፀው የግብ ዘቡ ፋሲል ገብረሚካኤልም በዛሬው ዕለት ከሽመልስ በቀለ ጋር አብሮ ሜዳውን የመሮጥን እንስቃሴ ሲያከናውን ተመልክተነዋል። ሆኖም ግን ብዙም ሳይቆይ ልምምዱን በማቆም ብሔራዊ ቡድኑ ልምምዱን እስኪጨርስ ተቀምጦ ለመጠበቅ ተገዷል። ሙሉ ለሙሉ ካለበት ጉዳት እንዳላገገመም ከሁነቱ መታዘብ ይቻላል።

ከዚህ ውጭ በቡድኑ ውስጥ ሌላ የጉዳት ዜና እንደሌለ እና በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ለማየት ችለናል።