ሪፖርት | ሲዳማ ቡና የውድድር ዘመኑን ሦስተኛ ድል አሳክቷል

በድሬዳዋ ስታዲየም አመሻሹን በተደረገው ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች ከመመራት ተነስተው በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ባህርዳር ከተማን በመርታት ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።

ነቃ ባለ ፉክክር የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎችን የተመለከተንበት ነበር። ይግዙ ቦጋለ ለሲዳማ ቡና ባደረጋት ሙከራ በጀመረው ጨዋታ ዓሊ ሱሌይማን ለባህርዳር ከተማ ሁለት ግሩም የማግባት አጋጣሚዎችን ቢያገኝም መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።

በንፅፅር የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ባህርዳር ከተማዎች በተለይ የአጥቂ አማካያቸው ፍፁም ዓለሙ በነፃነት የኳስ መቀበያ አማራጮችን በመፍጠር እና የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመምራት እድሎችን መፍጠር ሲችሉ በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ በፈጣን የመልሶ የአማካዮቹ ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ፍሬው ሰለሞን የሚነሱ እና ከባህርዳር ተከላካዮች ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ተደጋጋሚ የማጥቃት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል።

በ30ኛው ደቂቃ ላይም ፍፁም ዓለሙ ወደ ቀኝ ካደላ መነሻ ራሱ ያስጀመረውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳጥን ውስጥ ተገኝቶ በግሩም ሁኔታ በመምታት ባህርዳር ከተማን ቀዳሚ ያደረገችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ እስከ መጀመሪያው አጋማሽ ፍፃሜ ድረስ ሲዳማ ቡናዎች የአቻነቷን ግብ ፍለጋ በተሻለ መነሳሳት ጨዋታውን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም የጠራ የግብ እድል ግን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽን ከተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ጋር የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች ባህርዳር ከተማዎች በአጋማሹ ጥንቃቄን ቀላቅለው በመጫወታቸው ታግዘው የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል። ነገርግን እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ግን በመጨረሻው የማጥቂያ ሲሶ ላይ ግን የነበራቸው ሂደት ውጤታማ አልነበረም። ያም ሆኖ በ70ኛው ደቂቃ ላይ ከሰከንዶች በፊት ዳዊት ተፈራን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ብሩክ ሙሉጌታ ከማዕዘን የተሻገረችውን ኳስ በጨዋታው የመጀመሪያ በነበረችው ንክኪ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ታድያ በዚህች ግን ይበልጥ የተነቃቁ የሚመስሉት ሲዳማ ቡናዎች የማሸነፊያዋን ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት በ88ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል። ፍሬው ሰለሞን በግሩም ሁኔታ ያቀበለውን ጊዜውን የጠበቀ ኳስ ተጠቅሞ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከተከላካዮች አምልጦ በመግባት ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ ይገዙ ቦጋለ የውድድር ዘመኑን ስድስተኛ እንዲሁም ቡድኑን አሸናፊ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

የውድድር ዘመኑን ሦስተኛ ድል ያሳኩት ሲዳማ ቡናዎች ነጥባቸውን ወደ 14 በማሳደግ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችሉ ባህርዳር ከተማ በተመሳሳይ ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።