​የኢያሱ ለገሰ ጉዳይ መቋጫ አግኝቷል

ለወራት ጅማ አባ ጅፋር እና አዲስ አበባ ከተማን ሲያወዛግብ የቆየው የኢያሱ ጉዳይ በስተመጨረሻ መልስ አግኝቷል።

ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር እስከ ጥቅምት 30 ቀን ውል የነበረው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ኢያሱ ለገሰ  በቅድመ ስምምነት ዘንድሮ ለጅማ አባ ጅፋር ለመጫወት መስማማቱ ይታወሳል። እስከ ሦስተኛ ሳምንት ለአዲስ አበባ ከተማ ከተጫወተ በኋላ ተጫዋቹ በክለቡ የመቀጠል ፍላጎት ቢኖረውም ጅማ አባ ጅፋሮች ‘በቅድመ ስምምነቱ መሠረት ወደ ክለባችን ሊቀላቀል ይገባል’ በማለት ጥያቄ በማንሳታቸው በሁለቱ ክለቦች መካከል ለወራት ውዝግብ ተፈጥሮ ቆይቷል።

በመጨረሻም የተጫዋቹ ባለ ንብረት በቅድመ ስምምነቱ መሠረት ጅማ አባ ጅፋር መሆኑን ፌዴሬሽኑ በመወሰኑ ምክንያት ኢያሱ ለገሰ በዛሬው ዕለት ከፌዴሬሽኑ መልቀቂያውን በመውሰድ ወደ ድሬደዋ በማቅናት ጅማ አባ ጅፋርን ተቀላቅሏል።

ይህን ተከትሎ ተጫዋቹ ለስድስት ሳምንት ከራቀበት ሊግ ዳግመኛ በመመለስ ከአስረኛው ሳምንት ጀምሮ ለጅማ አባ ጅፋር አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል። በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የሚገኘው ክለቡ ይህንን ውሳኔ ተከትሎ በመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ ላለበት ችግር ኢያሱን ማግኘቱ አማራጭ እንደሚፈጥርለትም ይታመናል።