​አቡበከር ኮንትራት ለመፈረም መቃረቡ ተሰምቷል

ከደቡብ አፍሪካ የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለከቱት አቡበከር ናስር ለማሜሎዲ ሳንዳውንስ ለመፈረም ከጫፍ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የምን ጊዜውም ኮከብ ግብ አግቢነት ክብርን በእጁ ያስገባው የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ከሀገር ውጪ የመጫወት ዕድሉ ሰፊ ስለመሆኑ ሲነገር ቆይቷል። ተጫዋቹ ከዋሊያዎቹ ጋር በአፍሪካ ዋንጫ መድረክ ካደረገው ተሳትፎ መልስም ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ረስተንበርግ በሚገኘው የማማሎዲ ሳንዳውንስ የልምምድ ስፍራ ለአንድ ሳምንት ያህል የሙከራ ጊዜን አሳልፏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ማምሻውን መቀመጫውን በኬፕታውን ያደረገው ኪክኦፍ የተሰኘው ተነባቢ ድረገፅ ተጫዋቹ በነበረው የሙከራ ጊዜ ክለቡን መማረክ እንደቻለ ዘግቧል። ይህንንም ተከትሎ የሀገሪቱ የዝውውር መስኮት ዛሬ ለሊት ከመዘጋቱ በፊት አቡበከር ከደቡብ አፍሪካው ክለብ ጋር የሚያስተሳስረውን ውል የመፈረሙ ነገር እርግጥ ወደ መሆን መቃረቡን አስነብቧል።

ድረገፁ ለክለቡ ቅርብ ከሆነ ምንጭ አገኘሁት እንዳለው መረጃ ከሆነ አጥቂው በነበረው የሙከራ ጊዜ የክለቡን የቴክኒክ ኃላፊዎች ቀልብ መሳቡን ጠቅሶ በአሁን ሰዓት ክለቡ ጉዳዩን አስመልክቶ ስብስባ መቀመጡን ጠቅሷል። እንደ ምንጩ ተጨማሪ መረጃም ከሆነ ሳንዳውንስ ተጫዋቹን አሁን ላይ አስፈርሞት ቀሪውን የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ቡና አሳልፎ እንዲመለስ ሀሳቡ ሊኖር እንደሚቻም ጨምሮ ፅፏል።