ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከ35 ቀናት በኋላ በተመለሰው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ የጨዋታ ሳምንት ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮች በዚህኛው ፅሁፋችን ለመዳሰስ ሞክረናል።

👉 ድንቅ የጨዋታ ዕቅድ ፈረሰኞቹን የሰንጠረዡን አናት አቆናጧል

በጨዋታው ሳምንት ከፍተኛ ግምት አግኝቶ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ በፈረሰኞቹ የ4-0 የበላይነት ተጠናቋል። ከውጤቱ በስተጀርባ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው ይዘውት የገቡት የጨዋታ ዕቅድ ትኩረትን የሚስብ ነበር።

በጨዋታው ጊዮርጊሶች ከኳስ ውጪ ወደ ራሳቸው ሜዳ ሸሸት ብለው በጥንቃቄ በመከላከል እንዲሁም ኳሶችን በሚያገኙባቸው ቅፅበቶች ደግሞ በፈጣን መልሶ ማጥቃት እና ከመሰመር ተከላካዮች በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች ፋሲል ከነማ ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ይዘውት የገቡት የጨዋታ ዕቅድ ፍፁም ደካማ በነበረው የፋሲል የመከላከል መዋቅር ጋር ተዳምሮ ውጤታማ አድርጓቸዋል።

በመሰረታዊነት ከአራቱ የመልሶ ማጥቃት መንገዶች ውስጥ አቤል ያለው ባስቆጠራቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ግቦች ላይ ቀጥተኛ ቅብብሎች (Direct Pass) በግልፅ እና በላቀ ጥራት ተተግብረው ተመልክተናል። የመጀመሪያው የአቤል ያለው ግብ የተቆጠረችበት ሂደት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሰጠባቸውን የማዕዘን ምትን በአግባቡ ተከላክለው ግቧ እስክትቆጠር በድምሩ 12 ሰከንድ በፈጀ ሂደት እና በሦስት ተጫዋቾች መካከል በተደረጉ 5 የኳሱን ሂደት ለማፍጠን የረዱ ቅብብሎች ታግዘው በአቤል ያለው የተረጋጋ አጨራረስ ማስቆጠር ችለዋል።

ሁለተኛዋም ግብ ስትቆጠር እንዲሁ በተመሳሳይ መሀል ሜዳ ላይ የነጠቁትን ኳስ 6 ሰከንድ በፈጀ ሂደት በተመሳሳይ አቤል ያለው ከተከላካዮች አምልጦ በመግባት ከእስማኤል ኦሮ-አጎሮ የደረሰውን ኳስ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።

በመከላከሉ ላይ ይበልጥ አተኩረው እንዲጫወቱ ከተደረጉት ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች አንዱ የነበረው ሱሌይማን ሀሚድ ለሦስተኛው ግብ መነሻ የነበረችውን ኳስ በረጅሙ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲያደርስ አራተኛዋ ግብ በአስቻለው ታመነ ስህተት የተገኘች ነበረች።

ፈረሰኞቹ በጨዋታው ይበጀናል ያሉት የጨዋታ ዕቅድ በሚገባ ውጤታማ ያደረጋቸው ሲሆን በተጨማሪም ድሉ የተመዘገበው በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ቀጥተኛ ተፎካካሪያቸው ከሆነው የአምና አሸናፊው ፋሲል ከነማ ላይ መሆኑ ደግሞ በሥነልቦና ረገድ ውጤቱን ከፍ ያለ ትርጉም ይሰጠዋል። በቀጣይም ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚኖሩት ጨዋታዎች ይህን የአሸናፊነት ስሜት በማስቀጠል ምን ያህል ሊጓዝ ይችላል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 ሲዳማ ቡና እየተነቃቃ ይገኛል

በተጠበቀው ልክ ጥሩ አጀማመርን ማድረግ ተስኖት የነበረው ሲዳማ ቡና ቀስ በቀስ ከሰመመኑ እየነቃ መጥቷል። ሊጉ ከዕረፍት ሲመለስም ጠንካራውን ባህርዳር ከተማን ከመመራት ተነስቶ በማሸነፍ በሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታ አውንታዊ ውጤትን ማስመዝገብ ችሏል።

ባህርዳር ከተማን ከመመራት ተነስቶ በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ሁለት ለአንድ ባሸነፈበት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ወደ መሀል ሜዳ ተጠግቶ የመከላከል ፍላጎት የነበራቸው ባህርዳር ከተማዎች ትተውት የሚወጡትን የሜዳ ክፍል ከፍሬው ሰለሞን እና ቴዎድሮስ ታፈሰ በሚጣሉ የተመጠኑ ኳሶች ለማጥቃት ጥረት አድርጓል።

በዚህም ሂደት ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር ባለፈ ይገዙ ቦጋለ ያስቆጠራት የማሸነፊያ ግብ በዚህ ሂደት የተገኘች ነበረች። ነገርግን ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ አሁንም ቢሆን ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉበት የሚያሳይ የጨዋታ ዕለት ነበር ያሳለፈው።

በተለይ ደግሞ ከአራቱ ተከላካዮች ፊት በሚና የተለያዩ የሚመስሉ ሁለት አማካዮች (በ6 ቁጥር ሚና) የተጠቀመው ሲዳማ ተጫዋቾቹ በመከላከል ወቅት በነበርራቸው ደካማ የቦታ አረዳድ እና አጠባበቅ የተነሳ በተደጋጋሚ ለአደጋ ሲጋለጥ ተመልክተናል። ይህም ሂደት በተለይ ፍፁም ዓለሙ ለባህርዳር ከተማ ባስቆጠራት የመጀመሪያ ግብ ላይ በደንብ ተስተውሏል።

እንደ ቡድን ግን ከፍ ባለ ጫና ውስጥ ለከረመው ሲዳማ ቡና በተከታታይ ያስመዘገባቸው ውጤቶች የቡድኑን መንፈስ በአዎንታዊነት ለመቀየር ከሚኖረው ጥቅም አንፃር እንዲሁም የድሬዳዋውን ቆይታ በተሻለ ውጤት ለማጠናቀቅ የሚረዳ ዓይነተኛ ድል አስመዝግቧል።

በሰባተኛ የጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከነማ አቻው 4-0 በሆነ ውጤት አሰቃቂ ሽንፈትን ካስተናገደ ማግስት ሲዳማ ቡና በተከታታይ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ ሰባት ማሳካት ችሏል። በዚህም በሰባት ነጥብ ከነበሩበት ከ13ኛ ደረጃ በአሁኑ ወቅት በ14 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ በቅተዋል።

👉 ሁለት አጋማሽ ሁለት መልክ – ባህርዳር ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና

በጨዋታ ሳምንቱ ከተመለከትናቸው ስምንት ጨዋታዎች መካከል ባህርዳር ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ተጋጣሚዎቻቸው በነበሩት ሲዳማ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ ላይ የነበራቸውን የበላይነት በሁለተኛው አጋማሽ ማስቀጠል አለመቻላቸው ተከትሎ ነጥብ ለመጣል ተገደዋል።

ባህርዳር ከተማ በሲዳማ ቡና በተሸነፈበት ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ በተሻለ ፍላጎት እና አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ ተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሀል ሜዳ አስጠግተው ሜዳውን አጥብበው ለመጫወት ጥረት አደረገዋል። በዚህም በተለይ የአጥቂ አማካያቸው ፍፁም ዓለሙ በነፃነት እየተንቀሳቀሰ አደጋ ለመፍጠር ሲሞክር ተመልክተናል።

በተመሳሳይ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ወልቂጤ ከተማን ኳሶችን እንዳይመሰርቱ ጫና በማሳደር እንዲሁም መሀል ሜዳ ደግሞ በቁጥር ብልጫን ወስደው ወልቂጤ ከተማዎችን መፈተን ችለዋል። በዚህ ሂደትም የመስመር ተመላሾቻቸው የነበሩትን እያሱ ታምሩ እና ብርሃኑ በቀለን በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ይጠቀሙ የነበረበት መንገድ ድንቅ ነበር። ታድያ በዚሁ አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ሁለት ለአንድ እየመሩ ወደ መልበሻ ቤት ቢያመሩም በሁለተኛው አጋማሽ ግን ፍፁም የተለየ መልክ ነበራቸው።

ከላይ በጠቀስናቸው መንገዶች ተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫውን በመውሰድ በመጀመሪያ አጋማሽ መንቀሳቀስ የቻሉት ሁለቱ ቡድኖች በሁለተኛው አጋማሽ እነዚህን ሂደቶች ከማስቀጠል ይልቅ ከጅምሩ ጥንቃቄን መርጠው በኋላ ላይ ደግሞ ይበልጡኑ አፈግፍገው መጫወታቸውን ተከትሎ ከተጋጣሚያቸው ጫናን በመጋበዝ በስተመጨረሻም ውጤቱን አሳልፈው ለመስጠት ተገደዋል።

👉 ጅማ አባ ጅፋር በስተመጨረሻም ሦስት ነጥብ አሳክቷል

10ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጅማ አባ ጅፋሮች አዲስአበባ ከተማን በዳዊት እስጢፋኖስ የቆመ ኳስ ግብ በማሸነፍ የውድድር ዘመናቸውን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ከ810 የጨዋታ ደቂቃዎች በኋላ አሳክተዋል።

ቡድኑ በጨዋታ እንቅስቃሴ በተለይ ተጋጣሚዎቹን በኳስ ቁጥጥር በመገዳደር ረገድ የመሻሻል ፍንጮችን እያሳየ ቢቆይም ይህን ተስፋ በግቦች አለፍ ሲልም በውጤት ለማጀብ ግን አስር የጨዋታ ሳምንት ለመጠበቅ ተገዷል።

በሀዋሳ ከተማ 1-0 ተሸንፈው የውድድር ዘመኑን የጀመሩት ጅማዎች በመጀመሪያዎቹ ስድስት ጨዋታዎች በሙሉ ሲሸነፉ በሰባተኛ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ያለ ግብ የተለያዩበት ጨዋታ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ አንድ ነጥብ ሲያስገኝላቸው በቀጣይ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች እንዲሁ በጠባብ ውጤት መሸነፋቸው አይዘነጋም።

እስካሁን አስራ አምስት ግቦች ለተቆጠረበት ቡድን የዳዊት እስጢፋኖስ የቅጣት ምት ግቡ በውድድር ዘመኑ ያስቆጠራት ሦስተኛ ግብ ሆና ተመዝግባለች። ከዚህ ቀደም ኢዳላሚን ናስር እና ዳዊት ፍቃዱ የቀደሙትን ግቦች ማስቆጠራቸው አይዘነጋም።

ድሉን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ አራት ያሳደጉት ጅማዎች ከላያቸው ከሚገኘው ሰበታ ከተማ ጋር ያላቸውን ልዩነት ወደ ሦስት ማጥበብ ሲችሉ እስከ 12ኛ ደረጃ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ደግሞ ያላቸው ልዩነት የሰባት ነጥቦች ሆኗል። ይህም አሁን ባለው ሁኔታ ጅማዎች ይህን የመጀመሪያ ድል የውድድር ዘመናቸውን መልክ እንደቀየረ አጋጣሚ የሚጠቀሙበት ከሆነ ቆይታቸው ሊሳካ የሚችል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህን የማሸነፍ ስሜት ለማስቀጠል ጠንክረው መስራት ይኖርባቸዋል።

👉 አሁንም የተመራው አዳማ ከተማ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኋላ ተነስቶ አሸንፏል

በአስረኛ የጨዋታ ሳምንት ሰበታ ከተማን የገጠሙት አዳማ ከተማዎች በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረባቸው ግብ ሲመሩ ቢቆዩም በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን ሦስተኛ ድላቸውን ማሳካት ችለዋል።

በ15 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ በአጠቃላይ በውድድር ዘመኑ የአስር ሳምንታት ጉዞ ውስጥ ብዙ አቻ (6ጊዜ) ተለያይቷል። ከዚህ ውስጥ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለግብ ከተለያየባቸው ጨዋታዎች ውጪ በተቀሩት አራት ጨዋታዎች አንድ አቻ በሆነ ውጤት ሲጨርስ ከመመራት ተነስተቶ (ከአንዱ ውጪ) በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ባስቆጠሯቸው ግቦች ነበር።

ታድያ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት 1-0 እየተመሩ ከዕረፍት የተመለሱት አዳማዎች በ51ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ከፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም በ79ኛው ደቂቃ አብዲሳ ጀማል ባስቆጠሯቸው ግቦች በውድድር ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመመራት ተነስተው ማሸነፍ ችለዋል።

መመራትን ወደ አቻ መቀየር የለመደው ቡድኑ በዚህ ሳምንት ተሳክቶለት እስከማሸነፍ ቢዘልቅም በቀጣይ ግን ጨዋታዎችን የሚጀምርበት መንገድ ላይ የማሻሻያ ሥራዎችን መስራት የግድ ይለዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ውድድሩ በቀጣይ ይበልጥ የፉክክር ደረጃው እየጨመረ ከመሄዱ ጋር በተያያዘ ቡድኖች አስቀድመው ያስቆጠሯትን ግብ በየተኛውም መንገድ ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥተው የመጫወታቸው ነገር የሚቀር ባለመሆኑ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ በዚህ ነጥብ ላይ ይበልጥ መስራት ይጠበቅባቸዋል።