​ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ሌሎች ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች የመጨረሻው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉ሊጉ ከዕረፍት ተመልሷል

የ2014 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከተካሄዱ በኋላ ሀገራችን ተካፋይ በነበረችበት የአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት ለ35 ያክል ቀናት ተቋርጦ በሳምንቱ መጨረሻ ዳግም ጅማሮውን አድርጓል።                                                          

የማስተናገድ ኃላፊነቱንም ከሀዋሳ ከተማ የተረከበችው ድሬዳዋ ከተማ ለቀጣዮቹ አምስት የጨዋታ ሳምንታት ሊጉን የምታስተናግድ ይሆናል።

መለስተኛ የቅድመ ውድድር ጊዜ ያልተናነሰ የዕረፍት ጊዜን አሳልፎ የተመለሰው ሊጉ ዳግም ሲጀመር በጨዋታ ፍጥነታቸው የተሻሉ በሁለቱም አቅጣጫዎች ወደሚገኙ ሳጥኖች በተደጋጋሚ የሚደርስ ነቃ ያሉ ጨዋታዎችን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በስፋት ተመልክተናል።

👉የድሬዳዋ ስታዲየም ጉዳይ 

የ2014 የውድድር ዘመን ሁለተኛ ምዕራፍ የሊግ የውድድር አስቀድሞ በአዳማ ከተማ ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም የአዳማን ወቅታዊ የማስተናገድ ቁመናን የገመገመው የሊጉ አክሲዮን ማህበር ዝግጁቱ በቂ ሆኖ አለማግኘቱን ተከትሎ የአስተናጋጅነት ድርሻው ለድሬዳዋ ተላልፎ ተሰጥቷል።

በቀጣይ በሚኖሩ ምዕራፎች የማስተናገድ ተራዋን እየተጠባበቀች የነበረችው ድሬዳዋም በተወሰነ መልኩ የተለጠጠ የነበረውን ዕቅዳቸውን በመከለስ አቅም በፈቀደ መልኩ የቅድመ ዝግጅት ስራቸውን በፍጥነት በማጠናቀቅ ውድድሩን በብቃት እያስተናገዱ ይገኛል።

በተለይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሊጉ በድሬዳዋ በነበረው ቆይታ ወቅቱ የዝናብ ወቅት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ከመጠነኛ ዝናብ መጣል በኋላ “ረግረጋማ” ይሆን የነበረው የመጫወቻ ሜዳ ለማሻሻል ያደረጉት ጥረት በጣም የሚደነቅ ነው። የሜዳውን የውሃ ማስወገጃ ስርአትን ለማሻሻል ከተደረጉ ጥረቶች ባልተናነሰ የመጫወቻ ሳሩን ይበልጥ ጠቅጠቅ ብሎ እንዲበቅል እና አረጓዴያማ ይዘት ለማላበስ የሚደነቁ ተግባራት ተከውነዋል።

በዚህም ጥሩ የሚባል ውጤት ማግኘት የተቻለ ሲሆን ሊጉ አስቀድሞ በተደመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ወደ ድሬዳዋ አምርቶ ቢሆን ኖሮ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ውጤት በተገኘ ነበር። በተጨማሪነትም አምና በግንባታ ሂደት ላይ የነበረው የክቡር ትሪቡን ግንባታ ተጠናቆ ወንበር የለበሰ ሲሆን በተጨማሪነትም ለዚህኛው ውድድር ሳይደርስ ቀረ እንጂ በስታዲየሙ ሁለት ግዙፍ ስክሪኖችን ለመግጠምም የሚያስችሉ ግንባታዎች ተከናውነውለታል።

በድንገት የማስተናገድ ዕድሉን እንዳኘች ከተማ ግን የድሬዳዋ ከተማ መስተንግዶ በጣም በመልካሙ የሚነሳ ነው።

👉የሁለተኛ አጋማሾች ጉዳይ

በ10ኛ የጨዋታ ሳምንት የተደረጉት አብዛኛዎቹ ጨዋታዎች ውጤት የተወሰነው በሁለተኛ አጋማሽ በነበሩ ሁነቶች ነበር።

በጨዋታ ሳምንቱ ከተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ ሰባቱ በመሸናነፍ የተጠናቀቁ ሲሆን ፤ ከእነዚህ ውስጥ በአምስቱ ጨዋታች አሸናፊው ቡድን የማሸነፊያ ግቦች የተገኙት በሁለተኛው አጋማሽ ነበር።

በጨዋታ ሳምንቱ ብቸኛ በአቻ ውጤት በተጠናቀቀው እና ወልቂጤ ከመመራት ተነስተቶ በሁለተኛው አጋማሽ አቻ የተለያየበትን ጨዋታ ጨምረን ከተመለከትን በጨዋታ ሳምንቱ ከነበሩት ስምንት ጨዋታዎች ስድስቱ ውጤታቸው የተወሰነው በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ነበር።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ምክንያቶችን በግልፅ ለማስቀመጥ ጨዋታዎችን በደንብ ማጥናት ቢፈልግም የጨዋታ ማኔጅመንት ፣ የተጫዋቾች የአካል ብቃት ደረጃ ፣ በመከላከል ረገድ ያሉ ውስንነቶች ፣ የትኩረት ማነስ የመሳሰሉ ጉዳዮች የራሳቸው ሚና እንዳላቸው በጨዋታዎቹ መታዘብ ችለናል።