ዋልያዎቹ ነገ ይገመገማሉ

ከካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ በጊዜ ተሰናብተው ወደ ኢትየጵያ የተመለሱት ዋልያዎቹ ነገ ለግምገማ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።

በካሜሩን አዘጋጅነት በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሀ ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዶ በአንዱ አቻ በመውጣት ከምድቡ የማለፍ እቅዱን ሳያሳካ በጊዜ መመለሱ ይታወሳል። በካሜሩን የነበረውን አጠቃላይ ቆይታ አስመልክቶ ባሳለፍነው ሳምንት የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ቢጠበቅም በአንዳንድ ምክንያቶች ሪፖርቱ ሳይደመጥ ለሌላ ጊዜ መሻገሩ ይታወቃል። አሁን ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ ነገ ከጠዋቱ ከአራት ሰዓት ጀምሮ ወሎ ሰፈር በሚገኘው በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ሊደረግ ቀጠሮ መያዙን ሰምተናል።

ነገ በሚኖረው ግምገማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና የአሰልጣኝ ቡድን አባለት የአፍሪካ ዋንጫ ቆይታቸው ምን ይመሰል እንደነበረ ሪፖርት የሚያቀርቡ ሲሆን በቀረበው ሪፖርት ዙርያ ውይይት ለማድረግ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ጨምሮ የስራ አስፈፃሚ አባለት የሚገኙ ይሆናል። በነገው ዕለት ከሚካሄደው ግምገማ በኋላ የተነሱ ዋና ዋና ነጥቦች ነገ በሚኖረን ዘገባ የምንመለስበት ይሆናል።