ፕሪምየር ሊግ | ዐበይት ጉዳዮች

የአምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቀናት በፊት በተካሄዱ ጨዋታዎች መቋጫውን አግኝቷል። እስካሁን ድረስ በተካሄዱት ጨዋታዎች
ሊነሱ ይገባቸዋል ያልናቸውን ትኩረት የሳቡ ዐበይት ጉዳዮች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።

አልቀመስ ያለው የኃይቆቹ ግድግዳ

ሀዋሳ ከተማዎች በመጀመርያው ጨዋታ ሦስት ግቦች አስተናግደው ሊጉን ከጀመሩ በኋላ በቡድኑ የተከላካይ ክፍል ላይ ያልተጠራጠረ አልነበረም። በቻርለስ ሉክዋጎ፣ በረከት ሳሙኤል፣ መድሀኔ ብርሀኔ፣ አቤኔዘር ኦቴ እና ሚልዮን ሰለሞን የተዋቀረው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ለ360 ደቂቃዎች መረባቸውን ሳያስደፍሩ ከወጡ በኋላ ግን የተጠራጠሩት አፋቸውን ይዘዋል። የኃይቆቹ ጠንካራ ተከላካይ መስመር ከሻሸመኔ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድንና ሲዳማ ቡና በተከታታይ በገጠሙባቸው አራት ጨዋታዎች ምንም ግብ አላስተናገዱም፤ በሊጉ ዝቅተኛው የግብ መጠን(3) በማስተናገድም ቀዳሚ ናቸው።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የተጫዋቾች ሚና እየቀያየሩ እንደ ቡድን የሚከላከል ጠንካራ አደረጃጀት ያለው ቡድን ገንብተዋል። ይህንን ተከትሎ የአጥቂዎቹ ገመና በጉያው ሸሽጎ ለቡድኑ ውጤታማነት የጎላ ድርሻ እየተወጣ ካለው የተከላካይ ክፍል በተጨማሪ በመከላከሉ ላይ ቀላል የማይባል ድርሻ ያላቸው ሌሎች የቡድኑ ክፍሎችንም ማወደስ ግድ ይላል።

የፊት አጥቂዎች ከግብ መራቅ

እግርኳስ የቡድን ጨዋታ መሆኑ አያጠያይቅም። እንደ ቡድን የሚደረግ ድምር ጥረት ለውጤታማነት ትልቁ ድርሻ ቢወስድም ተጫዋቾች በግል የሚፈጥሩት ተፅዕኖም ቀላል የማይባል ለውጥ መፍጠሩ አይቀሬ ነው። በተለይም የፊት አጥቂዎች በግል ጥረታቸው የሚያበረክቱት አስተዋፆ ከምንም በላይ ተፈላጊና ለቡድኖች ውጤታማነት ቁልፍ ቦታ አለው። እስከ አራተኛ ሳምንቱ ላይ በዘለቀው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ የፊት አጥቂዎች አስተዋፆ ካየን ግን አናሳ ነው። በሊጉ የሚገኙ በርካታ አጥቂዎች በተከታታይነት ግቦች እያስቆጠሩ አይገኝም። እስካሁን በተካሄዱ አምስት ሳምንታት ጎልተው ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ የተጠቀሰው የአጥቂዎች ከግብ መራቅ አንዱ ቢሆንም በአንፃሩ በጥሩ ብቃት ቡድናቸው ተሸክመው የወጡ ሁለት አጥቂዎችም አሉ።

ከእነዚህ ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው አንዱ ነው። በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኘው አቤል ቡድኑ ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየበት ጨዋታ ውጪ በአራት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ችሏል።  ሁለተኛው የባህር ዳር ከተማው አጥቂ ሀብታሙ ታደሰ ነው። በአራተኛው ሳምንት ላይ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሀትሪክ የሰራው ይህ አጥቂ ቡድኑ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በሦስቱም ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በግብ ድርቅ የተመቱ ቡድኖች

አምስተኛ ሳምንት ላይ በደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአማካይ በጨዋታ 2.5 ግቦች ተቆጥረዋል። 14 ኳሶች ከመረብ ጋር ያዋሀዱት የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በርካታ ግቦች በማስቆጠር ሲመሩ ባህር ዳሮች በ9 ግቦች ይከተላሉ። በአንፃሩ ሀድያ ሆሳዕናና ወልቂጤ ከተማ በአምስት ጨዋታ ሁለት ግቦች ብቻ በማስቆጠር ዝቅተኛ የግብ መጠን ያስቆጠሩ ክለቦች ሆነዋል። ዋናው ትኩረት የሚስበው ጉዳይ ግን ቡድኖቹ በተከታታይነት ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ናቸው።

ሀድያ ሆሳዕናዎች በመጀመርያው ሳምንት መቻል ላይ ሁለት ግቦች ካስቆጠሩ በኋላ ባደረጓቸው አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች የባዶ ለባዶ ውጤቶች በማስመዝገብ መረቡ ባያስደፍርም ለ360 ደቂቃዎች ከግብ ጋር ተራርቋል። ሌላው በተከታታይ የግብ ድርቅ የሚገኘው ክለብ ወልቂጤ ከተማ ነው። ቡድኑ በሁለተኛው ሳምንት ሲዳማ ላይ አንድ ግብ አስቆጥሮ አቻ ከተለያየ በኋላ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖታል። ከተጠቀሱት ሁለቱ ክለቦች በተጨማሪ ሀምበሪቾ እና ሻሸመኔ ከተማ እስካሁን ድረስ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ያልቻሉ ቡድኖች ናቸው።