ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የመክፈቻ ቀን ውሎ

የ 2016 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ሲጀመር ሀዋሳ ከተማ ፣ አርባምንጭ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማን አሸናፊ ያደረጉ ውጤቶች ተመዝግበውበታል።

በቴዎድሮስ ታከለ

ሀዋሳ ከተማ 2-1 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የ2016 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ሁለቱን የሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆኑትን ሀዋሳ ከተማ እና የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን የሆነውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያገናኘው ጨዋታ ረፋድ ላይ ጅምሩን አድርጓል። ወይዘሪት ብዙአየሁ ጀምበሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ፣ የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ አባል ሊዲያ ታፈሰ እና አቶ አንበሴ አበበ የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ባስጀመሩት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እና የሚጣሉ ኳሶች በርክተው ባየንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጥቂት የግብ አጋጣሚዎችን ያስተዋልንበት ነበር። ሀዋሳዎች ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክፍል በመስመር በሚላኩ ኳሶች የንግድ ባንክን የግብ ክልል በእሙሽ ዳንኤል አማካኝነት ባደረጉት ሙከራ ቀዳሚ የሆነ ጥቃትን ሰንዝረዋል። ከቆሙ እና ለአጥቂዎች በሚጣሉ ተሻጋሪ ኳሶች ቀዳዳ ሲፈልጉ የታዩት ንግድ ባንኮች 18ኛው ደቂቃ ላይ ጠጠር ያላች ጠንካራ ሙከራን አድርገዋል። እመቤት አዲሱ ከግራ የሀዋሳ የግብ ክልል የተገኘን የቅጣት ምት ኳስ ወደ ውስጥ ስታሻማ ሰናይት ቦጋለ ወደ ጎል ስትመታው ግብ ጠባቂዋ ቤቴልሄም ዮሐንስ በጥሩ ቅልጥፍና አውጥታባታለች። ሀዋሳዎች በቀሩት ደቂቃዎች በረድኤት ንግድ ባንክ በአንፃሩ በሎዛ አበራ አማካኝነት የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረው ቢታይም አጋማሹ ግን ያለ ጎል ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል በይበልጥ የሰላ በድናቸው ይዘው ወደ ሜዳ የገቡት ሀዋሳዎች ኳስ እና መረብን 48ኛው ደቂቃ ላይ አገናኝተዋል። ከቀኝ ወደ ውስጥ እሙሽ ዳንኤል ብልጠቷን ተጠቅማ ያሻማችውን ኳስ ቱሪስት ለማ በግንባር ገጭታ ቡድኗን ወደ መሪነት አሸጋግራለች። የሀዋሳን የማጥቃት ሀይል ለመቆጣጠር የከበዳቸው የሚመስሉት ንግድ ባንኮች ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ሁለተኛ ጎልን ለማስተናገድ ተገደዋል። ከመሐል ሜዳ በረጅሙ የደረሳትን ኳስ እሙሽ ዳንኤል የብርቄ አማረን ስህተት ተጠቅማ ወደ ሳጥኑ ሁለቴ ብቻ ገፋ በማድረግ ታሪኳ በርገና መረብ ላይ በማሳረፍ የቡድኗን የጎል መጠን አሳድጋለች። ንግድ ባንኮች ሁለት ጎሎችን ካስተናገዱ በኋላ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ፣ ሰናይት ቦጋለ ፣ አረጋሽ ካልሳ እና ሴናፍ ዋቁማን በማስወጣት ንቦኝ የን ፣ መሳይ ተመስገን ፣ አሪያት ኦዶንግ እና መዲና ዐወልን ለውጠው በማስገባት ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት በብርቱ ታትረዋል። መሐል ሜዳ ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ ወደ ራሳቸው በማድረግ የሀዋሳን የጥንቃቄ አጨዋወት በመረዳት የተንቀሳቀሱት ንግድ ባንኮች 72ኛ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሎዛ አበራ ስታሻማ የሀዋሳ ተከላካዮች በአግባቡ ከግብ ክልላቸው ማራቅ ያልቻሉትን ኳስ ተጠቅማ አሪያት ኦዶንግ ጎል አስቆጥራ ባንክን ወደ ጨዋታ ብትመልስም በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎሎችን ሳንመለከት ጨዋታው በሀዋሳ የ2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ልደታ ክ/ከተማ 0-1 አርባምንጭ ከተማ

የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ በነበረው ጨዋታ ልደታ ክፍለ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማን አገናኝቷል። እምብዛም የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን መመልከት ባልቻልንበት እና ወጥ ያልሆኑ ቅብብሎች በርክተው ባስተዋልንበት ጨዋታ በሙሉ የጨዋታ ደቂቃው የተፈጠረው ሁለት ሙከራዎች ነበሩ። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ 16ኛው ደቂቃ ላይ ከመሐል ሜዳ ወደ ግራ መስመር የደረሳትን ኳስ አጥቂዋ ሰርካለም ባሳ ጎል አድርጋው እንስት አዞዎችን መሪ ማድረግ ችላለች። 

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽም ቀጥሎ አሁንም ግልፅ የማግባት ዕድልን የተመለከትንበት መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሩ ላይ የልደታዋ አጥቂ ህዳት ካሱ ከግብ ጠባቂዋ ገነት ኤርሚያስ ጋር ተገናኝታ ግብ ጠባቂዋ ካዳነቻት ኳስ በኋላ ጨዋታው በአርባምንጭ 1ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

አዲስአበባ ከተማ 1-0 ሲዳማ ቡና

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የመዲናይቱን ክለብ አዲስ አበባ ከተማን አሸናፊ ያደረገበት ውጤት ተመዝግቦ ተቋጭቷል። በአመዛኙ መሐል ሜዳ ላይ አዘውትሮ በሚደረግ ቅብብል የታጀበው የአዲስ አበባ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ከሙከራዎች ይልቅ በብዛት በሚንሸራሸሩ ኳሶች የታጀበ ነበር። በተለይ በመጀመሪያ የጨዋታ አጋማሽ አንድም ለግብ የቀረበ ዕድል ማየት አልቻልንም።

ከዕረፍት መልስ የተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ በተሻለ ተነሳሽነት ለመጫወት የጣሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ያገኟትን አንድ የግብ አጋጣሚ ወደ ጎልነት በመለወጥ አሸናፊ ሆነዋል። 81ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ ከገባች በኋላ ለቡድኑ መሻሻል ጥሩ አስተዋጽኦ ያደረገችው ዮርዳኖስ ምዑዝ አመቻችታ የሰጠቻትን ኳስ እየሩስ ወንድሙ ጥሩ ቦታ አያያዝ ላይ ለምትገኘው ቤቴልሄም መንተሎ አቀብላት ተጫዋቿም ወደ ጎልነት ለውጣው ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተፈፅሟል።