ሪፖርት| የጦና ንቦቹና ብርቱካናማዎቹ አቻ ተለያይተዋል

ድሬዳዋ ከተማዎች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ነጥብ ሲያገኙ ወላይታ ድቻዎች ተከታታይ የአቻ ውጤት አስመዝግበዋል።

ብርቱካናማዎቹ በአዳማ ከተማ ሽንፈት ካስተናገደ ስብስብ ኤፍሬም አሻሞ በዳዊት እስጢፋኖስ ተክተው ሲገቡ የጦና ንቦቹ በበኩላቸው ከመጨረሻው ጨዋታ ቋሚ አሰላለፋቸው ዘላለም አባተ በ ዮናታን ኤልያስ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ሁለቱም ቡድኖች የመሀል ሜዳ ብልጫ ለመውሰድ በሚያደርጉት ብርቱ ጥረት የጀመረው ይህ ጨዋታ በሙከራዎች የታጀበ ነበር። በአጋማሹ ከቆመ ኳስ ባደረጉት ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት የጦና ንቦች ዕድሎች በመፍጠርም ሆነ ሙከራዎች በማድረግ የተሻሉ ነበሩ። ቡድኑ በተለይም የተጋጣሚ ተከላካዮች ከኋላ የሚተውት ክፍተት ለመጠቀም ጥረት ሲያደርግ በነበረው ቢንያም ፍቅሩ ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርጓል። በተለይም አጥቂው በረዥሙ የተሻገረለትን ኳስ ገፍቶ የመታትና መረቡን ታካ የወጣች ኳስ ለግብ የቀረበች ነበረች። ፈጣኑ አጥቂ በሀያ አራተኛው ደቂቃ በተደጋጋሚ ያደረገው የግብ ማግባት ጥረት ሰምሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ተጫዋቹ አበባየሁ ሀጂሶ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው።

የጦና ንቦቹ ከግቡ በኋላም በፀጋዬ ብርሀኑ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ተጫዋቹ ከሳጥኑ ቀኝ ጠርዝ የተሻገረለት ኳስ በጥሩ መንገድ አብርዶ ቢመታም የግቡ ቋሚ መልሶበታል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ ተነቃቅተው የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ብልጫ ቢወስዱም ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ቻርለስ ከያሬድ የተቀበለው ኳስ መቶት ግብ ጠባቂው እንደምንም ቢያወጣውም በግቡ ቅርብ ርቀት የነበረው ኤልያስ የተመለሰው ኳስ መቶ ለጥቂት ወጥቶበታል።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ በሙከራዎች ታጅቦ በቀጠለው ሁለተኛ አጋማሽ ሁለት ቅያሪዎች አድርገው አጋማሹን የጀመሩት ብርቱካናማዎቹ ተሻሽለው የቀረቡበት ነበር።

ቡድኑ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻሉና ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርጓል፤ በተለይም አሰጋሀኝ ከቅጣት ምት አሻግሯት ዘርአይ በግንባሩ ገጭቶ አግዳሚውን ለትማ የወጣችው ኳስ ቡድኑን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች። በስልሳ አንደኛው ደቂቃ ግን የብርቱካናማዎቹ የቆመ ኳስ ሙከራ ፍሬ አፍርቶ ቡድኑ አቻ የሚሆንበት ግብ አስቆጥሯል።
ተቀይሮ የገባው ተመስገን ደረስ፤ አሰጋሀኝ ያሻገረው ኳስ በግንባር ገጭቶ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ ወደ ሳጥን በሚሻገሩ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች በቢንያምና አብነት ኳሶች ጨዋታውን ለመምራት ተቃርበው ነበር። በተለይም አብነት ከመአዘን የተሻገረው ኳስ በግንባሩ ገጭቷት ዓብዱለጢፍ መሐመድ ከመስመር የመለሳት ኳስ እጅግ ለግብ የቀረበች ነበረች። የጦና ንቦቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጭነት በመጫወት በመጨረሻ ሰዓት ጨዋታውን አሸንፈው የሚወጡበት ዕድል አባክነዋል። ብስራት በቀለ ዮናታን ከርቀት መቷት ግብ ጠባዊው የመለሳት ኳስ አግኝቶ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው አብነት ብያቀብለውም አማካዩ ወርቃማውን ዕድል ሊጠቀምበት አልቻለም።

ቅድምያ ሀሳባቸውን የሰጡት አሰልጣኝ አስራት አባተ ለጨዋታው ትልቅ ትኩረት ሰጥተውት እንደነበር ገልፀው በሁለተኛ አጋማሽ ያደረጓቸው ለውጦች ብያንስ አንድ ነጥብ ይዘው እንዲወጡ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ሁሉም ቡድን በውድድር ላይ እስካለ ጫና አይቀሪ ነው ካሉ በኋላ የተለየ ጫና ውስጥ እንደሌሉ ገልፀዋል። ድክመቶታቸው ላይ በመስራት ላይ እንዳሉ በመግለፅም ቡድናቸው በቀጣይ እንደሚሻሻል ገልፀዋል። ቀጥለው ሀሳባቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹም ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ገልፀው በሰሯቸው ጥቃቅን ስህተቶች ውጤቱን እንዳጡ ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ከዚ በላይ በርካታ ግቦች ማስቆጠር ይገባቸው እንደነበር ገልፀው እንደፈጠሩት ዕድል ግብ እንዳላስቆጠሩ ገልፀዋል።