ሪፖርት | ዐፄዎቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

በምሽቱ መርሐግብር ፋሲል ከነማ በግንባር ተገጭተው በተቆጠሩ ሦስት ግቦች ሀምበሪቾን 3ለ0 መርታት ችሏል።

በምሽቱ መርሐግብር ሀምበሪቾ እና ፋሲል ከነማ ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች ከአንድ ወር በፊት የአምስተኛ ሣምንት ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ሀምበሪቾዎች በመቻል 1-0 ከተረቱበት ስብስብ ማናዬ ፋንቱን እና በረከት ወንድሙን አሳርፈው ብሩክ ቃልቦሬን እና የኋላሸት ፍቃዱን ሲያስገቡ ዐፄዎቹ በበኩላቸው ከባህርዳር ከተማ ጋር ያለ ግብ ከተለያየው ስብስባቸው ውስጥ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካተው የነበሩትን ሱራፌል ዳኛቸው እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን አሳርፈው በምትካቸው ኤልያስ ማሞ እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን አስገብተው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ምሽት 12፡00 ሲል በተጀመረው ጨዋታ 5ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያው ትኩረት ሳቢ አጋጣሚ ተፈጥሯል። ቃልኪዳን ዘላለም ከጌታነህ ከበደ በተሰነጠቀለት ኳስ ወደ ሳጥን ሲገባ በሀምበሪቾው የመሃል ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ ጥፋት ተሠርቶበታል። ዋና ዳኛው ኤፍሬም ደበሌም የፍጹም ቅጣት ምት ይሰጣሉ። በዚህ ቅፅበትም ሁለተኛው ረዳት ዳኛ ሙሉነህ በዳዳ ጥፋቱ የተሠራ ከሳጥን ውጪ መሆኑን በመናገር ለመሃል ተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለ የቀይ ካርድ እንዲሰጥ ይጠቁማሉ በዚህም ዋና ዳኛው ኤፍሬም ደበሌ የመጀመሪያ ውሳኔያቸውን በመቀልበስ የመሃል ተከላካዩን በቀይ ካርድ አስወጥተው የቅጣት ምት ሰጥተዋል። የተሰጠውን የቅጣት ምትም ጌታነህ ከበደ ሲመታ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ በግሩም ቅልጥፍና አወጥቶበታል።

የተጫዋች ቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው በአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ የሚመሩት ሀምበሪቾዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ይበልጥ ተጠግተው ለመጫወት ሲሞክሩ ፋሲል ከነማዎች በአንጻሩ በኳስ ቁጥጥሩ ሙሉ ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መግባት ሲችሉ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ግን እስከ 34ኛው ደቂቃ መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ኤልያስ ማሞ ከመሃል ያሻገረለትን ኳስ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ኳሱን ያገኘው ጌታነህ ከበደ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ጨዋታው 43ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ዐፄዎቹ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሽመክት ጉግሣ ከመሃል ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በግንባሩ ገጭቶት የግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ መዘናጋት ተጨምሮበት መረቡ ላይ አርፏል። ከዕረፍት መልስ ሱራፌል ዳኛቸውን ቀይረው ያስገቡት ፋሲሎች ያደረጉት ቅያሪ ውጤታማ ለመሆን ሦስት ደቂቃዎች ብቻ ፈጅቷል። በዚህም 48ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ጌታነህ ከበደ በግሩም አጨራረስ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በቀሪ ደቂቃዎችም ፋሲሎች በተሻለ የራስ መተማመን ወደ ጎን በሚደረጉ ቅብብሎች ጨዋታውን ለማረጋጋት ሲሞክሩ ሀምበሪቾዎቾ በአንጻሩ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ፊት ተጭነው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን ፋሲል ከነማ 72ኛው ደቂቃ ላይ ሦስተኛ ግብ አስቆጥሯል። ሽመክት ጉግሣ በቀኝ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት ወደኋላ መልሶ ሲያቀብል ዓለምብርሃን ይግዛው ወደ ውስጥ አሻምቶት ያንን ኳስም ጌታነህ ከበደ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ በግንባሩ በመግጨት ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ምኞት ደበበም በግንባር በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ይህ ግብም በጨዋታው በግንባር ተገጭቶ የተቆጠረ ሦስተኛ ግብ ሆኗል። በአራት ደቂቃዎች ልዩነትም የሀምበሪቾው የመስመር ተከላካይ አብዱልሰላም የሱፍ ለማራቅ በሚመስል መልኩ ከረጅም ርቀት የመታው ኳስ ፈታኝ ቢሆንበትም ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ አስወጥቶታል። ከዚህ ሙከራ በኋላም ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው በፋሲል ከነማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀምበሪቾው አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ አስበው የመጡት እንቅስቃሴ ሌላ እንደነበር በመጥቀስ ቀይ ካርዱ ተጫዋቾችን እንደረበሻቸው እና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መሆኑ ደግሞ ተጫዋቾች ላይ የስነልቦና ጫና እንደፈጠረ በመግለጽ የሚፈልጉትን እንቅስቃሴ እንዳላዩም ጠቁመዋል። የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው ሀምበሪቾ ሊፈትናቸው እንደሚችል ገምተው መግባታቸውን በመናገር የመጀመሪያ ግባቸውን እስኪያገኙ የተጋጣሚ ቡድን ፈትኗቸው እንደነበር ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ግን ጨዋታውን ተቆጣጥረው እንደተጫወቱ ገልጸዋል።