ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ12ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች የታዘብናቸው ትኩረት የሳቡ ክለቦችን የተመለከቱ ጉዳዮች የመጀመሪያ ፅሁፋችን ክፍል ናቸው።

👉 ሊጉን መምራት የሚገባው ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከጨዋታ ጨዋታ ይበልጥ እየተሻሻለ የሚገኘው በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማን በአሳማኝ ሁኔታ 4-0 በመርታት የፋሲል ከነማን ነጥብ ተከትሎ በ26 ነጥቦች ከተከታይ ቡድኖች በአራት ነጥብ ርቆ ሊጉን መምራት ጀምሯል።

የቡድኖች ጥንካሬ መለኪያ ከሆነው የነጥብ ብዛት ባለፈ አሁን ላይ ቡድኑ የሊጉ ምርጥ መከላከል ሆነ ማጥቃት ባለቤት ሆኗል። በ12 ሳምንታት የሊጉ ጉዞ አራት ግቦችን ብቻ ያስተናገደው ቡድኑ በአስገራሚ መልኩ በስምንት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ መውጣትም ችሏል።

በተቃራኒው 20 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ፋሲል ከነማ በአንድ ግብ ልቆ ምርጡ የሊጉ ማጥቃት ባለቤት ሲሆን እስማኤል ኦሮ-አጎሮ በስምንት ግቦች የቡድኑ ከፍተኛ አስቆጣሪ፣ አቤል ያለው በሦስት እንዲሁም፣ ሦስት ተጫዋቾች ደግም በእኩል ሁለት ግቦች ይከተላሉ። ይህም የቡድኑን የአግቢዎች ስብጥርን በአግባቡ የሚያሳይ ነው።

ውድድሩ እኩሌታው ላይ ለመድረስ በተቃረበበት በዚህ ጊዜ ጥሩ የማሸነፍ ግስጋሴ ላይ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከ2009 በኃላ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት የተሻለ ቁመና ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም ይህን ወቅታዊ ብቃት አስቀጥለው ሊጉን ያነሳሉ ወይ የሚለው ጉዳይ በቀጣይ ይጠበቃል።

👉 በምቾት የሚከላከለው ወላይታ ድቻ

በ22 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ምናልባት በእስካሁኑ የ12 ሳምንት የሊጉ ጉዞ ከዕቅድ በላይ አፈፃፀም እያስመለከተን እንገኛለን። የጦና ንቦቹ ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ በነበረው የክረምቱ የዝውውር መስኮት እንደሌሎች ክለቦች በንቃት በገበያው አለመሳተፋቸው እንዲሁም በቅድመ ውድድር ጊዜ በቂ ጨዋታዎችን አለማድረጋቸው በጥቅሉ ቡድኑ ከያዙት ስብስብ አንፃር የስጋት ድምፆች በክለቡ ዙርያ እንዲነሱ ያስገደደ ነበር።

በሽንፈት የውድድር ዘመኑን የጀመረው ቡድኑ በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ድል ማድረጉን ተከትሎ በአምስተኛው የጨዋታ ሳምንት ሊጉን መምራት እስከመቻል ደርሶ የነበረ ቢሆኑም በቀጣይ አራት ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው የነጥብ ብዛት አንድ መሆኑን ተከትሎ ወደ ታች መንሸራተቱ አይዘነጋም።

የፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ቡድን ውድድሩ ወደ ድሬዳዋ ካመራ ወዲህ ከሦስት ጨዋታዎች ሦስቱንም በማሸነፍ ብዙዎችን በማስገረም ላይ ይገኛል። ከውጤቱ በስተጀርባ ደግሞ የቡድኑ የመከላከል ትጋት አድናቆት የሚቸረው ነው። በመጨረሻ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብን ብቻ ያስተናገደው ቡድኑ በጨዋታዎቹ የነበረው የመከላከል ጥንካሬ የሚያስደንቅ ነበር። ከጨዋታ መንገድ ይልቅ ለውጤት የሚጨነቀው ቡድኑ በተደራጀ መልኩ ጠቅጠቅ ብሎ በመከላከል እንዲሁም በተጋጣሚ ቡድን በኩል አደጋ ሊደቅኑ የሚችሉ ተጫዋቾች ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚረዱ ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ የተሳኩ ጊዜያትን እያሳለፈ ይገኛል። በተጨማሪም በሊጉ ከገባበት በላይ ካስቆጠሩ ሰባት ቡድኖች ተረታ የሚመደበው ቡድን የሚፈጥራቸውን እድሎችን ወደ ግብነት በመቀየር ረገድ መጥፎ የማይባል የማጥቃት አፈፃፀም ባለቤት ነው።

ምናልባት በተከታታይ ሽንፈት ባስተናገደባቸው ጨዋታዎች በጥራታቸው የላቁ ተጋጣሚዎች ሲገጥሙት በተወሰነ መልኩ ካልተቸገረ በቀር በሊጉ አማካይ የሚባሉ ቡድኖችን የአዕምሮ ጥንካሬ መፈተን እንደሚችል እያሳየ የሚገኘው ቡድኑ በዚህ መልኩ ምን ድረስ ይጓዛል የሚለው ይጠበቃል።

👉”አቻ ከተማ” አሁንም አቻ ወጥቷል

12ኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዳማ ከተማ እስካሁን በስምንት ጨዋታዎች አቻ በመለያየት ወደር አይገኝለትም። በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ በአንድ ጨዋታ ብቻ ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ቀጥሎ በሊጉ ሁለተኛ ዝቅተኛ ሽንፈት ያስተናገደው ቡድን ቢሆንም ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ ማሸነፉን ተከትሎ በሊጉ በ17 ነጥብ የሊጉ እኩሌታ ላይ ይገኛል።

በሊጉ በተመሳሳይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ (4) ቀጥሎ 7 ግቦች ብቻ በማስተናገድ በሊጉ ሁለተኛው ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ባለቤት የሆነው ቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴው ግን አመርቂ የሚባል አይደለም። ቡድኑ 9 ግቦችን ብቻ በማስቆር አነስተኛ ግብ ካስቆጠሩ የሊጉ አምስት ቡድኖች ተርታ ይመደባል።

ደካማ አጀማመርን በጨዋታዎች የሚያደርገው ቡድኑ ካስቆጠራቸው ዘጠኝ ግቦች ውስጥ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተቆጠረውን የአሜን ግብ ጨምሮ ሶስት ግቦችን ብቻ በመጀመሪያው አጋማሽ ማሽቆጠር የቻለ ሲሆን በአምስቱ ጨዋታዎች ከመመራት ተነስተው ውጤት ማስመዝገባቸው ስለደካማ አጀማመራቸው የሚነግረን ነገር ይኖራል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የወቅቱን የሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማን ሲገጥሙ ግን ጨዋታውን የጀመሩበት መንገድ ግን ብዙዎችን ያስገረመ ነበር። ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶም የሚገኙ ኳሶችን በፍጥነት ወደ ሦስተኛ የሜዳ ሲሶ እየወሰዱ ለአደጋ ምንጭነት ሲጠቀሙባቸው የታየ ሲሆን ፋሲሎችም በዚህ ተደናግጠው የመጀመሪያ ደቂቃዎችን ወደራሳቸው ሜዳ ተጠግተው ነበር ሲጫወቱ የነበረው። እስከ 22ኛው ደቂቃም ከቆመ ኳስ ውጪ በክፍት ጨዋታ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያደርጉ የአዳማን ጥቃት መመከቱ ላይ ተጠምደው ውለው ነበር።

ሦስት ፈጣን አጥቂዎችን አሰልፎ የነበረው ቡድኑም በዋናነት በትንሽ ቅብብሎች ጎል ጋር ለመድረስ ሲጥር የነበረበት መንገድ የሚያስደንቀው የነበረ ቢሆንም የስልነት ችግር ግን በቶሎ መሪ እንዳይሆን አድርጎታል። በጨዋታው ግማሽ ሰዓት ግን ይኸው ጥረት ፍሬ አፍርቶ አሜ መሐመድ ድንቅ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑ ቀዳሚ ሆናል። እርግጥ ከግቡ በኋላ ብዙም ድፍረት ያጣ የማይመስለው ቡድኑ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ባይንቀሳቀስም ለክፉ የሚዳርገው አጨዋወት አልተከተለም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን የቡድኑ ቁጥብ መሆን ለፋሲሎች የልብ ልብ ሰጥቶ በርካታ ጫናዎች ከየአቅጣጫው እንዲደርስበት አድርጓል። በዚህም በ74ኛው ደቂቃ ግብ አስተናግደው በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ አሳልፈው ሰጥተዋል። እንዳልነው ቡድኑ ጨዋታውን የጀመረበት መንገድ ድንቅ ቢሆንም በዛው ሪትም አለመጨረሱ ተጋጣሚን እያነሳ በመምጣት ጫናዎች እንዲበረክቱበት አድርጓል።

ደካማ የጨዋታ አጀማመር እንዲሁም የግብ እድሎችን በጥራት መፍጠር እና የተገኙትን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ስልነት የሚጎለው ቡድኑ አቻ ከተለያያቸው ጨዋታዎች ጥቂቶቹን እንኳን ወደ ድል መቀየር ቢችል ኖሮ ወደ ሰንጠረዡ አናት ይበልጥ የሚጠጉበትን ዕድል መፍጠር በቻሉ ነበር።

👉 መከላከል የሚልገው ነገርግን የማይከላከለው ሰበታ ከተማ

የዘንድሮው ሰበታ ከተማ ቀለል ባለ መንገድ ሲገለፅ መከላከል የሚፈልግ ነገርግን በቅጡ የማይከላከል፣ በተመሳሳይ ለማጥቃት ሲፈልግም እንዲሁ ማጥቃቱን በወጉ ለመከወን መጠነ ሰፊ ውስንነቶች ያሉበት ቡድን ስለመሆኑ እየታዘብን እንገኛለን።

በአሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚመራው ሰበታ ከተማ ክፉኛ የታመመ ቡድን እንደሆነ እያየን እንገኛለን። ከምንም በላይ ደግሞ በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ውስጥ ደካማ የሆነው ቡድኑ ጨዋታዎች ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮ መውጣት እንዴት እንደሆነ ፍፁም ጠፍቶታል። ለወትሮ በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ መሰረት በመጣል የሚታወቁት አሠልጣኝ ዘላለም በሰበታ ቤት የቀደመ ጠንካራ ጎናቸው የከዳቸው በሚመስል ሂደት ባልተለመደ ሁኔታ የተጋለጠ ቡድን እያስመለከቱን ይገኛል። እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች (18) በሊጉ ብዙ ግቦችን ያስተናገደ ክለብ የሆነው ቡድኑም በሀዲያ ሆሳዕና አንድ ለምንም ሲረታ ጎሉን በክፍት ጨዋታ ባያስተናግድም በመከላከል ወቅት የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዓለማየሁ ሙለታ በሰራው ጥፋት (ኳስ በእጅ በመንካቱ) ሦስት ነጥብ አስረክቧል።

እርግጥ ቡድኑ በጨዋታው የመከላከል አወቃቀሩን ወደ ኋላ 5 (Back 5) ቀይሮ በመግባት በመከላከል ወረዳ የቁጥር ብልጫ ለማግኘት በመሞከር የሀዲያን ጥቃት ለመቋቋም ያሰበ ቢመስልም በአጥጋቢ ሁኔታ ግቡን መከለል ግን ሳይችል ቀርቷል። አሠልጣኙም በድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸው “ፍፁም ቅጣት ምቱ ከተቆጠረብን በኋላ በተደጋጋሚ ግቦች ተቆጥረው ሽንፈት የሚመጣው ነገር ውስጣቸው (ተጫዋቾቹ) አለ። ይሄ ደግሞ ስሜትን በጣም ነው የሚበርዘው።” ማለታቸው ተጫዋቾቹ በቡድናዊ መዋቅር በሚከናወነው የመከላከል አደረጃጀት እንደማይተማመኑ እና ሌሎች ግቦችም ይቆጠርብናል የሚል ስሜት በውስጣቸው እንደሚኖር ያመላከተ ነው። ይህ የመከላከል ጥንካሬ እንዲሁ ዝም ብሎ የሚመጣ ስላልሆነ አሠልጣኙ ራሳቸው እንዳሉት በልምምድ ሜዳ ላይ በደንብ ሰርተው ሊያመጡት የሚችል ጉዳይ ነው። ካልሆነ ግን የግብ ፊት አያናፋርነታቸውን ቢያሻሽሉት እንኳን ግቦች እየተቆጠረባቸው ጨዋታዎች ከእጃቸው ሊወጣ ይችላል። በፍላጎት ደረጃም የመከላከል ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ማብዛት ብቻውን ለመከላከል ዋስትና እንደማይሰጥም ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች ትምህርት እንደሚሆናቸው ይታሰባል።

👉 በተስፋ እና ስጋቶች ውስጥ የሚገኘው አዲስአበባ ከተማ

ሊጉን በተከታታይ ሽንፈቶች የጀመሩት አዲስ አበባ ከተማዎች አራት ተከታታይ አዎንታዊ ውጤቶችን በማስመዝገብ የተነቃቁ ቢመስሉም በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ግን አንድ ነጥብ ብቻ አሳክተው ዳግም ወደ ወራጅ ቀጠናው ገበተዋል።

ከውጤት አንፃር እጅግ አስደንጋጭ ማሽቆልቆል ላይ የሚገኘው ቡድኑ በስድስተኛው ሳምንት መጨረሻ ከነበረበት 5ኛ ደረጃ በሳምንታት ልዩነት አሁን ላይ በመጨረሻ ደረጃ ከሚገኘው ሰበታ ከተማ በአራት ነጥብ ከፍ ብሎ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ብዙዎች ቡድኑ ካለው የስብስብ ጥልቀት ችግር እና አሰልጣኙም በትልቅ ደረጃ የማሰልጠን ልምድ አለመኖር ጋር በተያያዘ ውጤታማ በነበሩባቸውም ጊዜያት ጥርጣሬዎች በስፋት ሲንሸራሸሩ ቆይተዋል። የሰሞኑም ውጤት አልባ ጉዞ ብዙዎች ከአሰልጣኝ ለውጥ ጋር ተያይዞ በቡድኖች የምናየው አዎንታዊ መነቃቃት (New Manager Bounce) ውጤት በሚመስል መልኩ ቡድኑ ይህን መነቃቃት ለማስቀጠል ተቸግሯል።

ምንም እንኳን ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ጥቂት ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈቶችን ቢያስተናግዱም ጨዋታዎችን ከውጤት ባለፈ መመዘኛ ከተመለከተን ግን የቡድኑ እንቅስቃሴው ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም። ለአብነትም በተሸነፈባቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች (ከወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና) ጋር በነበሩት ጨዋታዎች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በማድረግ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር የመቻላቸው ነገር በበጎ ጎኑ የሚወሰድ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ቡና በተሸነፉበት ጨዋታም ቡድኑ በሙከራዎች ረገድ ከኢትዮጵያ ቡና እኩል አራት ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም በተጫዋቾቻቸው ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ በጨዋታው ነጥብ ለመጣል ተገደዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ሀሳባቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ ይህን ብለዋል ፤

“አብዛኛው ተጫዋች ማጥቃትም ላይ ያሉት ከተወሰኑት በስተቀር ልምድ ይጎላቸዋል። በጋራ ከመጫወት ይልቅ በግል የመጫወቱ ነገር ስላለ ይሄ ነገር በእጅጉ ጎድቶናል። አሁን ትልቅ እየጎዳን ያለው በፊት የእኛ ቡድን የሚታወቀው በጋራ በመጫወት እና በጋራ ውጤት በማስመዝገብ ነው ። አሁን ግን ይሄን ነገር ትንሽ እያጣነው ስለመጣን ሀሉም በየግል ነው የሚጫወተው። ይህ የልምድ ጉዳይ ነው። ትንሽ እሱ እየጎዳን ነው የመጣው።” ሲሉ ተደምጠዋል።

ሌላኛው ከቡድኑ ጋር የሚነሳው ጉዳይ የተጫዋቾች ምርጫ ጉዳይ ነው። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥም ጥንቃቄን መርጠው ለመጫወት አልፍ ሲልም በመልሶ ማጥቃት ኢትዮጵያ ቡና ላይ ጉዳት ለማድረስ ፍላጎት የነበረው ቡድኑ በተለይ በፊት መስመር ላይ ግን የነበራቸው የተጫዋቾች ምርጫ ይህን ሂደት የሚደግፍ አልነበረም።

ለወትሮው እንዳለ ከበደ ፣ ሪችሞንድ አዶንጎ እና ፍፁም ጥላሁን ይመራ የነበረው የአጥቂ መስመር በተለይ ለመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በብዙ መንገዶቾ የተመቸ ቢሆንም ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን በገጠመበት ጨዋታ እንዳለ ከበደን እና ሪችሞንድ አዶንጎን ሳይዝ በምትካቸው የሺዋስ በለው እና ቢኒያም ጌታቸውን በመጠቀም የመጀመሪያውን አጋማሽ አድርጓል። በዚህ ሂደትም ለተጋጣሚው ብዙ ነገሮችን የፈቀደ ቡድን ሆኖ የተመለከትነው ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ የሁለቱ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ መግባት ግን ቡድኑ በተለይ በመልሶ ማጥቃቱ ረገድ የተሻለ መልክን አላብሶታል።

በአስራ አንድ ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ በመጨረሻ ደረጃ ከሚገኘው ሰበታ ከተማ በአራት ነጥቦች ብቻ የሚርቁ ሲሆን የመጀመሪያ ዙር ከመጠናቀቁ በፊት በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ቀጥተኛ ተፎካካሪያቸው ከሆነው ሰበታ ከተማ እንዲሁም በቀጣይነት ደግሞ በመነቃቃት ላይ ከሚገኘው ሲዳማ ቡና እና ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች እጅግ ወሳኝ ናቸው።

👉 ፋሲል ከነማ አሁንም ነጥብ ጥሏል

አምና 54 ነጥቦችን በመሰብሰብ የሊጉ አሸናፊ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች ዘንድሮ ግን ይህን ክብራቸውን ለማስጠበቅ በእስካሁኑ ጉዟቸው የተወሰኑ መንገራገጮች እያጋጠሟቸው ይገኛል። ከአሸናፊነት ማግስት ያለው የውድድሮ ዘመን ለቡድኖች ፈታኝ ሰለመሆኑ ይታመናል የባለፉት ጥቂት አመታት በሊጉ የተመለከትነው ተሞክሮም ይህን በሚገባ ያሳያሉ።

አምና በተመሳሳይ ወቅት ሊጉን በ29 ነጥቦች በወቅቱ ተከታዩ ከነበረው ኢትዮጵያ ቡና በአምስት ነጥብ ልቆ ይመራ የነበረው ቡድኑ ዘንድሮ ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ በአራት ነጥቦች ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከአምና አንፃር ባሸነፋቸው የጨዋታ ብዛት ሆነ ባስቆጠራችው ግቦች ብዛት መቀነስን አሳይቶ በ22 ነጥቦች አሁን በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

አምና በሙሉ የውድድር ዘመኑ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ የተሸነፈው ቡድኑ ዘንድሮ እስካሁን ሁለት ጨዋታዎችን የተሸነፈ ሲሆን በዚህ የጨዋታ ሳምንትም አቻ መለያየቱን ተከትሎ እስካሁን አራት ጨዋታዎችን በድምሩ አቻ የወጣ ሲሆን ይህም አምና በአጠቃላይ የውድድር ዘመኑ አቻ ከተለያው የጨዋታ መጠን (6) በሁለት ያነሰ ሆኗል።

ከቁጥሮች ባለፈ ሜዳ ላይ እየተመለከትነው የምንገኘው የቡድኑ እንቅስቃሴ ቡድኑ በተወሰነ መልኩ አዳዲስ የጨዋታ ሀሳቦች እንዲሁም ቡድኑ አምና ውጤታማ ሲሆን ጎልህ ድርሻ የነበራቸው የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች አሁናዊ አቋም በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመገኘት ቡድኑን ፈተና ላይ የጣለው ሲሆን ቡድኑ በፍጥነት የእነዚህን ተጫዋቾች ብቃት የሚሻሻልበትን መንገድ ማበጀቸት የማይችል ከሆነ በፍጥነት ከዋንጫ ፉክክር እየራቀ እንዳይመጣ ያሰጋል።