ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የዐበይት ጉዳዮች አምዳችን ሦስተኛው የትኩረታችን ክፍል ደግሞ አሰልጣኞች ላይ ያተኮረ ነው።

👉 “ለሰበታ እዚህ ደረጃ መገኘት ተጠያቂው እኛው ነን”

በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አንድ ጨዋታ ብቻ የረታው ሰበታ ከተማ የቁልቁለት ጉዞውን ተያይዞታል። በክረምቱ የዝውውር መስኮት አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ሾሞ በርካታ ተጫዋቾችን ያዘዋወረው ክለቡም እስካሁን የቡድን ውህደቱን ያገኘ አይመስልም።

በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ተደራጅቶ የማይታይ ሲሆን በየጨዋታውም የተለያዩ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ ሲገቡ ይስተዋላል። ክለቡ ዘንድሮ ካስመዘገባቸው 30 ተጫዋቾችም እስካሁን ሜዳ ገብተው አንድም ደቂቃ ያልተጫወቱት አራተኛ የግብ ዘቡ ቶማስ ትዕግስቱ እና አጥቂው ሀብታሙ ጉልላት ብቻ ናቸው። ከ28ቱ ተጫዋቾች ደግሞ ከቦጃ ኢዲቻ እና አስቻለው ታደሰ ውጪ ሁሉም ከ45 ደቂቃ በላይ የመጫወት ዕድል አግኝተዋል። ታዲያ ይህ ቡድኑ ገና እየተሰራ እንደሚገኝ የሚጠቁም ሲሆን የመሰሪያ ጊዜው ደግሞ በውድድር ላይ መሆኑ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል።

አሠልጣኙም “አሁን ዋናው ነጥብ ወደ ሌላው ጣትህን የምትቀስርበት አይደለም። ችግሩ ያለው እኛ ጋር ነው፡፡ እኛ ነን ይሄን መለወጥ መስራት ያልቻልነው። ስለዚህ ይሄ እንደዚህ አድርጓል፤ ያ እንደዚህ አድርጓል ወደሚል መጠቋቆም አንሄድም። ነገር ግን እኛ በተደጋጋሚ ነጥብ አስቆጥሮ የመውጣት ሂደት ላይ ቅድም ባልኩት መንገድ የእድለኝነቱ ጉዳይ ላይ ምን አልባት ደግሞ እጅግ በጣም በጥቂቱ ተፅእኖ ፈጣሪ ተጫዋቾች በቡድኑ ማሟላት ባለመቻላችን ድክመት መስሎ ይታየኛል፡፡ ነገር ግን ለዚህም ድክመት ተጠያቂው እኛ ነን፤ ሌላው አደለም። እኛ ነን ያልሰራነው። ስለዚህ ወደ ሌላው የምንጠቋቆምበት አንዳች ነገር አይኖርም፡፡” በማለት የሰጡት ሀሳብ ሀላፊነቱ በራሳቸው ላይ እንዳለ አመላካች ነው።

👉 “ተገማች ነን…” ካሣዬ አራጌ

ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ዳግም ወደ በስልጠናው ኢትዮጵያ ቡና ከተረከበ ወዲህ ለኢትዮጵያ እግርኳስ አንዳች የተለየ ነገር ለማበርከት እየተጋ የሚገኘው አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ የሀገራችን የድህረ ጨዋታ ቃለመጠይቆችን አንድ ደረጃ ከፍ እንዲል እያደረገ ይገኛል። ትኩረቶች ሁሉ እግርኳሳዊ እና እግርኳሳዊ አስተያየቶች ላይ እንዲሆኑ በማድረግ የካሣዬ ሚና የጎላ ነው።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ አዲስ አበባ ከተማን ከተረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ቡድኑ ላይ በተደጋጋሚ ስለሚቀርብበት “ቡድኑ ተገማች ነው…?” ለሚለው ጥያቄ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።

“አንድ የራሱ የሆነ የአጨዋወት ዘይቤ ያለው ቡድን ተገማች ነው። ምንም ነገር ከሌለህ ነው ተገማች የማትሆነው ፤ መገመት ማለት ደግሞ መታወቅ አይደለም። የራስህ ነገር መኖሩ አስተዋፅዖው ያንተን ነገር መነሻ አድርገው ተጋጣሚዎች ሲመጡ በተዘዋዋሪ ደግሞ እነሱ እንዴት እንደሚመጡ ታውቃለህ ማለት ነው። እነሱ የሚመጡበትን ነገር ማረም ማስተካከል እሱ ተገቢ ነው። ግን ተገማች መሆን ደግሞ አንድ ቡድን አንድ ነገር እንዳለው ነው የሚያሳየው። እነባርሴሎና እና ማንቸስተር ሲቲ እኮ ተገማች ናቸው። ተገማች በሆኑበት ነገር ውስጥ ነው ብልጫውን የሚወስዱት። ስለዚህ ተገማች መሆኑ ይቀጥላል። ምንም ነገር ሳይኖረን ሲቀር ግን ተገማች አንሆንም።”

ካሣዬ የሰጠው ሀሳብ ብዙ ሊያነጋግር የሚችል ነው። ነገርግን መሰረታዊው ጥያቄ ”ተገማች በመሆን እና ባለመሆን መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው?” የሚለው ጉዳይ ነው።

በሊጉ ያሉ ክለቦች የራሳቸው የሆነ በዘመናት መካከል እንደ ቀኖና የሚከተሏቸው እግርኳሳዊ ሀሳቦች እንደሌላቸው እሙን ነው። ስለዚህ የአተገባበር ሁኔታ የሚፈጥረው ልዩነት እንዳለ ሆኖ የቡድኖቹ የጨዋታ መንገድ በሚሾሙት አሰልጣኞች ፍላጎት ጋር የተመሰረተ መሆኑ እሙን ነው።

በቀላሉ ለመረዳት በሊጉ ለአመታት በማሰልጠን የምናውቃቸው አሰልጣኞች አብዛኞቹ በገቡባቸው ክለቦች በመሰረታዊነት ለመተግበር የሚፈልጉት የጨዋታ መንገድ የሚታወቅ ነው። አሰልጣኞቹ መሰረታዊው የጨዋታ መፅሃፋቸውን በጉልህ የሚታዩ መሻሻሎችን ሳያደርጉ በቀጣይም ክለብ ተመሳሳይ ተጫዋቾች በመሰብሰብ የቀደመውን ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ሲጥሩ ይስተዋላል።

ስለዚህ በአንድ ሆነ በሌላ መንገድ ይህ ጥያቄ በተለየ ለኢትዮጵያ ቡና ብቻ የሚነሳ ሳይሆን የአብዛኞቹ ቡድኖች የጋራ ነገር ነው። በመሰረታዊነት የኢትዮጵያ ቡናን ለየት የሚያደርገው ምናልባት ባመኑበት እና ያዋጣናል ላሉት መንገድ ታምነው የመቀጠላቸው ነገርግን ካልሆነ በቀር በቀጥተኛ ኳስ ለመጫወት ሆነ ለመከላከል ቅድሚያ የሚሰጠው ቡድን በየራሳቸው መንገድ ተገማቾች ናቸው።

ሌላኛው ጉዳይ ካሳዬም በአስተያየቱ ያነሳው የራሱ የሆነ መገለጫ ያለው ቡድን በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ተጋጣሚዎች የሚጫወትበትን መንገድ ሊያውቁ ቢችሉም መሰረታዊውን ነገር ሳይለቁ መጠነኛ መለዋወጦችን በማድረግ ውጤታማ ለመሆን መሞከሩ ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ በአለም እግርኳስ ሃያላን ቡድኖች ሳይቀሩ ከጨዋታ ጨዋታ የማይለቋቸው መሰረታዊ የጨዋታ ሀሳብ ሲኖራቸው ተጋጣሚዎች በየሳምንቱ ከዚህ መነሻነት ይህን መንገድ ለማቆም ዝግጅት አድርገው ቢመጡም እነዚሁ ሃያላን ቡድኖች በአብዛኛው አጋጣሚ ከተጋጣሚያቸው ልቀው መውጣታቸው የተለመደ ነው። በዚህ ሂደት ተጋጣሚዎቻቸውን የቡድኖቹን የጨዋታ መንገድ ከግምት ውስጥ አስገብተው ስለማይዘጋጁ ሳይሆን ማድረግ የሚፈልጉትን ነገር በተለያየ መንገድ እና በላቀ ደረጃ መከወን መቻላቸው ነው። በመሆኑም ቡድኖች ከመሰረታዊው ነገራቸው ሳይወጡ የያዙት ሀሳብ በላቀ ደረጃ ስለመከወን እና ጥቃቅን የሚመስሉ ለውጦችን በማድረግ ሀሳባቸውን እንዴት ማስቀጠል ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

👉 አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ከድል ጋር ተመልሰዋል

ወደ ካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ካቀኑ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ የነበሩት እንስትራክተር አብርሀም መብራቱ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል። በካፍ የቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ ኃላፊነት የነበራቸው የባህር ዳር ከተማ ዋና አሰልጣኝ አህጉራዊ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ ሳሉ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መካሄዱን ቀጥሎ ነበር። በዚህም ምክንያት ቡድናቸው ከሲዳማ ቡና ፣ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች ለመምራት ሳይችሉ ቀርተዋል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ባህር ዳር ከተማ ሀዋሳ ከተማን ከገጠመበት ጨዋታ በፊት ወደ ስራቸው የተመለሱት አሰልጣኙ ከቡድናቸው ጋር የልምምድ ጊዜያትን በማሳለፍ ዳግም በጨዋታ ቀን የጣና ሞገዶቹን እየመሩ ወደ ሜዳ ብቅ ብለዋል። ባህር ዳር ከተማ ቀደም ብሎ በአዳማ ከተማ ካስተናገደው ሽንፈት በኋላ ዋና አሰልጣኙ ባልነበሩበት ሁለት ጨዋታዎችም ተሸታታይ ሽንፈቶች ደርሳውበት ነበር የጠበቃቸው። ከሽንፈቱ ባሻገር ቡድኑ በጨዋታዎቹ ላይ ይታይበት የነበረው የተነሳሽነት እና የስሜት ዝቅታ በቀጣይ ጨዋታዎች ላይም ውጤት እንዳያጣ የሚያስገው ነበር። ሆኖም በዚህ ሳምንት ከአሰልጣኙ መመለስ ጋር የተያያዘ በሚመስል መልኩ በጥሩ የቡድን መንፈስ እና ታክቲካዊ አፈፃፀም ባህር ዳር ጥሩ አቋም ላይ የነበረው ሀዋሳ ከተማን 2-0 መርታት ችሏል። በቀጣይ በሚኖሩ ጨዋታዎች ላይ በተመሳሳይ አኳኋን ይቀጥል ይሆን ? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ የሀዋሳው ጨዋትን የአሰልጣኙ መመለስ ለቡድኑ ማርሽ መቀየር መነሻ መሆኑን ፍንጭ ሰጥቶ አልፏል።

👉 የተጫዋቾች አደረደር ለውጦች

የተጫዋቾች አደራደር (ፎርሜሽኖች) በመሰረታዊነት የሜዳ ላይ ተጫዋቾች በአንፃራዊ የሜዳ ላይ የሚኖራቸውን መነሻ አቋቋም የሚያሳይ ጠቅለል ያለ መግለጫ ሲሆን በጨዋታ ላይ በመከላከሉ ሆነ በማጥቃቱ ተጫዋቾች የሚወጧቸው ሚናዎች አጠቃላይ የቡድኑን መልክ ይወስናሉ።

ቡድኖች በመሰረታዊነት የሚጠቁሙባቸው ተደጋጋሚ መነሻ ቅርፆች ሊኖሩ ይችላሉ ነገርግን እንደተጋጣሚ ሁኔታ ሆነ ማድረግ ለፈለጉት አንዳች አላማ መሳካት የቅርፅ ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ ፤ በእነዚህ ለውጦች ውስጥ ግን ከለውጡ ጋር ተጫዋቾች ሆነ የቡድኑ መዋቅር መስተካከል ካልቻለ ለውጡ በራሱ ይዞት የሚመጣው ተግዳሮት ሊኖር ይችላል።

ለአብነትም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማዎች ለወትሮው የሚጠቀሙበት የኃላ አራት ተከላካዮች ወደ ሶስት የመሀል ተከላካይ ቀይረው በገቡበት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ምንም እንኳን በ24ኛው ደቂቃ የዮናስ በርታ በቀይ ካርድ መወገድ የጨዋታው ሂደት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ቢያሳድርም ከቀይ ካርዱ በፊት የተመለከትናቸው ሂደቶች ግን የሚሰጠን ምስል አለ።

በ3-5-2 ለመጫወት ያሰቡት ወልቂጤ ከተማዎች በመስመር ተመላላሽነት ጫላ ተሺታን በቀኝ እንዲሁም ረመዳን የሱፍን በግራ በኩል ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል ፤ እርግጥ ከአደራደር ለውጦ በስተጀርባ የጊዮርጊስ ሶስት አጥቂዎችን በሶስት የመሀል ተከላካዮች እንዲሁም መሀል ሜዳ ላይ ከጊዮርጊሶች ሶስት ተጫዋቾች ጋር ለማለም የሚሉ አመክንዮዎችን ማስቀመጥ ቢቻልም ከቀደመው ቅርፅ ወደ ኃላ ሦስት በተደረገው ሽግሽግ ውስጥ ተጫዋቾች ሚናቸውን አስማምተው መቀጠል አለመቻላቸው ለወልቂጤዎች አደጋ ሲጋብዝባቸው አስተውለናል።

እርግጥ በየትኛውም የተጫዋቾች አደራደር ውስጥ ቢሆን ረመዳን የሱፍ ከፍ ያለ የማጥቃት ፍላጎት ያለው የመስመር ተከላካይ እንደሆነ ቢታመንም በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ግን በተለይ ረመዳን የተሰለፈበት የወልቂጤ የግራ መስመር በኩል ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተደጋጋሚ የማጥቃት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተመልክተናል።

ከኃላ አራት ይልቅ በኃላ ሶስት መጫወት ለመስመር ተመላላሾች ከመስመር ተከላካዮች በተሻለ ከፍ ባለ የመነሻ አቋቋም እንዲገኙ የሚፍቅድ ቢሆንም በመከላከል ወቅት ግን እነዚህ ተጫዋቾች በአግባቡ ሁኔታዎችን ተረድተው የቦታ አያያዛቸውን ማስተካከል ካልቻሉ በቡድናቸው ላይ አደጋ መጋበዛቸው አይቀሬ ነው።

በዚህ ሂደት ከቀይ ካርዱ በፊት እና በኃላ በነበሩት የጨዋታ ሂደቶች የረመዳን የቦታ አያያዝ ስህተቶች የጎሉ ነበሩ ፤ ከሶስቱ የመሀል ተከላካዮች በግራ እንዲሁም ከረመዳን ኃላ የነበሩት ክፍተቶች ወደ ግራ ባደላ መልኩ ማጥቃት ለፈለጉት ጊዮርጊሶች ምቹ የማጥቂያ ስፍራ ሲሆን ተመልክተነዋል።

የረመዳንን ለአብነት አነሳን እንጂ በሌሎች ስፍራዎችም መሰል ከአዲሱ አደራደር ጋር ራሳቸውን ማስተካከል የተቸገሩ ተጫዋችችን ስንመለከት ነበር ፤ ታድያ በመሰል የአደራደር ለውጦች ውስጥ አደራደሮቹ ከሚፈልጓቸው የተጫዋቾች ባህሪ ጋር የተጣጣሙ የተጫዋቾች ምርጫ ሆነ በልምምድ ወቅት በተሻለ መጠን ቅርፆቹ ላይ ያተኮሩ መሰረታዊ የጨዋታ ባህሪያትን በደንብ ተሰርተው ካልመጡ እንደ ወልቂጤ ከተማ ራስ ላይ አደጋ መጋበዣ መሆናቸው የሚቀር አይደለም።

👉 በአጭሩ የተቋጨው የጳውሎስ ጌታቸው ውጥን

የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በሦስት የተለያዩ ዋና አሰልጣኞች የጨረሱት ወልቂጤ ከተማዎች ዘንድሮ ደግሞ ከወዲሁ አሰልጣኛቸውን አግደው አዲስ አሰልጣኝ አምጥተዋል።

አሰልጣኙም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ለሶከር ኢትዮጵያ የስንብት የሚመስል ሀሳብ ሰጥተዋል። ” እንደተመለከታችሁት ነው። በቀይ የወጣ ተጫዋች ነበር። ሳምንቱን መሉ እኛ ጥሩ ላይ አልነበርንም። በላዬ ላይ ሰው መጥቷል እየተባለ ሲወራ ነበር። እንደውም ይሄ ነገር ጥሩ ነው ብዬ እገምታለሁ ፤ እንደዚህ አይደረግም። በዚህ አጋጣሚ ግን ለወልቂጤ ደጋፊ ፣ ለወልቂጤ ህዝብ ወደ ፕሪምየር ሊግ ስገባ ከጎኔ ለነበሩት ሁሉ ምስጋና አቀርባለሁ።” በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።

ከሰሞኑ ከክለቡ አመራሮች ጋር ስለመቃቃራቸው እና ቡድኑም ከሌሎች አሰልጣኞች ጋር ንግግር የመጀመሩ ነገር በስፋት ሲዘዋወር የቆየ መረጃ ሲሆን አሰልጣኙም ለክለቡ ሰዎች በንግግራቸው መጨረሻ ያቀረቡት ምስጋና የስንብት ይዘት ያለው መሆኑ ነገሮች ያበቃላቸው ስለመሆኑ ይነግረናል።

በሊጉ በሚሰጧቸው አስተያየት ትኩረትን ይስቡ የነበሩት አሰልጣኙ ኳስ ተቆጣጥሮ በማጥቃት ሊጉን እናሸንፋለን ያሉት ውጥን ሳይሰምር ከወልቂጤ ከተማ ጋር የነበራቸው እህል ውሃ በዚህ መልኩ የተቋጨ መስሏል።

በአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው አምሳል ለኳስ ቁጥጥር የተመቸ እንዲሆን ተደርጎ የተሰራው ቡድኑ ወጣቱን አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን በዋና አሰልጣኝነት ስለመሾሙ ተሰምቷል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አሰልጣኝ የነበረው ተመስገን በፕሪምየር ሊጉ በሚገኝ ክለብ በዋና አሰልጣኝነት የመሰራት ልምድ ባይኖረውም በተለያዩ ክለቦች በተለያየ ሀላፊነት ሲሰራ እንደቆይ ይታወቃል።

በእግርኳሳችን ወደፊት ገፍተው እየመጡ ከሚገኙ አሰልጣኞች አንዱ የሆነው አሰልጣኙ በዘመናዊ እግርኳስ ንድፈ ሀሳብ አረዳዱ ሆነ ከዚህ ቀደም በሰራባቸው ሀላፊነቶች ካስመለከቱን ተስፋ ሰጪ ነገር አንፃር በሊጉ የመጀመሪያቸው በሚሆነው የዋና አሰልጣኝነት ሚና ምን አይነት ቡድን ያስመለክቱናል የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ ሲሆን ለሊጉ ግን ሌላ ተጨማሪ ሀሳብ ያለው ወጣት አሰልጣኝን ያገኘበት ሹመት ይሆናል ብሎ መውሰድ ይቻላል።