ሪፖርት | ሠራተኞቹ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸውን ተቀዳጅተዋል

በምሽቱ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ በጋዲሳ መብራቴ ብቸኛ ግብ ሻሸመኔ ከተማን 1-0 በመርታት በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል።

በምሽቱ መርሐግብር በውድድር ዓመቱ ምንም ድል ያላሳኩት ሻሸመኔ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ሲገናኙ ሻሸመኔዎች በአምስተኛው ሣምንት ከሀዲያ ጋር ያለ ግብ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ማይክል ኔልሰን እና ሙሉቀን ታሪኩ በ ሀብታሙ ንጉሤ እና በኢዮብ ገብረማርያም ተተክተው ሲገቡ ወልቂጤዎች በአንጻሩ በተመሣሣይ ሣምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 ከተረቱበት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ዋሃብ አዳምስ ፣ መሐመድ ናስር ፣ አብርሃም ኃይሌ እና አሜ መሐመድ አርፈው በምትካቸው ተስፋዬ መላኩ ፣ መሳይ ጳውሎስ ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ስንታየሁ መንግሥቱ ገብተዋል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የነበራቸው ሻሸመኔዎች 2ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ሙሉቀን ታሪኩ ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ የመሃል ተከላካዩ ተስፋዬ መላኩ ተደርቦ አግዶበታል።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ እየወሰዱ የመጡት ሠራተኞቹ በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ከራሳቸው የግብ ክልል በፍጥነት በመውጣት እና የመከላከል አደራጃጀታቸውን ከጥቃት በመጠበቅ ወደፊት ተጭነው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ 27ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ጋዲሳ መብራቴ ከሳጥን አጠገብ ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ ሲመልስበት ያንኑ ኳስ ሳይዘጋጅ ያገኘው ስንታየሁ መንግሥቱም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ሻሸመኔዎች ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደራጀ መንገድ ለመግባት ሲቸገሩ 33ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ተቆጥሮባቸዋል። አዳነ በላይነህ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው ጋዲሳ መብራቴ መሬት ለመሬት በመምታት በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ግብ አድርጎታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ተደርጎበታል። ሆኖም 67ኛው ደቂቃ ላይ የሠራተኞቹ የመሃል ተከላካይ ተስፋዬ መላኩ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተወገደበት ፣ የሻሸመኔው ያሬድ ዳዊት ያለ ንክኪ ብቻውን የቀኝ እግሩ በመታጠፉ ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዶ ወደ ወደ ሆስፒታል ካመራበት አጋጣሚ በቀር ትኩረት የሚስብ አጋጣሚ አልተፈጠረም። የአጋማሹ ብቸኛ ዒላማውን በጠበቀው ሙከራም የሻሸመኔው የግራ መስመር ተከላካይ አሸብር ውሮ ከቅጣት ምት ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለው በቀላሉ ይዞበታል። ጨዋታውም በወልቂጤ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሻሸመኔው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ብዙ መማር እንዳለባቸው ገልጸው ጊዜ ይፈልጋል እንጂ መሻሻል የሚችል ቡድን እንዳላቸው ሲናገሩ አንድን ቡድን ከመውረድ ለማትረፍ አሰልጣኝ ብቻ በቂ እንዳልሆነ እና አመራሮችም የተጫዋቾችን ጥያቄ በመፍታት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል። የወልቂጤው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት በበኩላቸው ልምምድ ባለመሥራታቸው ስጋት እንደነበራቸው እና ውጤቱ ካሰቡት ውጪ መሆኑን በመናገር ከዕረፍት መልስ በቁጥር ማነሳቸው ጫና እንዲፈጠርባቸው ምክንያት እንደሆነ በመግለጽ ነጥቡ አስፈላጊ ቢሆንም ቀስ በቀስ ለተመልካች ሳቢ የሆነ ጨዋታ ለመጫወት እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።