ሰበታ ከተማ ዩጋንዳዊ አጥቂ አስፈርሟል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ዩጋንዳዊው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ለሰበታ ከተማ ፊርማውን ያኖረ ሲሆን በዛሬው ጨዋታ የመሰለፉ ዕድሉም የሰፋ ይመስላል፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ12 ሳምንታት ጉዞው የተሳኩ የጨዋታ ወቅቶችን ማሳለፍ ያልቻለው ሰበታ ከተማ በደረጃ ሰንጠረዡ በያዘው ሰባት ነጥብ 15ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡ በተደጋጋሚ የአጥቂ አማራጭ እጦት በጉልህ ይታዩበት የነበረው ሰበታ ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ ኡጋንዳዊውን አጥቂ ዴሪክ ኒሲምባምቢን ወደ ክለቡ ቀላቅሏል፡፡

የትውልድ ሀገሩን ክለብ ካምፓላ ሲቲን ከለቀቀ በኋላ ወደ ግብፅ አምርቶ በስሞሃ ክለብ ቆይታን ማድረግ የቻለው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ጥቂት ቀናትን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ያሳለፈ ሲሆን በሰበታ ከተማ ደስተኛ መሆን በመቻሉ በፊፋ የነፃ ዝውውር መስኮት ወደ ስብስቡ መቀላቀሉን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች፡፡ የአጥቂ አማራጮች ውስንነት የነበረበትን ክለብ የማስቆጠር ክፍተት ይደፍናል ተብሎ የሚጠበቀው አጥቂው በዛሬው ዕለት የሊግ ካምፓኒውን ፍቃደኝነት ካገኘ የመሰለፉ ጉዳይ የሚታወቅም ይሆናል፡፡

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከሲዳማ ቡና ጋር የአንድ ዓመት ውል ከፈፀመ በኋላ ወደ ሀገሩ ባልታወቀ ምክንያት አምርቶ የነበረው አጥቂው ብቸኛው የሰበታ ከተማ የውጪ ሀገር ዜግነት ያለው ተጫዋችም ይሆናል፡፡ ክለቡ ከናሚቢያዊው አጥቂ ጂኒያስ ናንጄቦ እና ዩጋንዳዊው አማካይ ክሪዚስቶም ንታንቢ ጋር መለያየቱ ይታወሳል፡፡