የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 1-5 አዲስ አበባ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

አዲስ አበባ ከአምስት ጨዋታዎች ድል አልባ ጉዞ መልስ ሰበታ ከተማን በግብ ተንበሽብሾ ካሸነፈበት የምሽቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ደምሰው በፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ

ውጤቱን ጠብቃችሁት ነበር?

በእርግጥ ለማሸነፍ ነው የመጣነው፡፡ ጎሉ በርከት ብሏል፤ ማሸነፍ እንዳለብን መጀመሪያም ተናግሬ ነበር። ምክንያቱም ከዚህ ቀጠና ለመውጣት የግድ ማሸነፍ አለብን። ጎሉ በእርግጥ በርከት ያለ ነው፡፡

በጨዋታው ላይ የነበረው የቡድን ስራ ?

እውነት ነው፤ አዎ የኛ ቡድን መጀመሪያም የሚታወቀው እንደዚህ በጋራ በመጫወት ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ወጣቶች ስለሆኑ በጋራ በመጫወት ነው መሀል ላይ የተወሰነ ልምድ ያላቸው አሉ ያንን የሚያቀናጁ። ስለዚህ በጋራ የመጫወት መጀመሪያም ከሀዋሳ የነበረውን ያንን አጥተን ነው ትንሽ ውጤትም የራቀን። አሁን ግን ትክክለኛው ይሄ ነገር ነው፡፡

የተገኙ ዕድሎችን በመጠቀሙ ረገድ የተለየው ነገር ?

ያው አንዳንድ ጊዜ ሽንፈት ሲመጣ ብዙ ነገር ያሳይሀል። እነዛን ነገሮች ለመቅረፍ ትሰራለህ ፣ ትነጋገራለህ ያሉንን ችግሮች ለመፍታት የጋራ ስለሆነ እነኚህ ነገሮች ውጤታማ አድርገውናል፡፡

ውጤቱ ለቀጣይ ስለሚፈጠረው ሞራል ?

በጣም ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆነናል፡፡በተከታታይ ሽንፈት ስለበረብን ከዛ ሽንፈት ለመውጣት በጣም ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርግልናል፡፡

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ሰበታ ከተማ

ቡድኑ ላይ ስለተፈጠረው ነገር ?

እነርሱ ሲጫወቱ እኛ ተመልከትን ወጣን፡፡ እንደዛ ነው ማለት የሚቻለው። ምክንያቱም አጠቃላይ ቡድኑ የጨዋታ ፍላጎት ምንም የለውም። ተጫዋቾቹን እንደተመለከትከው ምንም አይነት የጨዋታ ፍላጎት የለም፡፡ ይሄ ደግሞ ብዙ ጊዜ በአንዳንድ ነገሮች ምክንያት የሚከሰቱ አሉ። ግን በአብዛኛው እንደዚህ አይነት ችግሮች ሲከሰቱ ችግሩን ዋጥ አድርገህ ነው የምትሰራው። ምክንያቱም ወደ ውጪ ማውራቱ ብዙም ትርጉም ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ ደግሞ ክለቡ ላይ ተፅእኖ እያደረገ ይመጣል፡፡ ክለቡ ላይ ብቻም ሳይሆን ለእኛም ባለሙያ ሆነህ ስትሰራ የራስህ ነው የሚያበላሸው ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ገጥሞኝ አያውቅም ዋና ገፀ ባህሪ ሆነህ የምትታየው አንተ ነህ። ስለዚህ ምን አይነት ችግሮች አሉ የሚለውን ጉዳዮች ያው እኛ እናውቀዋለን። ግን ብዙ አጉልተን አናወጣውም፡፡ በአጠቃላይ ይታይ የነበረው እንቅስቃሴ ምንም አይነት የጨዋታ ፍላጎት የለም ብሎ መደምደም ይቻላል እንጂ የፈለገ ቢሆን ቢያንስ ወይ መከላከሉን አልቻልክም ወይሞ ማጥቃቱን አልቻልክም፡፡ ስለዚህ እነርሱ ሲጫወቱ እኛ ተመልክተን ወጣን የሚለው በደንብ ይገልፀዋል፡፡

ተጫዋች በአንተ እምነት የላቸውም ወይንስ ለጨዋታው ዝግጁ አልነበሩም ?

ተጫዋቾቹ በእኔ ወይንም እኔ በተጫዋቾቹ ያለን እምነት እኔ ጠንካራ እንደሆነ ነው የማምነው። ምክንያቱም ከጅምሩ አንስቶ የነበሩ ነገሮች ብዙ ገላጭ የነበሩ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ የሚነሱ አሉ፡፡ እኔ ዛሬ ላይ ብናገረው ያን ያክል ውጤታማ ሳትሆን ሳትሆን ቀርተህ ወሬ ከማውራት የዘለለ ምንም የምፈጥረው ነገር አይኖርም፡፡ ነገር ግን እንደ ክለብ ስታወራ አስተዳደራዊ ችግሮች ብዙ አሉ፡፡ አሁንም ለሽንፈቱ ምክንያት እያደረኩ አይደለም ለምሳሌ የ2013 ደመወዝ ያልተከፈላቸው 11 ልጆች አሉ። ክለቡ ላይ ይሄንን እስከ ዛሬ አፍነን ነው የያዝነው። ከዚህ ክለብም ወጥተው ወደተለያዩ ክለባትም የገቡ ተጫዋቾች አሁንም ደመወዝ ይጠይቃሉ፤ የመቼውን የ2013 ነው የሚጠይቁት። እኛ ጋር ያለው አቋም ምንድነው ልምምድ በምንም አይነት ሁኔታ አይቆምም ነው፤ እየሰራህ ጠይቅ ነው ወስነን የነበረው። አሁንም አቋማችን ያ ነው፡፡ ግን እየሰራህ መጠየቅ የሚለው ከህግ አንፃር ትክክል ቢሆንም ተጫዋቹ ጋር ደግሞ ማቆም እንደማይችል ስለሚረዳ ማድረግ የሚችለው መቶ ፐርሰንት ሰጥቶ አለመጫወት ነው፡፡ የኛ አሁን እይታ ያ ነው። ከባለፈው ጀምሮ በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ፤ ነገር ግን የሚመለስ የለም። ያለፈው ወር ደመወዝ ጨምሮ እሱም አልተከፈለም። የ2013 ደመወዝ ያልተከፈላቸው ተጫዋቾች ቡድኑ ውስጥ አሉ 11 አሉ፡፡ አንደኛው ባለመከፈሉ ምክንያት በራሱ ትቶ ሄዷል፤ ንታንቢ ማለት ነው። ስላልተከፈለው አመልክቶ ትቶ ሄዷል፡፡ እነዚህ ተፅእኖ ያደርጉብሀል። ነገር ግን እነዚህን ነገሮች ሁል ጊዜ በውስጥህ ይዘህ የምትቆየው ለምንድነው ብቃት የሚባለው ጀግንነት የሚባለው የትኛውም ችግሮች ሲከሰቱ እነዛን አሸንፎ ማለፍ ነው የሚል እምነት ስላለን ነው፡፡ እንዳልኩህ ዛሬ ላይ ባወራ ሰሚ ላይኖረን ይችላል። ውጤት ሲጠፋ ምክንያት መደርደር ነው የእኛ ሀገር ባለሙያ የሚባል ነገር ይመጣል፡፡ ያ ነገር እንዳይመጣ ነው አፍነን ያቆየነው። እነዚህ ችግሮች ስላሉ ምናልባት በቀጣይም ሊከብዱ ይችላሉ፡፡ እነኚህ ካልተፈቱ ትንሽ ይከብዳል የሚል ግምት አለኝ፡፡