​የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በጨዋታ ሳምንቱ በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች የሁለተኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 በአራት ጎሎች ላይ የተሳተፈው ፍፁም ጥላሁን

አዲስ አበባ ከተማ ድንቅ የጨዋታ ዕለት አሳልፈው በወራጅ ቀጠና ፉክክር ውስጥ ትልቅ ዋጋ በነበረው ጨዋታ ሰበታ ከተማን 5-1 ሲረቱ ፍፁም ጥላሁን ደማቅ የነበረ ምሽት አሳልፏል።

በ23ኛው ደቂቃ ከቻርልስ ሪባኑ የደረሰውን አስደናቂ ረጅም ኳስ ተጠቅሞ ግብ ማስቆጠር የቻለው ፍፁም በ36ኛው ደቂቃም እንዲሁ ከዋለልኝ ገብሬ የደረሰውን ጊዜውን የጠበቀ ኳስ ተጠቅሞ ሁለተኛ ግብ አክሏል። ግብ ከማስቆጠሩ ባለፈም በ13ኛው እንዲሁም በ60ኛው ደቂቃ ከመስመር እና ከማዕዘን ምት ከተሻሙ ኳሶች የመጀመሪያ ኳሶችን በማሸነፍ ለሪችሞንድ አዶንጎ እና ሙሉቀን አዲሱ ላስቆጠራቸው ግቦች ኳሶቹን በማመቻቸት በጨዋታው በድምሩ ቡድኑ ካስቆጠራቸው አምስት ግቦች በአራቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ የተሳካ ጊዜን አሳልፏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ግብ አስቆጣሪነት የተመለሰው ፍፁም በሰጠው አስተያየት ድሉ ለቡድኑ የተሻለ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ገልፆ በግሉ አሁንም ከ30 በላይ ግቦችን የማስቆጠር ዕቅድ እንዳለው ሲገልፅ ከመጫወቻ ቦታ አንፃር ከተክለ ቁመናው እና ሰዎች ከሚሰጡት ሀሳብ መነሻነት ከፊት አጥቂነት ይልቅ ከመስመር ሲነሳ ምርጫው እንደሆነም እንዲሁ ተናግሯል።

የቡድን ተጫዋቾች አይደለም በሚል ተደጋጋሚ ትችቶች ሲሰነዙሩበት የነበረው ፍፁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከማስቆጠር አልፎ ለቡድን አጋሮቹ ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ መስጠቱ በቡድን መዋቅር ውስጥም የቡድን ተጫዋች ሆኖ መጫወት እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ነው።

👉 ሁለገቡ አማካይ ቻርልስ ሪባኑ 

በዘንድሮው የአዲስ አበባ ከተማ ስብስብ ውስጥ በሜዳ ላይ መኖሩ እና አለመኖሩ ትልቅ ልዩነት ሲፈጥር ከተመለከትንባቸው ተጫዋቾች ውስጥ በቻርልስ ሪባኑ ደረጃ አጠቃላይ የቡድኑ የጨዋታ መንገድ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር ተጫዋች አለ ብሎ መናገር አይቻልም። 

ናይጄሪያዊው አማካይ እንደ አብዛኞቹ የውጭ ሀገር ዜግነት እንዳላቸው ስድስት ቁጥር ተጫዋቾች የተጋጣሚን እንቅስቃሴ የማቋረጥ (ቆሻሻውን ስራ) ከመስራት ባለፈ አስደናቂ ረጃጅም እና አጭር ኳሶቹ የተጫዋቹን ሁለገብነት በአግባቡ የሚያሳዩ ናቸው። 

ፍፁም ጥላሁን ሰበታ ከተማ ላይ ሁለተኛውን ግብ ሲያስቆጥር ከራሳቸው የሜዳ አጋማሽ እጅግ አስደናቂ የሆነ የረጅም ኳስን ማድረስ የቻለው ተጫዋቹ በጨዋታው በመሰል ረጃጅም ኳሶች የቡድን አጋሮቹ ለማግኘት ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል።

ከዚህም ባለፈ እሱ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ከተከላካይ መስመሩ ፊት ያሉትን ቦታዎች በሚገባ እየተንቀሳቀሰ ሽፋን በመስጠት ረገድ ድንቅ ጊዜያትን እያሳለፈ የሚገኝ ሲሆን ምንም እንኳን ከከፍተኛ ሊግ ክለብ ወደ አዲስአበባ ከተማ ቢያመራም የቡድኑን ደረጃ በማሻሻል ረገድ ግን ቁልፍ ሚናን እየተወጣ ይገኛል።

👉 የጀማል ጣሰው ስህተቶች 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የአዳማ ከተማው የግብ ዘብ ጀማል ጣሰው በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች በተጋጣሚ ተጫዋቾች ወደ ግብነት የተቀየሩ ሁለት አደገኛ ስህተቶችን ሲሰራ ተመልከተናል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ፋሲል ከነማን መርቶ ነጥብ በጣለበት ጨዋታ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ ለመያዝ ግቡን ለቆ የወጣው ጀማል ጣሰው የጊዜ አጠባበቁ ስህተት ስለነበር ኦኪኪ ቀድሞት በግንባሩ ያስቆጠረ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ብሩክ  ሰሙ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ በመጀመሪያ ሙከራው መቆጣጠር ባለመቻሉ አዲሱ አቱላ ላስቆጠራት ግብ ምክንያት ሆኗል።

እርግጥ በሁለቱ ጨዋታዎች ቡድኑ ለጣለው ነጥብ ጀማልን ብቻ ተወቃሽ ማድረግ ባይቻልም ተጫዋቹ በሚጠበቅበት ደረጃ ትክክለኛ ውሳኔዎችን ወስኖ ቢሆን ኖር ግን ቡድኑ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ በቻለ ነበር።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተቀዳሚ ሦስት ግብ ጠባቂዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ባለልምዱ ጀማል በዚህ ደረጃ መሰረታዊ የግብ ጠባቂ ክህሎት በሚሰኙት መመዘኛዎች ስህተትን ሲፈፅም መመልከት በጣም የሚያስገርም ሲሆን በተከታታይ ጨዋታዎች እነዚህን ስህተቶች መስራቱ ምናልባት በቀጣይ ጨዋታዎች የመጀመሪያ ተሰላፊነት ዕድሉን እንዳያሳጣው ያሰጋል።

👉 አዲሱ ተስፋዬ ወደ ሜዳ ተመልሷል 

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሰበታ ከተማን ለቆ ወደ አዳማ ከተማ ያመራው የቀድሞው የወላይታ ድቻ እና መከላከያ የመሀል ተከላካይ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በአዳማ ከተማ መለያ የመጀመሪያውን ጨዋታ በመጀመሪያ ተሰላፊነት አድርጓል።

ወደ አዳማ ከተማ ከተዘዋወረ ወዲህ የአሁኑን ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ሳይጨምር በአንድ ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ለ44 ያህል ደቂቃዎች ከመጫወቱ ባለፈ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት ሰብሮ ለመግባት ተቸግሮ የቆየው ተጫዋቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የቡድኑ ሁለገብ ተከላካይ የሆነው ሚሊዮን ሰለሞን በአምስት ቢጫ ካርድ መሰለፍ አለመቻሉን ተከትሎ በመጨረሻም በመጀመሪያ ተመራጭነት ተሰልፎ ተጫውቷል።

ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት በመጣበት የመከላከያው ጨዋታም ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም በምናውቀው መልኩ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ይበልጥ ኃይልን በመቀላቀል የተጋጣሚን እንቅስቃሴ በማቋረጥ ረገድ ጥሩ ቀን ያሳለፈ ሲሆን በተጨማሪነትም የአየር ላይ ኳሶችን በማሸነፍ ሆነ እንዲሁም በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ የአየር ላይ ኳሶችን በመግጨት ተደጋጋሚ ስጋቶችን ሲደቅን አስተውለናል።

👉 አስደናቂዋ የወንድማገኝ ኃይሉ ጎል 

ሀዋሳ ከተማ ፋሲል ከነማን በረታበት ጨዋታ ሀዋሳዎች የጨዋታውን የማሸነፍያ ግብን ያገኙበት መንገድ ትኩረት የሚስብ ነበር።

የጨዋታው ውጤት መግለጫ 1-1 በሚያሳይበት እና የደቂቃ መቆጠርያው 86ኛው ደቂቃ ላይ በሚያመላክትበት ወቅት ፋሲል ከነማዎች የማሸነፍያዋን ግብ ፍለጋ ያገኙትን የማዕዘን ምት ለመጠቀም የሀዋሳን ሳጥን በ7 ሰዎች ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከማዕዘንኑ ከተሻማው ኳስ መነሻነት በሁለተኛ ምዕራፍ የተገኘውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ ዳግም ወደ ግብ ሜክሮ በግቡ አግዳሚ ሲመለስበት በሳጥኑ ጠርዝ አካባቢ ኳሶችን ሲጠብቅ የነበረው ወንድማገኝ ኃይሉ ኳሱን ይዞ በመውጣት በፍጥነት የተሻለ አቋቋም ላይ ለሚገኝ የቡድን አጋሮቹ ለማቀበል ያደረገው ጥረት በከድር ኩሊባሊ ቢቋረጥም መልሶ በማግኘት ራሱ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በአስደናቂ ፍጥነት እየነዳ ሄዶ ግሩም የመልሶ ማጥቃትን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከግቧ መቆጠር አስቀድሞም በተመሳሳይ ፋሲል ከነማዎች ካገኙት የማዕዘን ምት የተነሳውን ኳስ ፋሲል ከነማዎች ኳሱን የሚያሻማውን ተጫዋች ጨምሮ በስምንት ተጫዋቾች የማዕዘን ምቱን ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም የማዕዘን ምቱን ማቋረጥ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በወንድማገኝ ኃይሉ አማካኝነት ወደ ማጥቃት ከተሸጋገሩ በኋላ 3ለ2 በሆነ የቁጥር ብልጫ ለተባረክ ሄፋሞ ያደረሰውን ኳስ ተባረክ መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።

ከተቆጠረው ግብ እና ከዚያ ቀደም በነበረው ሙከራ ጋር በተያያዘ የፋሲል ከነማዎች “Rest Defense” ጥያቄ ውስጥ መክተት ቢቻልም ወንድማገኝ ከራሱ ሜዳ ኳሱን ተሸክሞ የወጣበት ድፍረት ፣ ፍጥነት እና ኳሷን ለመጨረስ የነበረው መረጋጋት ፍፁም የሚያስገርም ነበር።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ወጣት ተጫዋቾች የተሰኘው ወንድማገኝ ኃይሉ ዘንድሮ ሁለተኛው ሙሉ የውድድር ዘመን እንደመሆኑ እና በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ካሳየው አስደናቂ ብቃት አንፃር ከፍ ባለ ጥበቃ (Expectation) ውስጥ ሆኖ ውድድሩን ቢጀምርም በተጠበቀው ደረጃ ከፍ ያለ ብቃቱን ለማሳየት ተቸግሮ ሰንብቷል ፤ በመጨረሻዎቹ ጥቂት ጨዋታዎች ግን በሚታይ መልኩ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል።

👉 ድንቅ የነበረው አላዛር ማርቆስ 

በግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ በእስካሁኑ የ13 ሳምንት ጉዞ ውስጥ ሦስት ግብ ጠባቂዎችን የተጠቀሙት ጅማ አባ ጅፋሮች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ የተሰለፈው አላዛር ማርቆስ ድንቅ የሚባል ብቃቱን አሳይቷል።

ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች የቡድኑን ግብ ሲጠብቅ የሰነበተው ዮሀንስ በዛብህ ወደ ተጠባባቂነት ወርዶ ከጨዋታዎች በኋላ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት የመጣው ወጣቱ የግብ ዘብ ቡድኑ ወላይታ ድቻን 1-0 በረታበት ጨዋታ ቡድኑ ለተጋጣሚው ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን በቀላሉ ቢሰጥም የአላዛር አስደናቂ ግብ አጠባበቅ ግን ቡድኑ የውድድር ዘመኑን ሦስተኛ ድል እንዲያሳካ አስችሏል።

ከሀዋሳ ከተማ በውሰት ውል ለጅማ አባ ጅፋር እየተጫወተ የሚገኘው ወጣቱ ግብ ጠባቂ ከዚህ ቀደምም በተሰለፈባቸው ስድስት ጨዋታዎች ድንቅ ብቃቱን ማሳየት የቻለ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ሲያመክን አስተውለናል። 

በቀጣይም ግብ ጠባቂው ይህን ብቃቱን ማስቀጠል ከቻለ በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በቀዳሚዎቹ ግብ ጠባቂዎች ተርታ ለመመደብ የሚያበቃ አቅም እንዳለው ፍንጭ እየሰጠ ይገኛል።

👉 የጫላ ተሺታ እና አብዱረህማን ሙባረክ ጉዳይ 

ጫላ ተሺታ እና አብዱረህማን ሙባረክ ለቡድኖቻቸው ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ በመጀመሪያ ተሰላፊነት በመጀመር ጥሩ ጊዜያትን እያሳለፉ ይገኛል።

በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን የወልቂጤ ከተማ አስደናቂ የማጥቃት መሳሪያ የነበረው ጫላ ተሺታ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ወደ ሲዳማ ቡና ቢያመራም በሲዳማ በነበረው ቆይታ በተደጋጋሚ ጉዳቶች ሳቢያ በቂ ጨዋታዎችን ለማድረግ ተቸግሮ ቆይቷል። በተመሳሳይ አብዱራህማን ሙባረክም ከኢትዮጵያ ቡና የዕድሜ ዕርከን ቡድን ካደገ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ቆይታ ማድረግ ቢችልም ተደጋጋሚ ጉዳቶች የእግርኳስ ዕድገቱን በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሆን ሲያስተጓጉላቸው ተመልክተናል።

13ኛው የጨዋታ ሳምንትን ሳይጨምር ጫላ ተሺታ ዳግም በተቀላቀለው የወልቂጤ ከተማ መለያ 572 ደቂቃዎች መጫወት ሲችል በዚህም ሂደት ሁለት ግቦችንም ማስቆጠር ችሏል። በተመሳሳይ በፋሲል ከነማ በሚያቁት አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ አማካኝነት ድሬዳዋ ከተማን የተቀላቀለው አብዱረህማን ሙባረክ ደግሞ በተመሳሳይ የዚህኛውን የጨዋታ ሳምንት ጨምሮ በድሬዳዋ ከተማ መለያ ለ749 ያህል ደቂቃዎች መጫወት ሲችል እንደ ጫላ ሁሉ ሁለት ግቦችን ለቡድኑ ማስቆጠር ችሏል።

በጉዳት ሳቢያ ጫላ በ2013 እንዲሁም አብዱረህማን ደግሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መሰል ተከታታይ የጨዋታ ደቂቃዎች ለማግኘት ተቸግረው ከማሳለፋቸው አንፃር ከጉዳት በፀዳ መልኩ በተከታታይ ጨዋታዎች ለቡድኖቻቸው አገልግሎት የመስጠታቸው ጉዳይ ለክለቦቻቸው ተስፋ የሚሰጥ ነው።

👉 እዮብ ዓለማየሁ የድቻን ውለታ አልዘነጋም

በጅማ አባ ጅፋር መነቃቃት ውስጥ ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች መሀል የሆነው እዮብ ዓለማየሁ በዚህ ሳምንት የቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ አስቆጥሮ ደስታውን ባለመግለፅ ለሌሎች ምሳሌ ሆኗል።

እርግጥ ነው ከዚህም ቀደም በርካታ ተጫዋቾች በፊት የለበሱትን መለያ በማክበር ግብ ሲያስቆጥሩ ዝምታን መርጠው መታየታቸው አዲስ ነገር አይደለም። ሆኖም ከዚህ በተቃራኒ በቀደመ ክለባቸው ውስጥ ሳሉ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ውስጥ ያለፉ ተጫዋቾች እንደውም ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ደስታቸውን ሲገልፁ አስተውለናል። እዮብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ ጀምሮ እስከዋናው ቡድን ድረስ የተጫወተለት ወላይታ ድቻ ጋር አምና ሆድ እና ጀርባ ለመሆን ተቃርቦ እንደነበር አይዘነጋም። ተጫዋቹ በረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ በነበረበት ጊዜ ክለቡ ቦታውን በሌላ ተጫዋች ለመሸፈን ያደረግው ጥረት ከፍተኛ ቅሬታ ውስጥ ከቶትም ነበር። ምንም እንኳን እዮብ ከጉዳቱ በኋላ ዳግም ቡድኑን ቢቀላቀለም መሰል ክስተቶች በክለብ እና ተጫዋች መሀል እስከወዲያኛው መቃቃርን ሊያስከትሉ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።

ይህ ጉዳይ ተከስቶ ካለፈ ዓመት የሞላው ባይሆንም ግን ተጫዋቾቹ ቂም ያልያዘ መሆኑን በሚያሳይ መልኩ ለቀድሞው ክለቡ ያለውን ክብር ከመግለፅ አልተቆጠበም። ተጫዋቾች በእግርኳስ ህይወታቸው ከክለብ አስተዳደሮች ጋር በሚኖራቸው የስራ ግንኙነት የሚፈጠሩ ችግሮችን በውስጣቸው ይዘው ስሜታቸውን ብዙ ባሳለፉበት ክለብ ላይ ለሚገልፁበት አግባብም የእዮብ ምላሽ ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ነበር።