​ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ13ኛ ሳምንት ምርጥ 11

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ13ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች የተሻለ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን በሚከተለው መልኩ በምርጥ ቡድናችን አካተናል።

የተጫዋች አደራደር ቅርፅ 4-4-2 (ዳይመንድ)

ግብ ጠባቂ


አላዛር ማርቆስ – ጅማ አባጅፋር

በጉዳት ምክንያት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች አምልጦት የነበረው ቁመታሙ የግብ ዘብ አላዛር ቡድኑ ጅማ ድቻ ላይ ወሳኝ ሦስት ነጥብ እንዲያሳካ እጅግ ከፍ ያለ አበርክቶ ነበረው። ቡድኑ የጨዋታውን የማሸነፊያ ግብ 35ኛው ደቂቃ ላይ ከማግኘቱ በፊትም በቃልኪዳን ሁለት በስንታየሁ ደግሞ አንድ ጊዜ የተሰነዘሩትን እጅግ ለግብ የቀረቡ ኳሶች ያመከነበት መንገድ እና ቡድኑን በጨዋታው ያቆየበት ሂደት በምርጥ ቡድናችን ውስጥ ያለ ከልካይ እንዲገባ አድርጎታል።


ተከላካዮች


ሙና በቀለ – አርባምንጭ ከተማ

ዘንድሮ 732 ደቂቃዎችን ለአዞዎቹ ግልጋሎት የሰጠው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሙና በቀለ ቡድኑ ቡናን ሲረታ የተዋጣለት ቀን አሳልፏል። በመከላከሉም (ብዙም ጫና የኖረበት ባይሆንም) ሆነ በማጣቃቱ ረገድ ኮሊደሩን በሚገባ የሸፈነው ሙና በ56ኛው ደቂቃ ወርቅይታደስ ወደሜዳ ሲገባ ደግሞ መጀመሪያ ከተሰጠው የቀኝ ተከላካይነት ሚና ወደፊት በመጠጋት በመስመር ተጫዋችነት ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ወደ ሳጥን ሲልክ አስተውለናል።


ሳሙኤል አስፈሪ – አዲስ አበባ ከተማ

የግብ ክልላቸውን በደንብ ካላስደፈሩ የመሐል ተከላካዮች መካከል ፈርጣማው የአዲስ አበባ ተከላካይ ሳሙኤል ተጠቃሽ ነው። ቡድኑ ሰበታን 5-1 በረታበት ጨዋታም አልፎ አልፎ የሚሰነዘሩ ጫናዎችን ለማምከን ሲሞክር ነበር። በተለይ ሰበታዎች ጥራት ያላቸው የግብ ሙከራዎችን መሐል ለመሐል እንዳይሞክሩ የአንድ ለአንድ ፍልሚያዎችን እያሸነፈ በቀላሉ ግብ ጠባቂው ዳንኤል እንዳይጋለጥ አድርጓል።


መናፍ ዐወል – ባህር ዳር ከተማ

የጣና ሞገዶቹ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያለግብ በተለያዩነት ጨዋታ በተጋጣሚያቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አስተናግደው ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ የቡድኑ የኋላ ተመራጭ የነበረው መናፍ ከድሬዳዋ አጥቂዎች ጋር ይገናኝ በነበረባቸው ቅፅበቶች በንቃት እና በድፍረት ኳሶችን ሲያስጥል ተመልክተነዋል። አልፎ አልፎ አደገኛ አገባቦችን በመጠቀም ጭምር ቡድኑ ቢያንስ አንድ ነጥብ እንዲያገኝ ያደረገበት መንገድ ተመራጭ አድርጎታል።


መድኃኔ ብርሀኔ – ሀዋሳ ከተማ

በዕለቱ የሀዋሳ ከተማ የጨዋታ ዕቅድ ውስጥ የፋሲል ከነማን የመስመር ጥቃት መቋቋም ዋነኛው ትኩረት ነበር። ለዚህ መሳካት ደግሞ የቡድኑ የመስመር ተመላላሾች ሚና እጅግ አስፈላጊ ነበር። ከዚህ አንፃር መድኃኔ በጥሩ አተገባበር ኮሪደሩን ከጥቃት ሲከላከል የተመለከትነው ሲሆን ወደ ፊት በመሄድም የማጥቃት ተሳትፎን ሲያደርግ ነበር።

አማካዮች


ቻርለስ ሪባኑ – አዲስ አበባ ከተማ

ናይጄሪያዊው የአማካይ ተከላካይ ቻርለስ ሪባኑ ባሳለፍነው ሳምንት ጥሩ ጊዜ ካሳለፉ አማካዮች መካከል ቀዳሚው ነበር ማለት የሚቻል ይመስላል። ዋና ሀላፊነቱ ከነበረው ለተከላካዮች ሽፋን የመስጠት ሚና በዘለለ የማጥቂያ አማራጭ መነሻ (Focal point) የሆነው አማካዩ የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ አሲስቱን ያደረገበት መንገድ በግርምት የብዙዎችን ቅንድብ ወደላይ ከፍ ያደረገ ነበር። ከዚህ ውጪም በታታሪነት ብዙ የሜዳ ክፍሎችን በመሸፈን ቡድኑ እንዳይጋለጥ ጥሯል።


ሀብታሙ ሸዋለም – ወልቂጤ ከተማ

ከወትሮው በተለየ እንደ ቅፅል ሥማቸው ሠራተኛ ሆነው ከሲዳማ ቡና ጋር የተፋለሙት ወልቂጤዎች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ድንቅ በነበሩበት ሰዓት የአማካዩ ሀብታሙ ብቃት ልዩ ነበር። ከሳጥን ሳጥን ከኳስ እና ከኳስ ውጪ በፍጥነት ሲንቀሳቀስ የታየው ሀብታሙ የቡድኑ አሠልጣኝ ተመስገን እንዳሉት የመጀመሪያ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቶ አጨዋወቱን ረገብ እንዲያረግ እስከተነገረው ድረስ እና ከዛም በኋላ በዋናነት ከኳስ ጋር ሲያደርገው የነበረው ብቃት ምርጫችን ውስጥ አካቶታል። የተጋጠሚ ቡድን አሠልጣኝ ገብረመድህን እንዳመኑትም የአማካይ መስመር ላይ ብልጫ እንዲወሰድባቸው ያደረገው አንድም የሀብታሙ ልዩ ብቃት ይመስላል።


ሙሉቀን አዲሱ – አዲስ አበባ ከተማ

በሊጉ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች አንፃር የጎላ አድናቆት ካልተቸራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሙሉቀን አዲሱ ነው። 13ቱም የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ከተጫወቱ የቡድኑ አራት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሙሉቀን (ሁለቱን ተቀይሮ ገብቶ) የቡድኑ የኳስ ቁጥጥር እድገት እንዲኖረው በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት ይታያል። ምንም እንኳን ሰበታ ላይ ከቆመ ኳስ መነሻን ያደረገ ግብ ቢያስቆጥርም በተደጋጋሚ ዘግየት ያሉ ሩጫዎችን በማድረግ በሦስተኛው የሜዳ ሲሶ እየተገኘ አማራጭ ሲሆን ይስተዋላል። 


ወንድማገኝ ኃይሉ – ሀዋሳ ከተማ

ከአማካይ መስመር እየተነሳ ዘንድሮ በስሙ ሁለት ጎል እና ሁለት አሲስት ያለው ወንድማገኝ የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን ላይ ያስቆጠራት የማሸነፊያ ግብ ከብዙዎች ዘንድ አድናቆት እንዲቸረው አድርጓል። በጨዋታው ለራሱ ሳጥን ተጠግቶ እንዲጫወት በአሠልጣኙ ሀላፊነት ተሰጥቶት የነበረው ወንድማገኝ  አይደክሜነቱን በማሳየት ለአጥቂ መስመሩም እንደ ድልድይ በመሆን ኳሶችን ወደፊት ሲልክ ነበር። እንዳልነው ደግሞ ባለቀ ሰዓት እጅግ ረጅም ርቀት ኳስ እየገፋ ሄዶ ያስቆጠራት ጎል ወሳኝነቷ ከፍ ያለ ነው።    

አጥቂዎች


በላይ ገዛኸኝ – አርባምንጭ ከተማ

አርባምንጭ ከተማ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል እንዲመለስ የበላይ ጎል አስፈላጊ ነበር። በቡድኑ ተመራጭ አደራደር ከኤሪክ ካፓይቶ ጋር ሳጥን ውስጥ እንዲያሳልፍ ሀላፊነት ተሰጥቶት ወደ ሜዳ የገበው ተጫዋቹ ኳስ እና መረብን ከማገናኘቱ በተጨማሪ የቡና ተከላካዮች በምቾት ኳስ እንዳይመሰርቱ የመቀባበያ አማራጮችን ለመዝጋት ሲታትር አስተውለናል። በጨዋታ ሳምንቱ ብዙ ግቦችን ያስቆጠሩ አጥቂዎች አለመኖራቸውን ተከትሎም በአንፃራዊነት የተሻለ ያልነው በላይ በስብስባችን የአጥቂ ቦታን አግኝቷል።                                     

ፍፁም ጥላሁን – አዲስ አበባ ከተማ

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ከ6ኛ ሳምንት (9) በመቀጠል ከአንደኛ እና ስምንተኛ ሳምንት ጋር በጣምራ ጥቂት ጎሎች (12) በተስተናገዱበት ሳምንት አራት ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረገው ፍፁም የነጠረ ብቃት አስመልክቷል። ተጫዋቹ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ግብ አግቢነት ሲመለስም ከዚህ በፊት የነበሩበትን የውሳኔ አሰጣት ችግሮች በቀጣይ እንደ ሰበታው ጨዋታ ካሻሻለ ለተከላካዮች የራስ ምታት እንደሚሆን ፍንጭ የሰጠበት ቀን ነበር።

አሠልጣኝ


ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ዓምና ከሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ጋር በማሳለፍ ለስኬት የቀረበ ውጤት ያላስመዘገቡት አሠልጣኝ ዘርዓይ ዘንድሮ በሀይቆቹ ቤት እጅግ አድናቆት የሚያስቸራቸው ቡድን እየገነቡ ይመስላል። የታታሪ፣ ተስፋ የማይቆርጥ እና አይደክሜ ስብስብ ባለቤት የሆኑት አሠልጣኙም የወቅቱን የሊጉን አሸናፊ ፋሲል ከነማ 2-1 ያሸነፉበት መንገድ የሳምንቱ ምርጥ አሠልጣኝ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የተጨዋች እና የፎርሜሽን ለውጥ አድርገው ጨዋታውን የቀረቡት አሠልጣኙም የተጋጣሚን የጨዋታ መንገድ አምክነው በራሳቸው መንገድ ከባዱን ፍልሚያ የወሰኑበት ሂደትም ድንቅ ነበር።


ተጠባባቂዎች
 

ቸርለስ ሉክዋጎ

ረመዳን የሱፍ

ጊት ጋትኩት

ኢማኑኤል ላርያ

ዳንኤል ኃይሉ

መስዑድ መሐመድ

ፀጋዬ አበራ 

እዮብ አለማየሁ