የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ14ኛ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮች በመጀመሪያው የፅሁፋችን ክፍል ተዳሰዋል።

👉 የተኛው ሰበታ ሊነቃ ይሆን ?

በደረጃ ሰንጠረዡ ቅርቃር እየዳከረ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ከአሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር የገባበት ሰጣ ገባ የብዙዎችን ትኩረትን ስቦ ነበር። አሠልጣኙ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ እንዲታገዱ ከተደረገ በኋላ ከሦስት ሳምንት በላይ ከክለቡ ጋር ያልነበሩት አሠልጣኝ ብርሃን ደበሌ ወደ ቡድኑ መጥተው በጊዜያዊነት እንዲያሰለጥኑ ተደርጓል። ለወትሮ በቡድናዊ መዋቅር በሁሉም የጨዋታ ምዕራፎች ላይ ደከም ብሎ የሚታየው ስብስቡ በወረቀት የዋንጫ ተፎካካሪ ተደርጎ ከሚሰወደው ባህር ዳር ከተማ ጋር ያደረገው ፍልሚያ እጅግ ጠንካራ አልሸነፍ ባይነት የተስተዋለበት ነበር።

በበርካታ ክለቦች የአሠልጣኝ ሹም ሽር ሲደረግ እንደ ጫጉላ ጊዜ የሚቆጠር መነቃቃት ሲከሰት የሚታይ ሲሆን በሰበታም ቤት ይህ ሂደት የመጣ ይመስላል። ይህንን በአፅንኦት እንድንናገር የሚያደርገን ደግሞ በቀደመ አሠልጣኙ ስር ሲጫወቱ የነበሩ ተጫዋቾች በተለየ ተነሳሽነት ጨዋታውን ሲከውኑ በማስተዋላችን ነው። እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ የመሰለፍ ዕድል ተነፍጓቸው የነበሩት እንደ ዱሬሳ ዓይነት ተጫዋቾችም ራሳቸውን ለማሳየት እና በመጀመሪያ አሰላለፍ ገብተው ክለባቸውን የማገልገል ብቃት እና ፍላጎት እንዳላቸው ሲያስመለክቱ ነበር። ከላይ እንዳልነው ይህ መነቃቃት በቀጣይ ጨዋታዎችም ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ በመጠኑም ቢሆን ሰበታ ብዙ ሳያረፍድ ከግርጌው ሊስፈናጠር ይችላል።

በዋናነት ግን በጨዋታው ቡድኑ ከኳስ ውጪ መታተር፣ ቦታዎችን መዝጋት፣ የተጋጣሚን ወሳኝ ተጫዋቾች መቆጣጠር እንዲሁም ፈጣን ሽግግር በማድረግ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል መድረስ ባህሪው ሆኖ ተጫውቷል። የባህር ዳር ከተማው አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከጨዋታው በኋላ እንደመሰከሩትም ሰበታ ከወትሮው በተለየ መልኩ ቅርፅ ያለው እንቅስቃሴ አድርጓል። የአንደኛውን ዙር ሊያገባድድ አንድ ጨዋታ ብቻ የቀረው (ከአርባምንጭ ከተማ) ቡድኑ ለቀጣይ የሊጉ ምዕራፍ ስንቅ የሚሆንለትን አዎንታዊ ውጤት በመጨረሻው ጨዋታ ይዞ ከወጣ እና በተለያየ መልኩ እንደምንሰማው በውድድር ዘመኑ አጋማሽ በሚከፈተው የዝውውር መስኮት ራሱን ካጠናከር ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ከሦስት ጨዋታዎች ያነሰ ነጥቦች ብቻ እንደመቅረቱ ራሱን ከስጋት ሊያፀዳ ይችላል።

👉 በእንቅስቃሴ ረገድ ተሻሽለው የቀረቡት ኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሊጉን 1ኛ እና 2ኛ ሆነው ማጠናቀቅ የቻሉት ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ ግን በአምናው ደረጃ እንደማይገኙ በተደጋጋሚ እየተመለከትን እንገኛለን። በተለይ ደግሞ ሁለቱም ሽንፈት ባስተናገዱበት የባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሜዳ ላይ ያሳዩት እንቅስቃሴ ጥያቄ እንዲነሳባቸው ያስገደደ ነበር።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሁለቱን ቡድኖች ባገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ሁለቱም ከባለፈው የጨዋታ ሳምንት አንፃር ፍፁም የተሻሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን አሳይተው ጨዋታቸውን አንድ አቻ በሆነ ውጤት ፈፅመዋል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በአርባምንጭ ከተማ ሲሸነፉ በሙሉ ዘጠና ደቂቃ ምንም ዓይነት ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራም ሆነ እንደከዚህ ቀደሙ ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ማሳደግ ተስኗቸው የነበሩት ቡናዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ፋሲልን ሲገጥሙ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከፍ ያለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በመውሰድ እና በቀጥተኛ ቅብብሎች ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በማድረስ ረገድ የተሻሉ ጊዜያትን አሳልፈዋል።

ነገር ግን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም የተሻለ በነበረበት የመጀመሪያ አጋማሽ በክፍት ጨዋታ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግሮ የተስተዋለው ቡድኑ በአጋማሹ ያስመዘገባት ብቸኛ ኢላማዋን የጠበቀች ሙከራ አቡበከር ናስር በቀጥታ ከቅጣት ምት የመታት እና የግቡን ቋሚ ለትማ ስትመለስ አበበ ጥላሁን ወደ ግብነት የቀየራት ኳስ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽም ቡድኑ በማጥቃቱ ረገድ ፍፁም ተቀዛቅዞ የተመለከትነው ሲሆን በንፅፅር በአጋማሹ በግብ ጠባቂያቸው አቤል ማሞ ንቃት ታግዘው በመከላከሉ ከነበራቸው ትጋት ውጪ በማጥቃቱ ረገድ በአዎንታዊነት የሚጠቀስን ነገር ማስመልከት ሳይችሉ ቀርተዋል።

በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ከወትሮው አነስተኛ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢኖራቸውም ከሳጥን ውጪ በሚደረጉ ሙከራዎችም ሆነ በተለይ መሀል ለመሀል ከተሰለፉት ሱራፌል ዳኛቸው እና በዛብህ መለዮ መነሻ ባደረጉ ኳሶች ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል።

በሁለተኛው አጋማሽም ከመጀመሪያው በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻቸውን ያሳደጉት ፋሲሎች በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ በመሀል ተገድቦ የነበረውን ማጥቃታቸውን በተሻለ ከመስመሮች ከሚነሱ ኳሶች እና ከኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመር በተስጀርባ በሚላኩ ቀጥተኛ ኳሶች ተጋጣሚያቸውን መፈተን ችለዋል።

በጨዋታው ፋሲል ከነማዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ላይ ጫና በማሳደር ኳሶችን በሜዳው የላይኛው ክፍል ማግኘት የቻሉ ሲሆን ግቧን ካስቆጠሩበት አጋጣሚ ውጪ የተገኙትን ኳሶች በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ፍፁም ደካማ ከነበሩበት የባለፈው የጨዋታ ሳምንት አንፃር በግልፅ የሚታዩ አዎንታዊ ለውጦችን በዚህ ሳምንት ቢያሳዩንም የቀደመው ጥንካሬያቸውን መልሰው ለማግኘት ግን ከዚህ በተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጉድለቶችን ሞልተው ይበልጥ ተሻሽለው መቅረብ ይኖርባቸዋል።

👉 ድሬዳዋ ከተማ እና የ’ባለሜዳ’ ተጠቃሚነት

ከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አንስቶ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በተወሰነ የደጋፊ ቁጥር በተመረጡ ከተሞች እየተካሄደ ይገኛል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ብዙዎች ባለሜዳ እና ከሜዳ ውጪ የሚጫወት ቡድን የሚባለው እግርኳሳዊ ሀሳብ ተፅዕኖው ቀንሷል የሚሉ ሀሳቦች እየተሰነዘሩ ይገኛል።

ውድድሩ አሁን እየተካሄደ በሚገኝበት ቅርፅ መካሄድ ከጀመረበት የተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አንስቶ ተቀማጭነታቸውን ባደረጉበት ከተማ ጨዋታዎችን ያደረጉ ቡድኖች ማግኘት ከሚገባቸው ነጥብ አንፃር ያሳኩትን ነጥብ ከመቶኛ ያለውን ንፃሬ ከተመለከተን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን 57.73% ነጥቦችን የማሳካት ስኬት የነበራቸው ሲሆን ዘንድሮ ግን እስካሁን ባለው ሂደት ይህ ንፃሬ ወደ 41.98% ወርዷል።

የዘንድሮው የውድድር ዘመን ከአፍሪካ ዋንጫ መልስ ከ10ኛ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ በድሬዳዋ ዓለምዓቀፍ ስታዲየም መካሄዱን ተከትሎ ብዙዎች በተወሰነ መልኩ የተንረጋገጨ የሊግ አጀማመር ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች መቀመጫቸውን ባደረጉበት ከተማ በቁጥር በርከት ካሉት ደጋፊዎቻቸው ታግዘው የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ ተብሎ ቢጠበቅም በእስካሁኑ ቆይታቸው በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ማስመዝገብ እየቻሉ አይገኝም።

በሜዳቸው እስካሁን አምስት ጨዋታዎችን ያደረጉት ድሬዎች አንድ ጨዋታ አሸንፈው በሁለቱ ሲሸነፉ በተቀሩት ሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል ይህም ማግኘት ከሚገባቸው አጠቃላይ የነጥብ መጠን 33.34% ብቻ ማሳካት እንደቻሉ ይጠቁማሉ። ይህም ከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አንስቶ በሜዳቸው ውድድሮችን ካደረጉ ቡድኖች የነጥብ ስኬት ንፃሬ አንፃር ስንገመግመው ሁለተኛ ዝቅተኛው ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከ7ኛ እስከ 11ኛ የጨዋታ ሳምንት ውድድሩን በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም አድርጎ 8.4% ነጥብን ከሰበሰበው ጅማ አባ ጅፋርን ብቻ የሚልቅ ነው።

በዚህ ረገድ በትልቅነቱ የሚጠቀሰው ባህርዳር ከተማ ከ12ኛ እስከ 16ኛ ሳምንት በባህርዳር ዓለምዓቀፍ ስታዲየም በተደረገው ውድድር ማግኘት ከሚገባው ነጥብ 83.34% በማሳካት ስኬታማ ጊዜ በማሳለፍ በቀዳሚነት የሚቀመጥ ሲሆን ሲዳማ ቡና በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የመጨረሻ አምስት የጨዋታ ሳምንታት እንዲሁ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም 73.34% ነጥቦችን በማሳካት ሁለተኛው ቡድን ነው።

እርግጥ የውድድሩ ቅርፅ መለወጡ በተወሰነ መልኩ ቡድኖች እንደቀደመው ጊዜ በሜዳቸው በመጫወታቸው የበለጠ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ያደረገ ሲሆን በተጨማሪም ቡድኖች ለሳምንታት ቆይታ በሚያደርጉባቸው ከተሞች ያለውን የመጫወቻ ሜዳም ሆነ ሌሎች ሁናቴዎችን ለመላመድ ከሚሰጣቸውዕድል አንፃር ይህ ሂደት ብዙ ላያስገርም ይችላል። የሆነው ሆኖ ግን በተገደበ የደጋፊዎች ቁጥርም ቢሆን በራሳቸው ከተማ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ ይበልጥ ወጥ ሆነው ውጤቶችን ማስመዝገብ የግድ ይላቸዋል።

👉 ስህተቶች የበረከቱበት የመከላከያ እና ሀዋሳ ጨዋታ

በ14ኛ የጨዋታ ሳምንት ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ሀዋሳ ከተማ እጅግ ድራማዊ በሆኑ ክስተቶች በተሞላው ጨዋታ መከላከያን 3-2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ሲችል በጨዋታው አምስት የፍፁም ቅጣት ምቶች ፣ አንድ ቀይ ካርድ እንዲሁም በርካታ የመከላከል ስህተቶች የተፈፀሙበትም ነበር።

የመጀመሪያው የዓዲስዓለም ተስፋዬ ግብ ስትቆጠር በቅድሚያ አዲሱ አቱላ መድሀኔ ብርሃኔ ላይ የሰራው ጥፋት አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ ማንሳት የሚቻል ሲሆን ከቆመ ኳስም የተሻማውን ኳስ መከላከያዎች ሰው ለሰውም ሆነ በዞን መከላከል ሳይችሉ በቁጥር በርከት ብለው ከመቆም በዘለለ ኳሱን ለመከላከል ያደረገጉት ጥረት ደካማ መሆኑ መነሻ ነበር።

ብሩክ በየነ ከፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ መነሻ የነበረው ዳዊት ማሞ ወንድማገኝ ኃይሉ ላይ የሰራው ጥፋት በወንድማገኝ ኃይሉ ቅርብ ርቀት ውስጥ አራት የመከላከያ ተጨዋቾች ቢኖሩም ኳሱን በአግባቡ መከላከል ባለመቻለቸው የመስመር ተከላካዩ በወሰደው እርምጃ ነበር።

መከላከያዎች ወደ ጨዋታ የተመለሱት ሁለት ግቦች የተገኙትም በተመሳሳይ ስህተቶች ነበር። የመጀመሪያው የኦኩቱ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ስትቆጠርም ሀዋሳ ከተማዎች ሳጥናቸውን በአግባቡ መከላከል ባለመቻላቸው አምበላቸው ዳንኤል ደርቤ በመጨረሻዎቹ ቅፅበቶች ቢኒያም በላይ ግብ እንዳያስቆጥር ለማገድ ጥፋት የሰራ ሲሆን የሰመረ ሃፍታይ ግብም እንዲሁ መሀመድ ሙንታሪ በፍጥነት ኳስ ለማስጀመር በማሰብ ለዓዲስዓለም የሰጠው ኳስ ዳግም ተመልሶ ወደ እግሩ ሲደርስ በፍጥነት መወሰን አለመቻሉን ተከትሎ ሰመረ ሃፍታይ ደርሶ ኳሷን አቋርጦ ግብ አስቆጥሯል።

መስፍን ታፈሰ ያስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት የተሰጠበት መንገድ በተወሰነ መልኩ አከራካሪ የነበረ ሲሆን በደቂቃዎች ልዩነት ላውረንስ ላርቴ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ በሚያሰጥ መልኩ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተነሳ የተሰጠበት ሂደት እጅግ ግልፅ የነበረ ስህተት ሆኖ አልፏል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች መከላከያዎች ያገኙት እና ቢኒያም በላይ ሳይጠቀምብ የቀረው የፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥም መጀመርያ በአግባቡ ማቋረጥ ያልቻለውን ኳስ ደግም ለማፅዳት ጥረት ያደረገው ፀጋሰው ድማሞ የሰራው ያልተገባ ጥፋት ቡድኑን ዋጋ ለማስከፈል ተቃርቦ ነበር ። በተቃራኒው እንዲሁ አሌክስ ተሰማም ኳስ በእጅ መንካቱን ተከትሎ ሀዋሳዎች ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

በእግርኳስ ጨዋታዎች ላይ የሚፈጠሩ ስህተቶችን ቡድናዊ በሆነ መዋቅር ውስጥ መመልከት የተሻለው አማራጭ እንደሆነ ይታመናል። ይህም ሲባል በመከላከል መዋቅር ውስጥ እያንዳንዱ የቡድን አባላት ማድረግ የሚገባቸውን ነገር ማድረግ አለመቻላቸውን ተከትሎ የእነዚህ ስህተቶች ድምር (Cumulative Effect) በመጨረሻ ሂደቱ ላይ ወስኖ እርምጃ የሚወስደውን ተጫዋቾች የትኩረት ማዕከል እንዲሆን ያስገድዳል።

በመሆኑም ሁለቱም ቡድኖች በመከላከሉ ረገድ መወገድ የሚችሉ በርካታ ጥፋቶችንም ሆነ መዋቅራዊ ስህተቶችን ሲሰሩ በተደጋጋሚ የተመለከትን ሲሆን በቀጣይ ቡድኖቹ በተሻለ መልኩ ለመፎካከር ላላቸው ውጥን መሰል ስህተቶችን መቀነስ አለፍ ሲልም እንደ ቡድን የሚከላከሉባቸውን መንገዶች መዘየድ ካልቻሉ ምንም እንኳን ግቦችን ማስቆጠር ቢችሉ እንኳን የተከላካይ መስመራቸው መሰል ስህተቶችን መስራቱን ከቀጠለ ዋጋ እንዳያስከፍላቸው ያሰጋል።

👉 ቅዱስ ጊዮርጊስ በስተመጨረሻም ግብ አስተናግዷል

ሊጉን በ28 ነጥብ እየመራ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ለሁለተኛ ተከታታይ የጨዋታ ሳምንት ነጥብ በመጋራት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር አቻ ሲለያይ ከሰባት ጨዋታዎች በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ አስተናግዷል።

በመከላከሉ ረገድ በሊጉ ዝቅተኛ ግብ የተቆጠረበት (5) ጠንካራውን የመከላከል መስመር ባለቤት የሆነው ጊዮርጊስ ከ630 ደቂቃዎች በላይ ግቦች ሳይቆጠሩበት ቢቆይም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ኤሪክ ካፖይቶ ከፍፁም ቅጣት ያስቆጠራት ግብ ከቆይታ በኋላ
የቻርልስ ሉኩዋጎን መረብ የደፈረች ግብ ሆና ተመዝግባለች።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ካፓዬቶ ካስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ በፊት ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ላይ በ6ኛ የጨዋታ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳ ከተማን 2-1 ሲረታ በተመሳሳይ በ50ኛው ደቂቃ ላይ ዓዲስዓለም ተስፋዬ በተመሳሳይ ከፍፁም ቅጣት ምት ግብ ማስቆጠሩ አይዘነጋም።

ከ2009 በኋላ ዳግም የሊጉን ክብር ለመቀዳጀት እየተጉ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከተከታዮቻቸው ያላቸውን ልዩነት ሊያሰፉባቸው የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ባለፉት ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ለመፍጠር ሰፊ ዕድል የነበራቸው ቢሆንም ባለፈው ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ መጋራታቸውን ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ከሚገኘው ሀዋሳ ከተማ በሁለት ነጥብ ብቻ ከፍ ብለው ሊጉን መምራታቸውን ቀጥለዋል።

👉 አርባምንጭ እና በልካቸው የተሰፋው የጨዋታ ስልት

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከከፍተኛ ሊግ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀሉት አርባምንጭ ከተማዎች በሊጉ ጥሩ የሚባል ጊዜን እያሳለፉ ይገኘሉ። ከጠንካራዎቹ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ያስመዘገቡት አራት ነጥብም አስደናቂ የሚባል ነው።

አካላዊ ዝግጁነት ላይ ያተኮረው የቡድኑ የተጫዋቾች ስብስብ ብዙ ርቀትን በታታሪነት በመሸፈን ሆነ በሌሎች አካላዊ ዝግጁነትን በሚጠይቁ የጨዋታ ባህሪያት ምቹ የሆነው አሰልጣኝ መሳይ ለእነዚህ ተጫዋቾች በተመቸ መልኩ እንደ ቡድን ታትሮ የሚከላከል አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ በሜዳው የላይኛው ክፍል ከፍ ያለ ጫና ተጋጣሚ ላይ በማሳደር በቀጥተኛ አጨዋወት እንዴት መጫወት እንደሚችል በግልፅ ባሳየባቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት ከባድ ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ማስመዝገቡ በራሱ አድናቆት የሚቸረው ነው።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ የሆነው ቡድኑ አሁን ላይ በ17 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በሊጉ የመጀመሪያ የውድድር ዘመናቸው ላይ እንደመገኘታቸው በሊጉ መቆየት ተቀዳሚ ግባቸው ስለመሆኑ ቢታመንም በተለይ በፊት መስመር የተገኙ ዕድሎችን ወደ ግብ በመቀየር ረገድ የቡድኑን አፈፃፀም ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥራት ደረጃቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾችን ማግኘት የሚችል ከሆነ ከዚህ በተሻለ ከፍ ማለት እንደሚችል ይታመናል።

አሁን ባለበት ደረጃም ቢሆን ግን በከፍተኛ ሊግ በቆየው ስብስብ ላይ መጠነኛ የሰው ኃይል ማሻሻያ በማድረግ እንደክለብ ያለውን አቅም እንዲሁም እንደ ቡድን የሚታይበትን ጠንካራ እና ደካማ ጎን ያገናዘበ አቀራረብን መከተሉ ለአርባምንጭ ከተማ አዋጭ ሆኖ እንደቀጠለ ማንሳት ተገቢ ነው።