የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች በሦስተኛው የፅሁፋችን ክፍል ተመልክተናቸዋል።

👉 የስንብት ዳርዳሩ እገዳ ነው

የመጀመሪያው ዙር ሊጠናቀቅ አንድ የጨዋታ ሳምንት በቀረው የዘንድሮው የሊግ ውድድር እስካሁን አሰልጣኝ የቀየሩ ቡድኖች ብዛት አምስት ደርሷል።

በዚህ ረገድ ቀዳሚ ከነበረው አዲስ አበባ ከተማ አንስቶ አሁን ላይ አሰልጣኝ ለመቀየር ሂደት ላይ የሚገኘውን ሰበታ ከተማን ጨምሮ ሁሉም ቡድኖችን ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው ሂደት በቀጥታ ከአሰልጣኞቹ ጋር ከመለያየት ይልቅ በቅድሚያ ዋና አሰልጣኞቹን በማገድ በሂደት ከቡድኑ ጋር የሚለያዩበትን አግባብ ለመፍጠር የሚሄዱበት መንገድ ተጠቃሽ ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ግን የዋና አሰልጣኙን መታገድ ተከትሎ በጊዜያዊነት መንበሩን መረከብ የቻሉት አራቱ የቀድሞ ምክትል ወይንም የቡድኑ ቴክኒክ ዳይሬክተሮች በኃላፊነታቸው እስካሁንም መዝለቅ ሲችሉ ወልቂጤ ከተማዎች ብቻ በቋሚነት አዲስ አሰልጣኝ መሾም ችለዋል።

በሀገራችን አሁን ላይ መጠነኛ መሻሻሎች ቢኖርም አሁን ድረስ ግን ደካማ የውል ስምምነት አስተዳደር እንዳለ እየታዘብን እንገኛል ፤ በተጫዋቾች ሆነ አሰልጣኞች ከቀጣሪዎቻቸው ጋር የሚኖራቸው የውል ስምምነት ላይ በዝርዝር ጥርት ብለው የተቀመጡ ነገሮች አለመኖራቸው ለበርካታ ንትርኮች በር ሲከፍት እየተመለከትን እንገኛለን። በተለይም በአንድ ወገን ፍላጎት በመነጨ ሀሳብ መነሻት የውል ስምምነቶች ሲፈርሱ በርካታ አሰጣገባዎች ሲፈጠሩ እየተመለከትን እንገኛለን።

ለአብነትም በአሰልጣኞች ቅጥር ወቅት ክለቦች ለሚቀጥሯቸው አዳዲስ አሰልጣኞች ህጋዊ መሰረት የሌለውን እና በውል ዘመን ቆይታ ተከፋፍሎ መከፈል የሚገባን ገንዘብ “በቅድመ ክፍያ” መልክ አስቀድመው መስጠታቸው ነገሮች በተፈለገው መልኩ አለመሄዳቸውን ተከትሎ በተለይ በክለቦች በኩል ለሚመነጩ የማሰናበት ፍላጎቶች እነዚህ በቅድመ ክፍያ ስም የሚፈፀሙ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ያላቸው ክፍያዎች ተግዳሮት ሲሆንባቸው እንመለከታለን።

ዘንድሮ እንኳን የታዘብናቸው አብዛኛዎቹ የአሰልጣኝ ስንብቶች ከአሰልጣኞቹ አልያም በጋራ ስምምነት የተመሰረቱ ሳይሆኑ የክለብ አመራሮች ክለባቸው እየተጓዘበት በሚገኘው የውጤት መንገድ ደስተኛ ባለመሆናቸው የሚፈጠሩ ሲሆን በዚህ ሂደት ክለቡ አሰልጣኙን ማሰናበት ቢፈልግም አስቀድመው የሰጡትን የቅድመ ክፍያ ገንዘብ ሊያስመልሱበት የሚችሉት የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩን ተከትሎ በይፋ ከማሰናበታቸው በፊት አሰልጣኞቹን በማገድ ይህን ገንዘብ መልሰው ሊያገኙበት የሚችሉበትን አግባብ እስኪፈጥሩ ድረስ በዚህ መንገድ መጓዝን ይመርጣሉ።

ታድያ ይፋዊ ባልሆኑ መንገዶች በሚደረጉ ድርድሮች አሰልጣኞቹ ገንዘቡን በተወሰነ መጠን ለመመለስ ከተስማሙ በይፋ መልቀቂያ ወስደው ከክለቡ ሲሰናበቱ ይህ ካልሆነ ግን “የሥነልቦና ጦርነት” በሚመስል መልኩ ክለቦቹ በንግግር ገንዘባቸውን ማግኘት ካልቻሉ አሰልጣኞቹን ከደረጃቸው ዝቅ ብለው የሚሰሩበት የስራ ከባቢ ውስጥ ወርደው እንዲሰሩ በማስገደድ መፍትሔ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ እየተመለከትን እንገኛለን።

ይህ ሂደት ከህግ አግባብ አንፃር በምን መልኩ ይቃኛል የሚለው ጉዳይ የህግ ባለሙያዎች የሚመልሱት ቢሆንም መሰል ህጋዊ ማዕቀፍ የሌላቸው አሰራሮችን በማስወገድ ወደ ዘመናዊው አሰራር መምጣት ግን የግድ የሚልበት ሰዓት ላይ እንገኛለን።

👉 በሊጋችን ያለው የአሰልጣኝነት መልከዓምድር እየተቀየረ ይሆን ?

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከሰማናቸው ዜናዎች አንዱ አዲስ አበባ ከተማዎችን ከእስማኤል አቡበከር ስንብት በኋላ ክለቡን በጊዜያዊነት እየመሩ የነበሩትን አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመሩ የመሰየማቸው ጉዳይ ነው።

እርግጥ ይህንን ሹመት በተለያዩ መንገዶች መመልከት ቢቻልም በጊዜያዊነት ቡድኑን በመሩባቸው ጨዋታዎች ባሳዩት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የተማመነው የክለቡ ቦርድ በሊጉ ለመቆየት እየተፋለመ ለሚገኘው ቡድናቸው በሊጉ የማሰልጠን ልምድ ለሌለው አሰልጣኝ የመስጠታቸው ጉዳይ ትኩረትን የሚስብ ነው።

በቀደሙት ጊዜያት አብዛኞቹ ቡድኖች በተለይ ደግሞ በሊጉ የመቆየት ስጋት ያለባቸው ቡድኖች በውድድር መሀል አሰልጣኞችን ሲቀይሩ ይበልጥ በሊጉ የመስራት ልምድ ያላቸው አሰልጣኞች ላይ የማተኮር ዝንባሌ የነበራቸው ሲሆን አሁንም ላይ በሚታይ መልኩ ተስፋ ሰጪ የእግርኳሳዊ አስተሳሰብ ለውጥ በክለብ አመራሮች ዘንድ እየተመለከትን እንገኛለን።

ከዚህ ቀደም በነበረው አካሄድ በፕሪሚየር ሊጉ የማሰልጠንዕድልን በብቸኝነት (Exclusively) የያዙ “የፕሪሚየር ሊግ” አሰልጣኞች በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ክለቦችን እየተዘዋወሩ ሲያሰለጥኑ እንጂ ሌሎች ደግሞ ከዚህ ስብስብ ውጪ የሆኑ አሰልጣኞች በሊጉ የማሰልጠን ዕድልን ለማግኘት እጅግ ፈታኝ የነበሩባቸው ሁኔታዎች የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ናቸው።

ታድያ አሁን ላይ ግን ይህን አካሄድን በተወሰነ መልኩ ሰብረው ለአዳዲስ አሰልጣኞች ዕድል የሚሰጡ የክለብ አመራሮችን በስፋት እየተመለከትን እንገኛለን። ለማሳያነትም በአሁኑ ወቅት በቋሚነትም ሆነ የሙከራ ዕድል አግኝተው ክለቦችን በኃላፊነት እየመሩ ከሚገኙ አሰልጣኞች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑትን አሰልጣኞች ከአንድ እና ሁለት ዓመት በፊት በፕሪሚየር ሊጉ የአሰልጣኞች ዝርዝር ውስጥ ያልነበሩ መሆናቸው የሊጉ የአሰልጣኞች ዝርዝር ምን ያህል እየተቀየረ እንደሚገኝ ማሳያ ነው።

👉 ዘርዓይ ሙሉ የተወደሰበት ጨዋታ

ከሀዋሳ ከተማ ጥሩ የሚባል ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሜዳ የተገኙት የሀዋሳ ደጋፊዎች እሱን የሚያወድስ ባነርን አሰርተ ይዘው በመግባት በመከላከያው ጨዋታ ወቅት ታይተዋል።

በተጫዋችነት ሲዳማ ቡናን በአምበልነት እየመራ ጥሩ ጊዜያትን ማሳለፍ የቻለው ዘርዓይ ወደ ሥልጠናውም ከመጣ ወዲህ የዓለማየሁ አባይነህ ረዳት በመሆን በሲዳማ ቡና ያገለገለ ሲሆን የዓለማየሁን ስንብት ተከትሎ ሲዳማ ቡናን በዋና አሰልጣኝነት ጥሩ ተፎካካሪ አድርጎ በመምራት አገልግሏል። አሰልጣኙ ከሲዳማ ከተለያየ በኋላ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በአዳማ ከተማ አጭር ቆይታ ማድረግ ችሏል። ዘንድሮ ደግሞ ሀዋሳ ከተማን እያሰለጠነ የሚገኘው ዘርዓይ አጀማመሩ ጥሩ የነበረ ባይሆንም በሂደት ግን የኃይቆቹን የውድድር ዘመን ወደ መስመር በማስገባት በአሁኑ ሰዓት ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለት ነጥብ አንሰው በሁለተኛ ደረጃ ለመቀመጥ በቅተዋል።

በመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ሳምንታት ከውጤት እንዲሁም ከጨዋታ መንገድ ጋር በተያያዘ ከደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ ትችትን ያስተናግዱ ከነበሩ አሰልጣኞች መካከል አንዱ የነበረው አሰልጣኙ በጨዋታ ሂደት የደጋፊዎችን ልብ ስለማሸነፉ የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ባነር ጠንካራ ማሳያ ሆኖ አልፏል።