​የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ግብዣ እና የገንዘብ ድጋፍ ተደረገለት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የ180 ደቂቃዎች ፍልሚያ ብቻ ለሚጠብቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የእራት ግብዧ እና የገንዘብ ድጋፍ ምሽት ላይ ተደረገለት።

በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ውድድር ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎች እያደረገ ይገኛል። በሁለተኛ፣ ሦስተኛ እና አራተኛ ዙር የማጣሪያ ፍልሚያዎች ተጋጣሚዎቹን ያሸነፈው ቡድኑም ወደ ዋናው ውድድር ለማለፍ ከጋና ጋር ብቻ መጫወት እንደሚቀረው ይታወቃል። ለደርሶ መልስ ፍልሚያው በጁፒተር ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ እየተዘጋጀ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ምሽት ከ1 ሰዓት ጀምሮ በቤል ቪው ሆቴል በተከናወነ መርሐ-ግብር የእራት ግብዧ እና የማበረታቻ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎለታል።

ቢ ኤፍ ፕሮሞሽን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ማኅበር በጋራ በመሆን ያዘጋጁት ፕሮግራም ይጀመራል ተብሎ ከተነገው ሰዓት እጅግ ዘግይቶ የተጀመረ ሲሆን በስፍራውም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እና ምክትል ፀሐፊው አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ታላቅ ተጫዋች ንጉሴ ገብሬ፣ የተለያዩ ተቋም አመራሮች፣ ባለ ሀብቶች፣ ኮሜዲያኖች እና የስፖርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

በደማቅ ሁኔታ አቀባበል የተደረገላቸው የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ቦታቸውን እንዲይዙ ከተደረገ በኋላ በክብር እንግድነት የተገኙት የቀድሞ ታላቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ንጉሴ ገብሬ የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል። ንጉሴ ለታዳጊዎቹ ራሳቸውን ካስተዋወቁ በኋላ ከፊታቸው ላለው ጨዋታ መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል።

በማስከተል የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የክብር እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ውጤታማ የሆነውን ብሔራዊ ቡድን አድንቀዋል። ፌዴሬሽኑ ባለው ውስን በጀት በስሩ ያሉትን ብሔራዊ ቡድኖች እያስተዳደረ እንደሚገኝ ገልፀው እንደ ሌሎች ሀገራት መንግስት ከብሔራዊ ቡድኑ ጎን ሆኖ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪም አቅርበዋል። በመጨረሻም ቢ ኤፍ አድቨርታይዚን እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበርን ይህንን ዝግጅት ስላዘጋጁ አመስግነው ንግግራቸውን ቋጭተዋል።
በስፍራው በተገኙት ኮሜዲያን በረከት (ፍልፍሉ) እና ደምሰው (ዋኖስ) ጨዋታ እየተዋዛ የቀጠለው መርሐ-ግብሩ ብሔራዊ ቡድኑ በሴካፋ ውድድር ዋንጫ ሲያመጣ ያለፈውን መሰናክል እንዲሁም ለዓለም ዋንጫ የሚያደርገውን የማጣሪያ ዝግጅት የሚያሳይ ዶክመንተሪ በስፍራው ለተገኙ አካላት ቀርቧል።

ዝግጅቱ እንዲሰምር ድጋፍ ያደረጉ አካላትን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ለብሔራዊ ቡድኑ ድጋፍ እንዲያደርጉ መድረክ ሲመቻች የተለያዩ አካላት ከ267 ሺ ብር በላይ እንዲሁም ከ150 ሺ ብር በላይ የሚያወጣ ትጥቅ በማበረታቻ መልክ ተሰጥቷል። ንብ ባንክ 100 ሺ ብር፣ አቶ መንሱር ጀማል 10 ሺ ብር፣ አቶ አዲስዜማ 12 ሺ ብር፣ አቶ ስለሺ 15 ሺ ብር፣ አቶ አሸናፊ ሰይፉ 30 ሺ ብር፣ አቶ እሱባለው ልይህ 50 ሺ ብር፣ አቶ አዛሪያስ ሀበሻ 20 ሺ፣ አቶ ሰለሞን ታምረት 10 ሺ ብር፣ አቶ ደረጄ ይበይን 20 ሺ ብር፣ አቶ ሳሙኤል መኮንን (ጎፈሬ) 150 ሺ ብር የሚፈጅ ትጥቅ ሲሰጡ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እና ወ/ሮ ትልቅሰው ድማሙ በቀጣይ ለቡድኑ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ፍሬው እና አምበሏ ናርዶስ ዝግጅቱ እንዲሰምር ላደረጉ ተቋማት እና ግለሰቦች የምስጋና የምስክር ወረቀት ከተሰጠ በኋላ የተሰማቸውን ስሜት በስፍራው ለሚገኙ አካላት አጋርተዋል። በቅድሚያም ናርዶስ ጌትነት በሴካፋ ውድድር በመጣው ውጤት የስፖርት ቤተሰቡ ደስተኛ በመሆኑ የተሰማቸውን ከፍ ያለ ደስታ ተጫዋቾችን ወክላ ከተናገረች በኋላ “የኮስታሪካን ትኬታችን እናንተ ጋር ነው ብላችሁናል። የኮስታሪካን ትኬት እኛ ለመቁረጥ ዝግጁ ነን። እናንተ ሻንጣችሁን ለመያዝ ተዘጋጁ” በማለት በስፍራው የተገኙ ሰዎችን ያስጨበጨበ ንግግር አሰምታለች። በተጨማሪም ሁለት የቡድኑ አባላት በክልላቸው ጋምቤላ የተደረገላቸው የመሬት ስጦታ ለሌሎቹም እንዲደረግ ጥሪ አቅርባለች።

አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል በበኩሉ ለተደረገላቸው ነገር ምስጋና አቅርበው “እግርኳስ በጣም ከባድ ነው። ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈው ነው ተጫዋቾቹ እዚህ የደረሱት። የሴቶች እኩልነት የሚከበርበት ሀገር ስለሆንን ተጫዋቾቹ ሊደገፉ ይገባል ብዬ አምናለው። አሁን የተደረገው ነገር በጣም ያስደስታል። የሚያበረታታም ነው። የጋምቤላ ክልል ባደረገው ነገር ደስተኛ ነን። ሌሎች ክልሎችም ተጫዋቾቹ ባሉበት ማበረታቻ ቢሰጧቸው ደስ ይለኛል። ሁለቱ ብቻ አይደለም ለብሔራዊ ቡድኑ የተጫወቱት። 24 እና 25 ተጫዋቾች አሉ። ለእነሱም የሆነ ነገር ቢደረግ ጥሩ ነው። እኛ ተጠሪነታችን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቢሆንም የምንጫወተው ለሀገር ነው። ስለዚህ የተለያዩ አካላት ይሄንን ቡድን ቢያበረታቱ ሀገርን እንደማበረታታት ነው።” ብለዋል።

በመጨረሻም ዋና አሠልጣኙ እና የተጫዋቾች ተወካይዋ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ህዝብ መዝሙር ከተዘመረ በኋላ ከቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ንጉሴ ገብሬ ሰንደቅ ዓላማ ተረክበዋል። የእራት ግብዧ ከተከናወነ በኋላም መርሐ-ግብሩ ፍፃሜውን አግኝቷል።