ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ15ኛ ሳምንት ምርጥ 11

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የውድድር ዓመቱ መጋመሱን ባበሰረው የጨዋታ ሳምንት በአንፃራዊነት የተሻለ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን እንደሚከተለው መርጠናል።

የተጫዋች አደራደር ቅርፅ 3-4-3

ግብ ጠባቂ

ይድነቃቸው ኪዳኔ – ፋሲል ከነማ

ዘንድሮ አስራ አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ያሳለፈው የግብ ዘቡ ይድነቃቸው በተደጋጋሚ ጨዋታዎችን በማድረግ የሚመጣው የጨዋታ ትኩረት ጉዳይ ሳይፈትነው ግቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። እርግጥ በጨዋታ ሳምንቱ ነጥረው የወጡ ግብ ጠባቂዎች አለመኖራቸውን ተከትሎ በቦታው አሳማኝ ሰው ለመምረጥ ብንቸገርም የፋሲልን ግብ ሲጠብቅ የነበረው ተጫዋች በአንዳንድ ቅፅበቶች ሲያሳያቸው የነበሩ ብቃቶች በምርጥ ቡድናችን እንዲካተት አድርጎታል።

ተከላካዮች

ደጉ ደበበ – ወላይታ ድቻ

አንጋፋው የመሐል ተከላካይ ደጉ ደበበ እንደ ከዚህ ቀደሙ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንትም ከወላይታ ድቻ ጠጣር የኋላ መስመር ጀርባ ያለ ቁልፍ ሰው መሆኑን አስመስክሯል። ደጉ ከወትሮ በተለየ ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት ሲከተል የተመለከትነው ሲሆን በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩት ወልቂጤዎች ዓላማ ያላቸው ቅብብሎችን በሦስተኛው የሜዳ ክልል አድርገው ግብ እንዳያስቆጥሩ ከፍተኛ ሚና ሲወጣ ነበር።

አዲስዓለም ተስፋዬ – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ ከ70 በላይ ደቂቃዎችን በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር ተጫውቶ ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ሲለያይ አዲስዓለም የሚመራው የኋላ መስመር ብቃቱ ከፍ ያለ ነበር። በተለይ ከቀይ ካርዱ በኋላ ከኳስ ውጪ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ቡድን ከኋላ ሆኖ በመምራት እንዲሁም አዳማ ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥሩ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች እና ቦታዎችን በመንፈግ ረገድ ትልቅ ሥራ አከናውኗል።

መልካሙ ቦጋለ – ወላይታ ድቻ

ብዙ የጨዋታ ዕድል የማያገኘው ቀልጣፋው የመሐል ተከላካይ እንደ አጣማሪው ደጉ ያሳየው ብቃት በምርጥ ቡድናችን እንዲገባ አድርጎታል። ከምንም በላይ በጥሩ ተግባቦት ግብ ጠባቂው ፅዮን ከሁለት ጊዜ በላይ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ እንዳይደረግበት የበኩላቸውን ሲያደርጉ የነበረበት መንገድ የሚደነቅ ነው። መልካሙም በዐየር እና የመሬት ፍልሚያዎች አልቀመስ በማለት ጥሩ ዕለት አሳልፏል።

አማካዮች

ዓለምብርሃን ይግዛው – ፋሲል ከነማ

በዘንድሮ የውድድር ዓመት በስሙ አንድ ጎል ያለው የቀኝ መስመር ተከላካይ በ15ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ድንቅ ብቃቱ ላይ ነበር። ተጋጣሚው ድሬዳዋ የመስመር ጥቃቶችን ለመመከት በ5 ተከላካዮች ለመጫወት ቢጥርም በቀኝ መስመር የተሰለፈው ዓለምብርሃን በፈጣን የፊትዮሽ ሩጫዎቹ የተቸመቸመወ የኋላ መስመር እንዲዘረዘር እና አጋሮቹ ክፍተቶችን እንዲያገኙ ተግቷል። በ61ኛው ደቂቃ ለተቆጠረው የሽመክት ጎልም ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል።

ሮቤል ተክለሚካኤል – ኢትዮጵያ ቡና

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ድንቅ ብቃት ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል ቀዳሚው ሮቤል ነው። በተከላካይ አማካይ ቦታ ተሰልፎ የነበረው ተጫዋቹ ለአዲሱ የመሐል ተከላካይ ጥምረት ተገቢ ሽፋን እየሰጠ የቡድኑ የኳስ ቅብብል እድገት እንዲኖረው ሲያደርግ የነበረበት መንገድ ጥሩ ነበር። የባህር ዳርን ወሳኝ ተጫዋቾች ከኳስ ውጪ ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረትም የሚደነቅ ነበር።

ዳዊት ተፈራ – ሲዳማ ቡና

ዳዊት ቡድኑ ሲዳማ ሀዲያ ሆሳዕናን ከመመራት ተነስቶ እንዲያሸነፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከኳስ ጋር ምቾት የሚሰማው ተጫዋች የአማካይ መስመሩን ከአጥቂ መስመሩ ጋር በደንብ እንዲገናኝ በረጃጅም እና አጫጭር ኳሶቹ የሚጥር ሲሆን በመስመሮች መካከል እየተገኘ የመጨረሻ ኳሶችን ለፈጣኖቹ አጥቂዎች ለማድረስ ሲሞክርም ይታያል። በጨዋታውም የማሸነፊያ ጎል ሀብታሙ እንዲያስቆጥር አመቻችቶ አቀብሏል።

ሽመክት ጉግሳ – ፋሲል ከነማ

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ወረድ ያለ ብቃት ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሽመክት በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ውድድር ማገባደጃ ላይ ድንቅ የጨዋታ ቀን በማሳለፍ የዓመቱ አንደኛ እና ሁለተኛ ጎሉን አስመዝግቧል። ዘንድሮ በቡድኑ 3ኛው ብዙ ደቂቃዎችን የተጫወተው ተጫዋች የሆነው ሽመክት የሚታወቅበትን ፍጥነት፣ ፍላጎት፣ ታታሪነት እና ስልነት በሚገባ በማስመልከት የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ሆኖ አምሽቷል።


አጥቂዎች

አዲስ ግደይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከጉልበት ቀዶ ጥገና በኋላ በዘንድሮ የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ መርሐ-ግብር የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው አዲስ የማይረሳው ምሽት አሳልፏል። የጨዋታ ዝግጁነት ክፍተት ሊኖርበት ይችላል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ቡድኑ በጨዋታው ድል እንዲያገኝ ያደረጉ ሁለቱ ጎሎች ላይ ተሳትፏል። በፈጣን ሽግግር ከተቆጠረችው የማሳረጊያ ጎል በተጨማሪ ቡድኑን አቻ ያደረገች እና ወደ ጨዋታው የመለሰች የፍፁም ቅጣት ምት የተገኘችውም በእሱ ላይ በተሰራ ጥፋት ነበር።

ስንታየሁ መንግሥቱ – ወላይታ ድቻ

ወላይታ ድቻ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ቦታን ይዞ የመጀመሪያውን ዙር እንዲያገባድድ የስንታየሁ መኖር ግድ ይላል። የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እንዲሁም ከፍተኛ አሲስት አድራጊ የሆነው ስንታየሁ በወልቂጤው ጨዋታ ሦስት ነጥብ የገዛችውን ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ጀርባውን ለጎል እየሰጠ አጋሮቹን በማጫወት እንዲሁም ሁለተኛ ኳሶችን በማመቻቸት ረገድ የተዋጣለት የማጥቃት መሐከል በመሆን ሲጫወት ተመልክተነዋል።

በረከት ደስታ – ፋሲል ከነማ

ፋሲል ከነማ ካስቆጠራቸው 25 ጎሎች 7ቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረገው በረከት በጨዋታ ሳምንቱ የመጀመሪያ ፍልሚያ የብዙዎችን አድናቆት ያገኘበትን ቀን አሳልፏል። ቀኝ እግሩን የሚጠቀመው በረከት ከግራ መስመር እየተነሳ ወደመሐል በመግባት የሚሞክራቸው ኳስ ለተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች ፈተና እንደሆነም በድሬዳዋው ጨዋታ በጉልህ ተመልክተናል። በጨዋታውም አንድ ጎል እና አሲስት በስሙ አስመዝግቧል።

አሠልጣኝ

ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ያለፉትን ስምንት ጨዋታዎች ያልተሸነፈውን ሲዳማ የሚመሩት አሠልጣኝ ገብረመድህን በሀዲያው ጨዋታ እየተመሩ ነጥቡን ወደ ራሳቸው ያደረጉበት መንገድ አድናቆት የሚያስቸራቸው ነው። እርግጥ በጨዋታ ሳምንቱ የፋሲል ከነማው አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ በቦታው ተፎካካሪ ቢሆኑም አሠልጣኝ ገብረመድህን በእረፍት ቡድናቸውን አሻሽለው ውጤት የገለበጡበት ሂደት የተሻለ ነጥብ አሰጥቷቸው የምርጥ ቡድናችን አሠልጣኝ አድርጓቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ጀማል ጣሰው
አሸናፊ ፊዳ
አምሳሉ ጥላሁን
በኃይሉ ግርማ
ናትናኤል ዘለቀ
ቃልኪዳን ዘላለም
አቡበከር ናስር
ኦኪኪ አፎላቢ