የሊጉ የዓምና እና ዘንድሮ የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች ንፅፅር (ክፍል 1)

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ድምፅ የሆነችው ሶከር ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው ዓመት እና ዘንድሮ የተደረጉ የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎችን ከቁጥሮች ጋር በማመሳከር ንፅፅራዊ ጥንቅር አሰናድታለች።

የዘንድሮ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ጅማሮውን በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በማድረግ የመጀመሪያውን የውድድር ዘመን አጋማሽ በድሬዳዋ ስታዲየም ማገባደዱ ይታወቃል። ዓምና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው የፀጥታ ችግር የትግራይ ክልል ክለቦችን ያላሳተፈው ውድድሩ ክረምት ላይ ከከፍተኛ ሊግ ከየምድባቸው ሁለተኛ የወጡ ክለቦችን ከዋናው ሊግ እርከን የመውረድ ዕጣ ፈንታ አጋጥሟቸው ከነበሩ ሦስት ክለቦች ጋር በማድረግ የማሟያ ውድድር ተከናውኖ በጎደለው ሦስት ቦታ ላይ ተተክቶ ሊጉ በ16 ክለቦች መካከል እየተከናወነ አጋማሹ ላይ ደርሷል። በጎዶሎ የተሳታፊ ቁጥር መከናወኑን ተከትሎ በየጨዋታ ሳምንቱ አራፊ ቡድን እየኖረ ስድስት ስድስት መርሐ-ግብሮችን ያደረገውን ውድድሩ ዘንድሮ በተሟላ ሁኔታ በማከናወን 120 መርሐ-ግብሮችን አገባዷል። ሊጉን በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ሰጥታ ከጨዋታ በፊት፣ ጨዋታ ላይ እና ከጨዋታ በኋላ የተለያዩ መረጃዎችን ስታደርስ የከረመችው ሶከር ኢትዮጵያ የዓምና እና ዘንድሮ የመጀመሪያውን ዙር ውድድርን በማነፃፀር ይህንን ዘገባ አጠናክራለች። እንደገለፅነው በዓምና እና ዘንድሮ ውድድር ላይ የክለቦች እና የጨዋታ ቁጥር አንድ ያለመሆን ጉዳይ ቢኖርም በዋናነት የዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር ውድድር የጨዋታ ሳምንት (15) እንደ መነሻ በመውሰድ ከዓምናው የመጀመሪያ 15 የጨዋታ ሳምንታት ጋር ያሉ ለውጦችን እያነፃፀርን ፅሁፉን አዘጋጅተናል።

ዓምና እስከ 15ኛ የጨዋታ ሳምንት ድረስ በአዲስ አበባ፣ ጅማ እና ባህር ዳር ከተሞች በተደረጉት 90 ጨዋታዎች አጠቃላይ 228 ኳሶች ከመረብ ጋር የተዋሀዱ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ በሀዋሳ እና ድሬዳዋ በተደረጉት 120 ጨዋታዎች 238 ጎሎች ተመዝግበዋል። እንዳልነው ዓምና በየጨዋታ ሳምንቱ 6 መርሐ-ግብሮች ብቻ እየተደረጉ የነበረ መሆኑ ልብ የሚባል ጉዳይ ሲሆን በአጠቃላይ በ30 ጨዋታዎች በላቀው የዘንድሮ ውድድር ግን በ10 ግቦች ብቻ ዕድገት ማሳየቱ በመጠኑ ኳስ የግቡን መስመር የምታልፍበት ንፃሬ እንደቀነሰ ያሳያል። ለማሳያነትም ዓምና በተደረጉት የመጀመሪያ 15 መርሐ-ግብሮች በየጨዋታው በአማካይ 2.53 ጎል የተመዘገበ ሲሆን ዘንድሮ ግን በጨዋታ በአማካይ 1.98 ጎል ብቻ በግብ ብረቶቹ መሐል ተገኝቷል።

የኮቪድ-19 ቫይረስን ስርጭት እና ለውድድር ምቹ የሆነ ሜዳ አለመኖርን ተከትሎ ከዓምና ጀምሮ በተመረጡ ከተሞች ብቻ እየተደረገ የሚገኘው ሊጉ ብዙ አዎንታዊ ጎኖቹ ያሉት ሲሆን በዛሬው ጥንክራችን ግን በዋናነት የተሳታፊ ክለቦችን ብቃት እናነፃፅራለን። በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክለቦቻችን እና ተጫዋቾች ላይ የሚነሳው የወጥነት ችግርም አሁንም በጉልህ እየታየ መገኘቱን ከቁጥሮች ጋር እያስደገፍን ለማቅረብ እንሞክራለን። በዋናነት የወቅቱ የሊጉ ባለ ክብር ፋሲል ከነማ ዘንድሮ ከዓምናው ወርዶ መገኘቱ ደግሞ የሀሳባችን መነሻ ሆኗል። በዚህኛው ክፍል መሰናዶዋችን ከዓምና ዘንድሮ የውጤት መንሸራተት ላይ የተገኙ ክለቦችን እንመለከታለን።

በአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚመራው ፋሲል ከነማ ከሌሎቹ የሊጉ ክለቦች በተለየ በተረጋጋ የቡድን ግንባታ ያለፉትን ሦስት እና አራት ዓመታት የዘለቀ መሆኑ ለውጤታማነቱ ትልቁን ድርሻ ቢወጣም በብዙ ክለቦች የሚከሰተው የቻምፒዮንነት ማግስት ቀውስ በመጠኑ ያገኘው ይመስላል። በክረምቱ የዝውውር መስኮት በአጥቂ እና ተከላካይ ቦታ ብቻ የተጫዋች ግዢ የፈፀመው ስብስቡ ከሙጂብ ቃሲም ሌላ ከሳምንት ሳምንት የሚጠቀምባቸው ወሳኝ ተጫዋቾቹን ባያጣም በአራቱም ክፍሎች መጠነኛ መውረድ አጋጥሞታል። እንደ ቡድን ብቻ ሳይሆን በተጫዋች ረገድም የተከሰተው የብቃት መቀነስ ዓምና በ15 የጨዋታ ሳምንታት ካሳካው 38 ነጥቦች ዘንድሮ በ12 ቀንሶ 26 ብቻ እንዲያገኝ አድርጎታል። በዓምና እና ዘንድሮ የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች የውጤት ንፃሬ ከፍተኛ መዋዠቅ በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆነው ቡድኑ ዋንጫ ባገኘበት ዓመት የመጀመሪያ ዙር ውድድር ብዙ ጨዋታዎችን (12) ያሸነፈ ቢሆንም ዘንድሮ ግን በ7ቱ ብቻ ከተጋጣሚ ቡድኖች ሦስት ነጥብ ወስዷል።

በ15ቱ ጨዋታዎች 15 ግቦችን ያስቆጠረለት ሙጂብ ቃሲምን በኦኪኪ አፎላቢ የተካው ፋሲል ዘንድሮ ከ5 ግብ በላይ ያስቆጠረለት ተጫዋች አለመኖሩ የጎዳው ይመስላል። እርግጥ ከዓምናው በተሻለ ዘንድሮ ጎሎች ላይ የተሳተፉ 9 ተጫዋቾች መኖራቸው የግብ ማስቆጠር ክፍፍሉ ስብጥር እንዳለው ቢጠቁምም ከዓምናው በተቃራኒ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ግብ ሳያስቆጥር መውጣቱ (ዓምና በ15ቱም ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠሩ ልብ ይሏል) እንዲሁም 7 ጨዋታዎች ላይ ከአንድ በላይ አለማስቆጠሩ ምንኛ ጎል ፊት ያለው አልምር ባይነት እንደቀነሰ ያሳያል። ፋሲል አሁንም የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለብ ቢሆንም ይህንን በልበ ሙሉነት እንድንል የሚያስደርገን ካስቆጠራቸው አጠቃላይ ግቦች አብዛኛውን ድርሻ የሚወስደው (56%) በአምስት ጨዋታዎች የተቆጠሩት ጎሎች መሆናቸው ሲታወስ ነው።

ከሊጉ የመጀመሪያ ሦስት ጨዋታዎች ውጪ አንድም ተከታታይ ድል ያላገኘው ፋሲል ከነማ የኋላ መስመሩ ከዓምናው በበለጠ ተጠናክሮ ይመጣል ሲባል ይባስ በ2 የላቀ ግቦችን አስተናግዷል። በተለይ በብሔራዊ ቡድን ተጣማሪ የሆኑት አስቻለው እና ያሬድ በግል ወረድ ያለ ብቃት ላይ መገኘታቸው የኋላ መስመሩ እንደታሰበው የጠበቀ እንዳይሆን ያረገው ይመስላል። ከዚህ ውጪ ዓምና ከመጀመሪያዎቹ 15 ጨዋታዎች በ9ኙ ግቡን ሳያስደፍር (clean sheet) የወጣው የግብ ዘቡ ሚኬል ሳማኬ ዘንድሮ ከተሰለፈባቸው 14 ጨዋታዎች 7ቱ ላይ ባይደፈርም በአንዳንድ ጨዋታዎች የሚያሳየው ደካማ ብቃት ለኋላ መስመሩ አለመጠናከር ምክንያት እንደሆነ ይታሰባል። በ2013 የመጀመሪያው ዙር ውድድር ከሁለተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ድረስ ከተቀመጡ እና በእውነተኛ የዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ከነበሩት ክለቦች ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 15 ነጥቦች 10ሩን አሳክቶ የነበረው ቡድኑ ዘንድሮ በተቃራኒው እስከ ስድስተኛ ደረጃ ከሚገኙት ክለቦች ጋር ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች 5 ነጥብ ብቻ ነው ያገኘው። እርግጥ አሁንም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ቢገኝም ከዓምናው አንፃር ያሳየው የብቃት መውረድ ብዙዎችን አስገርሟል።

ከፋሲል ቀጥሎ በአንፃራዊነት ከዓምና ዘንድሮ ወረድ ያለ ብቃት ላይ የሚገኘው ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ነው። እንደ ፋሲል ከነማ ሁሉ በኮቪድ-19 የተሰረዘውን የውድድር ዓመት ጨምሮ ያለፉትን ሦስት ዓመታት በተመሳሳይ ቅኝት ቡድኑን እየገነባ የሚገኘው ቡና ከ10 ዓመታት በኋላ ወደ አህጉራዊ ውድድር የተመለሰበትን ስኬት ባጣጣመ ማግስት የደረጃ ሰንጠረዡን አካፋይ ቦታ ይዟል። 5 ጨዋታ አሸንፎ በ5ቱ ተረቶ በቀሪዎቹ 5 አቻ የወጣው ስብስቡ በዋናነት ከወገብ በላይ የነበረውን ጥንካሬ ማጣቱ በግልፅ ይታያል። ከምንም በላይ ደግሞ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች 34 ግቦችን በተጋጣሚ መረብ ላይ ማሳረፉ እና ዘንድሮ እጅግ ወርዶ 11 ብቻ ማስቆጠሩ ሲታወስ ጎል ፊት ዓይናፋር እንደሆነ እንረዳለን። እርግጥ ዓምና ‘የአንድ ሰው ቡድን’ ተብሎ ተቀፅላ ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ያንን አንድ ሰው በሚገባ አለማግኘቱ እንደጎዳው ይታመናል።

የካሣዬን ስብስብ በጫንቃው ይዞ የተጫወተው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአንድ ውድድር ዘመን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አቡበከር ናስር እጅግ በሚገርም ሁኔታ ዘንድሮ ቡድኑ በአጠቃላይ ካስቆጠራቸው ጎሎች በ45 በመቶ የሚልቅ ጎል (20) ዓምና በግሉ በ15ቱ ጨዋታዎች ብቻ በስሙ አስመዝግቧል።

ዓምና ከመጀመሪያዎቹ 15 ጨዋታዎች ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በተደረገው መርሐ-ግብር ብቻ ያልተጫወተው አቡበከር ዘንድሮ በመጠኑ ዝቅ ያለ የጨዋታ ጊዜ ማግኘቱ እንደ ዓምናው አላደረገውም ብለን መደምደም ባይቻልም ዘንድሮ በ12 ጨዋታዎች ሜዳ ላይ ግልጋሎት ቢሰጥም በአንዳንድ ጨዋታዎች (በተለይ በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች) ከመስመር እየተነሳ እንዲያጠቃ የሚሰጠው ሚና ከጎል እንዳራቀው ሀሳብ ይነሳል። ይህ ቢሆን አሁንም የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው አቡበከር በክለብ እና ብሔራዊ ቡድን ከተፈጠረበትን የጨዋታ መደራረብ በአግባቡ እስኪያገግም ኃላፊነት የሚጋራለት ሰው እጅግ የሚያስፈልግ ይመስላል። አቡበከር ሊጉን በከፍታ ካገባደደ በኋላ በሴካፋ ውድድር ላይ የአምበልነት ኃላፊነት ጭምር ይዞ መሳተፉ እንዲሁም ያለ በቂ ዕረፍት የዓለም ዋንጫ እና አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎችን ማድረጉ በአካልም ሆነ በአዕምሮ እንዲዳከም ሳያደርገው አልቀረም። የተጫዋቹ የጨዋታ ባህሪ ደግሞ አንድ ቦታ ቆሞ ኳሶችን ከመጠበቅ በሂደቶች ላይ ተሳታፊ መሆንን ፣ ተከላላዮችን በግንኙነቶች ለማሸነፍ መሞከርን እና ወደ ሁለቱ መስመሮች እየወጡ መጫወትን የሚሻ ስለሆነ አድካሚ ነው። ቡና ደግሞ ይህንን ጫና የሚጋራለት ተጫዋች አለማዘጋጀቱ ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓል።

የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያ ቡና ግቦችን ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን የግብ ዕድሎችንም መፍጠር የተሳነው ሲሆን የቡድኑ ሞተር የነበረው ታፈሰ ሰለሞን ብቃት መቀነሱም ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ይመስላል። ከዚህ ውጪ በመስመር ተከላካይነት የተዋጣለት ጊዜን ሲያሳልፍ የነበረው አሥራት ቱንጆ እምብዛም ባልተጫወተበት የመስመር አጥቂ ቦታ መሰለፉ የቡድኑን የፊት መስመር በመጠኑ ዱልዱም አድርጎታል። እርግጥ አሥራት የማጥቃት ባህሪ ያለው እንዲሁም ሁለገብ ተጫዋች ቢሆንም የሚታወቅበትን የፊትዮሽ ሩጫ እና በማጥቃት እንቅስቃሴ ወቅት አደጋ መፍጠር የሚስችለው አደገኛ ቦታ ላይ ለመገኘት የሚያስችል ጊዜ እና ቦታ ከአዲሱ ሚናው አለማግኘቱ በጨዋታዎች ላይ ያለው ተፅዕኖ እንዲቀንስ አድርጎታል።

ኢትዮጵያ ቡና በውጤት ረገድ መንሸራተት ያጋጠመው ቢሆንም ዓምና ሲቸገርበት የነበረውን ግቦችን የማስተናገድ ችግር ማሻሻሉ መረሳት የለበትም። በዚህም በጨዋታ 1.26 ሲያስተናግድ የነበረ ሲሆን አሁን 0.93 ግቦችን በአማካይ አስተናግዶ የመጀመሪያውን ዙር ፈፅሟል። በተጫዋች ደረጃ ምንተስኖት ከበደን ብቻ በቦታው ያጣው ቡድኑ ቴዎድሮስ በቀለ እና ነስረዲን ኃይሉን ቢያመጣም ነስረዲንን በጉዳት ሳይጠቀምበት የቴዎድሮስን ግልጋሎት ብቻ አግኝቷል። ግዙፉ ተከላካይ ዘንድሮ 925 ደቂቃዎችን የተጫወተ ሲሆን በመሐል ተከላካይ ቦታ ብዙ ደቂቃ ከተጫወተው አበበ ጥላሁን እና ወንድሜነህ ደረጄ እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የጨዋታ ዕድል ካገኘው ገዛኸኝ ደሳለኝ ጋር በመሆን የኋላ መስመሩን እንዲሻሻል ያደረገው ይመስላል። በተለይ ቡድኑ በኳስ ምስረታ ወቅት የሚሰሩ የቅብብል ስህተቶችን በማረም በራሱ ጥፋት የሚቆጠሩ ጎሎችን መቀነሱ ትልቅ ነገር ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ቡና ከዓምና ዘንድሮ በተደረጉት የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች የ10 ነጥብ መውረድ ያስመለከተን ሰበታ ከተማ ነው። ያለፉትን ሁለት ዓመታት በአንፃራዊነት ተቀራራቢ የጨዋታ መንገድ የሚከተሉትን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና አብርሃም መብራቱን በመሾም ቡድኑን ለመገንባት ሲጥር የነበረው ሰበታ የዘንድሮ የውድድር ዓመት ከመጀመሩ በፊት ከቀደሙት ሁለት አሠልጣኞች ፍፁም የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱት አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በማምጣት የሦስት ዓመት አዲስ ፕሮጀክት ለመጀመር ያሰበ መስሎ ነበር። ክለቡ ያዋጣኛል ባለው መንገድ ለመጓዝ ማሰቡ ባያስወቅሰውም የቡድን ግንባታውን እንደ አዲስ ለመጀመር መጣሩ ለመንሸራተቱ እንደ ዋነኛ ምክንያት ይወሰዳል። ከለውጦቹ መካከል ዓምና ቡድኑን ካገለገሉ ተጫዋቾች 11ዱ ብቻ እንዲቀጥሉ ተደርጎ 13 አዳዲስ ተጫዋቾች ስብስቡን እንዲቀላቀሉ መደረጉ የሽግግር ወቅቱ አጭር እንዳይሆን ያደረገው ይመስላል። ዘንድሮ በ15 ጨዋታዎች ጥቂት ጨዋታ ያሸነፉ ቡድኖችን ከበላይ ሆኖ የሚመራ ሲሆን ዓምና በተመሳሳይ ጨዋታ ቁጥር 4ቱን በድል አጠናቆ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ዓምና ከተሸነፈው በእጥፍ 8 ጨዋታዎችንም ተረቷል። ከሁሉም በላይ ጠጣር የኋላ መስመር በመገንባት በሚታወቁት አሠልጣኝ ዘላለም እየተመራ በ15 ጨዋታዎች 25 ግቦችን ማስተናገዱ (የመጨረሻዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ጊዜያዊው አሠልጣኝ ብርሃን ነበር የመሩት) ብዙዎችን አስደንቋል።

ከዚሁ ከመከላከል ጋር በተያያዘ እንደጠቀስነው 25 ግቦችን ማስተናገዱ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ጨዋታዎች የመከላከል ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በርከት አድርጎ ወደ ሜዳ በማስገባት ዋነኛ ችግሩን ለመሸሸግ ቢጥርም አልሳካለት ማለቱ አግራሞትን የጫረ ጉዳይ ነበር። ዓምና የነበረው የአሠልጣኝ አብርሃም ቡድን በተመሳሳይ የጨዋታ ቁጥር 18 ግቦችን ማስተናገዱ የሚታወስ ነው። ዋነኛው የሁለቱ ቡድኖች ልዩነት የዓምናው ቡድን ከኳስ ጋር ብዙ ጊዜ ለማሳለፍ የሚጥር እና በኳስ ቁጥጥር የተጋጣሚን ጫናዎች ለመቀነስ የሚያስብ ሲሆን ይሄኛው ቡድን ግን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከኳስ ውጪ በመሆን ጊዜውን እያሳለፈ ግቡን ለመጠበቅ የሚውተረተር ነበር። እንደዚህም ሆኖ ግን ቡድኑ የሊጉን ከፍተኛ ግብ ያሰተናገደ ክለብ ሆኗል። በገለፅነው መሠረት የግል እና የቡድን የአቋቋም ስህተቶች እና የውሳኔ አሰጣጥ ክፍተቶች ከሚታዩበት የራስ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን እንቅስቃሴ በተጨማሪ በተቃራኒ ሳጥን ያለው የወረደ ብቃትም ቡድኑ በመጠኑ እንኳን ቀና እንዳይል አድርጎታል። ያለበትን የግብ ዕዳም እንዳይቀንስ ሆኗል። ሦስት ግቦች ካሉት የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ፍፁም ገብረማርያም በመቀጠል ለቡድኑ ኳስ እና መረብን ያገናኙ ተጫዋቾችን ስንመለከት ሁለተኛው ሳሙኤል ሳሊሶ ሲሆን ተጫዋቹ ካስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች አንዱ በቅጣት ምት እንዲሁም እኩል ሁለት ጎል ያስቆጠረው በረከት ሳሙኤል ደግሞ ሁለቱንም በፍፁም ቅጣት ምት መሆኑን ስናስታውስ በይበልጥ በክፍት ጨዋታ ግብ የማስቆጠር ችግር እንዳለበት እንረዳለን።

በተጨማሪም ቡድኑ ዘንድሮ ከያዛቸው 28 ተጫዋቾች 26ቱን አሰልፎ ያጫወተ ሲሆን ከቀሪዎቹ ሁለቱ አንዱ (ቶማስ ትዕግስቱ) አንድም ጨዋታ በተጠባባቂነት እንኳን አልተያዘም። ሌላኛው (ሀብታሙ ጉልላት) ደግሞ ሁለት ጊዜ ብቻ በተጠባባቂነት ተይዞ ወደ ሜዳ ገብቶ አልተጫወተም። ከሁለቱ ውጪ ያሉት 26ቱም ተጫዋቾች ግን በመጀመሪያ አሰላለፍ እና በተቀያሪነት የጨዋታ ዕድል አግኝተው ተጫውተዋል። ከ26ቱ ተጫዋቾች በሁሉም ጨዋታዎች ላይ የተሳተፈው ብቸኛው ተጫዋች ሳሙኤል ሳሊሶ ነው። ተጫዋቹ ስድስት ጊዜ ተቀይሮ የወጣባቸው ጨዋታዎችን ጨምሮ በድምሩ 1250 ደቂቃዎችን ለቡድኑ ግልጋሎት ሰጥቷል። ከእርሱ በመቀጠል ያለው ተጫዋች እንኳን በ95 ደቂቃዎችን ያነሰ ጊዜ ሜዳ ውስጥ ቆይቷል። ይህ በመግቢያችን እንደገለፅነው ቡድኑ ምን ያህል ሽግግር ላይ እንዳለ እና ወጥ ቋሚ ተሰላፊ እንኳን እንደሌለው ያሳያል።

እንዳልነው የተጫዋቾች መተካካት ቡድኑን በእርግጥ አድክሞታል። ግን ደግሞ የቀደመው ቡድን የነበረው የተጫዋቾች ጥራት በግልፅ ከዚህኛው ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑ ለውጤቱ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን መሸሸግ አይገባንም። ከከፍተኛ ሊግ ክለቦች የመጡ (ለከፍተኛ ሊግ ብቻ የተሰሩ የሚመስሉ እንደ ዘካርያስ ዓይነት )፣ አምና ላለመውረድ ሲጫወቱ ከነበሩ ቡድኖች የመጡ (እንደነ ታፈሰ ሰርካ) እንዲሁም አዲስ የመጡት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችም ቢሆኑ በቀደመ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያልሆኑ መሆኑ (እነ በረከት እና በኃይሉ)፣ እንደ አክሊሉ እና ፍፁም ዓይነት ለረጅም ጊዜ የፉክክር ጨዋታ ያልተጫወቱ ተጫዋቾች መያዙን ስንመለከት ቡድኑ ግርጌ ላይ መቀመጡ ሊያስገርመን አይገባም።
ከዚህ ውጪ አሠልጣኝ ዘላለም በአዲስ አበባ ከተማ ከተሸነፉ በኋላ በሰጡት የድህረ-ጨዋታ አስተያየት የጠቆሙት የደሞዝ ችግርም የተጫዋቾችን ተነሳሽነት ገድሎት ሊሆን ይችላል።

ከጠቀስናቸው ሦስት ክለቦች በተጨማሪ ሀዲያ ሆሳዕና 9 ፣ ባህር ዳር ከተማ ደግሞ 6 ነጥቦችን ከዓምና ዘንድሮ ቀንሰው ታይተዋል። የአሠልጣኝ ለውጥ ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች በቅደም ተከተል ዓምና ዕኩል 26 ነጥቦችን በመያዝ 5ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ሆነው የመጀመሪያዎቹን 15 ጨዋታዎች ያገባደዱ ሲሆን ዘንድሮ ግን በ17 ነጥቦች 12ኛ እንዲሁም በ20 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሆሳዕና የ2013 የውድድር ዓመትን ሲጀምር አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን አሸንፎ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሆነ ፍንጭ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን የዘንድሮ ቡድን ግን የመጀመሪያዎቹን 6 ጨዋታዎች ድል ማድረግ ሳይችል በመቅረቱ ጉዞው ወደኋላ እንዲል አድርጎታል። ከምንም በላይ ደግሞ ዓምና በተደረጉት የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች የሊጉ ጠንካራው የተከላካይ መስመር ባለቤት በመሆን ጥቂት ግቦችን (9) ብቻ ያስተናገደው ክለቡ ዘንድሮ ለእጥፍ የተጠጋ ጊዜ ግቡን (17) ማስደፈሩ ልዩነቱን እንዳመጣ ይታመናል።

ለሆሳዕና ንፅፅራዊ የውጤት መዋዠቅ ሁለት ምክንያቶችን ሳያነሱ ማለፍ አዳጋች ነው። አስተዳደራዊ አለመረጋጋት እና የተጫዋቾች ለውጥ። ካለፈው ዓመት በሊጉ ከሚገኙ ክለቦች በአስተዳደራዊ ችግር እና ከተጫዋቾች ጋር በነበረ አለመግባባት ስሙ ተደጋግሞ የሚነሳው ክለብ ከሀዲያ ሆሳዕና የበለጠ አይገኝም። አምና በልምድም ሆነ በወቅታዊ አቋም መልካም የሆነ ስብስብ ይዞ ውድድሩን የጀመረው ሆሳዕና የሊጉ 2/3ኛ ጨዋታዎች ከተደረጉ በኋላ በክፍያ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ አመዛኞቹን ተጫዋቾች መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። ይህንን ተከትሎም ቡድኑ አብዛኞቹን ተጫዋቾች ለቆ በአዲስ የመተካት ግዴታ ውስጥ ገብቷል የዘንድሮውን የውድድር ዓመት ጀምሯል።

ባህር ዳር ከተማም እጅግ ተጠብቆ የውድድር ዓመቱን በመጀመር ወረቀት ላይ ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሆነ ብዙዎችን ቢያሳስብም በውጤት ረገድ በተቃራኒ ጎዳና ተጉዞ ዙሩን አገባዷል። ቡድኑ ወጥ ያልሆነ አቋም በማሳየት በተከታታይ ከሁለት የበለጡ ጨዋታዎችን እንኳን ማሸነፍ ተስኖታል። በተለይ ሊጉን ዘንድሮ ከተቀላቀሉት ሦስቱ ክለቦች በመከላከያ እና አርባምንጭ የደረሰበት ሽንፈት የሚያስተች ነበር። ጥሩ ስብስብ ያለው ሆሳዕና ከዓምናው ዕኩል 13 ግቦችን ቢያስተናግድም በተቃራኒው ከዓምናው የተሻለ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ይዞ በ5 ያነሱ ግቦችን ማስቆጠሩ ለብዙዎች የሚዋጥ አልሆነም። እርግጥ ቡድኑ ጉዳቶች እና ቅጣቶች እንዳሳሱት ቢታወቅም ሁለተኛ ቡድን ለመስራት የሚያስችል የተጫዋች ስብስብ በመያዙ አሁን ካስመዘገበው በላይ ማስመዝገብ ይገባው ነበር።

የቡድኑ መለያ የሆነው ለተከታታይ ዓመታት ወጥነት የጎደለው ቡድንነት ፣ በርካታ የማጥቃት አማካዮችን ቢይዝም ጥሩ የጎል ማስቆጠር አቅም ያላቸው አጥቂዎች ቢኖሩትም የፈጠራም ሆነ የጎል ማስቆጠር ምንጩ ፍፁም ላይ የተንጠላጠለ መሆን ፣ አሰልጣኙን በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ አለማግኘት ፣ ገራገርነት የሚያጠቃው (ውጤት ለማግኘት የሚያፍር እና ቁርጠኛ ያለሆነ) መሆኑ ዋነኛ መሻሻል እንዳያረግ ያደረጉት ምክንያቶች ናቸው።

ይቀጥላል…