የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ የ15 ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመሩ በወሳኙ ጨዋታ መድን ነቀምቴን በመርታት ወደ መሪነት ተሸጋግሯል። ሶዶ ከተማ ከ አቃቂ ቃሊቲ፣ ደቡብ ፖሊስ ከ ጅማ አባቡና ደግሞ በተመሳሳይ አቻ ውጤት አጠናቀዋል፡፡

ተጠባቂው የምደብ ሐ ጨዋታ ረፋድ 4፡00 ላይ ጀምሯል፡፡ በአንድ ነጥብ ተበላልጠው በደረጃ ሰንጠረዡ አንደኛ እና ሁለተኛ ላይ የተቀመጡት ነቀምቴ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን በኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ መሪነት ጨዋታቸውን አድርገው መድኖች 2-0 አሸንፈዋል፡፡ ቀያይ ለባሾቹ ነቀምቶች በተለምዷዊ የጨዋታ መንገዳቸው እና ውጤታማ እየሆኑ በመጡበት ረጃጅም ኳስ ላይ ትኩረታቸው በማድረግ ሜዳ ላይ ተግባራዊ ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን በአንፃሩ የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገዱ ኢትዮጵያ መድን አብዛኛዎቹን የጨዋታ ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ በማድረግ የአንድ ሁለት የቅብብል አጨዋወትን ሲተገብሩ ተስተውሏል፡፡

የረዳት ዳኞች የተዛቡ የውሳኔ አሰጣጦች በበረከቱበት የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ብዙም የግብ አጋጣሚዎችን ባንመለከትም ቡድኖቹ ያደረጉት የሜዳ ላይ ፉክክር ግን ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ረጃጅም ኳስ ላይ ጥገኝነት የታየባቸው ነቀምቶች አጥቂው ኢብሳ በፍቃዱን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን በተለይ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች አድርገዋል፡፡ 9ኛው ደቂቃ ላይ ኢብሳ በፍቃዱ በዚህ የጨዋታ መንገድ ግብ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ የተባለበት ሲሆን በድጋሚ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ የጆርጅ ደስታን አለመኖር ተከትሎ በቋሚነት ወደ ሜዳ የገባሁ ዳንኤል ይስሀቅ ይዞበታል፡፡ መድኖች በቅብብሎሽ የጨዋታ ሂደት በተለየ መልኩ በግራ መስመር በኩል ወደ ኪቲካ ጀማ አድልተው በመጫወት ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት አልተለያቸውም። ኪቲካ ጀማ ግብም አስቆጥሮ የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ውጪ የተባለበት ሲሆን በመልሶ ማጥቃት ሁለት ጊዜ እጅግ አስገራሚ አቋም እያሳየ ከሚገኘው አማካዩ በኃይሉ ኃይለማርያም ያገኘውን ኳስ ኪቲካ ከግብ ትይዩ ሆኖ መጠቀም ያልቻለበት ተጠቃሾቹ ሙከራዎች ናቸው፡፡

ከእረፍት መልስ ጨወታው ሲቀጥል የመድን የበላይነት ሲንፀባረቅ የነቀምቴ ኃይል የቀላቀለበትን አጨዋወት በዋናነት ተመልክተናል፡፡ ወደ ሜዳ ሁለቱ ቡድኖች ከመግባታቸው አስቀድሞ ነቀምቴዎች አምስት ቢጫ ካርድ የተመለከተን ተጫዋች መድኖች በቋሚ አሰላለፍ ተጠቅመዋል በማለት ክስ አቅርበዋል፡፡ ማራኪ በሆነ የጨዋታ ቅርፅ ወደ ሜዳ የገቡት መድኖች ገና በጊዜ ከመልበሻ ክፍል መልስ ጥቃት ወደ መሰንዘር በፍጥነት ተሸጋግረዋል፡፡ 47ኛው ደቂቃ ላይም ኪቲካ ጀማ ከግራ በኩል ያሻገረውን አብዱለጢፍ ሙራድ በግንባር ገጭቶ ያመከናት እና 52ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ አቅሙን በደንብ ሲያሳየን የነበረው በኃይሉ ኃይለማርያም ወደ ግብ ሲያሻግር ኪቲካ በቄንጠኛ ቅልበሳ ሞክሮ በሚያስቆጭ መልኩ ሊወጣበት ችሏል፡፡ በሒደት አጨዋወታቸው ይበልጡኑ ግብ ፍለጋ ላይ ያተኮረ ይመስል የነበሩት መድኖች ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል ከመረብ አገናኝተዋል፡፡ 57ኛ ደቂቃ ላይ በኃይሉ ላይ የነቀምት ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት የግራ መስመር ተከላካዩ ተስፋዬ ታምራት ወደ ግብነት ለውጧት መድንን ወደ መሪነት አሸጋግሯል፡፡

ኃይል የቀላቀለ አጨዋወትን ከረጃጅም ኳሶች ጋር ለመጠቀም የሚጥሩት ነቀምቶች ጥቂት ሙከራን ብቻ በዚህኛው አጋማሽ ማድረግ ችለዋል፡፡ በዚህም ኢብሳ ለቴዎድሮስ መንገሻ ሰጥቶት ብቻውን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያመከናት እና ታምራት ስላስ ከቅጣት ምት የተገኘን ኳስ በግንባር ገጭቶ ግብ ጠባቂ የያዘበት ተጠቃሾቹ ነበሩ፡፡ 63ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳርዛ ከነቀምቱ ተከላካይ ባይሳ የነጠቀውን ኳስ ተጠቅሞ ግብ አስቆጥሮ የመድንን ጎል ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡ መድኖች ከዚህች ግብ በኋላ በሀይከን ድዋሙ ተጨማሪ ጎል ለማከል ቢቃረቡም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡

ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ ተቀይረው የገቡ ሁለት ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግደዋል፡፡ የመድኑ ሳምሶን ደጀኔ እና የነቀምቱ ውብሸት ስዩም እርስ በእርስ በፈጠሩት ሰጣ ገባ በዕለቱ ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ሰላባ ሆነዋል፡፡ ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት መድንን 2ለ0 አሸናፊ በማድረግ ተደምድሟል፡፡

የሳምንቱ ሁለተኛ መሀር ግብር በሶዶ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ መካከል የተደረገ ነበር ፡፡ ብዙም ለዕይታ ሳቢ ባልነበረው እና የጠሩ አጋጣሚዎችን በርከት ብሎ ማየት ባልቻልንበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከተደረገው ጨዋታ ይልቅ የቀድሞው የደደቢት ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ዳሽን ቢራ ግብ ጠባቂ ቢኒያም ሀብታሙ (ኦሼ) በአንፃራዊነት ጎልቶ የታየበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ማሳያ በመጀመሪያው አጋማሽ 14ኛ ደቂቃ ላይ ፊናንስ ተመስገን በጥሩ ዕይታ ከርቀት መትቶ ቢኒያም በሚገርም ብቃት ያደነበት ተጠቃሿ ሙከራ ሆነናለች፡፡

በረጃጅም ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር በተወሰነ መልኩ ጥረት ያደረጉት ሶዶ ከተማዎች ተጨማሪ ሙከራን በመልሶ ማጥቃት 38ኛው ደቂቃ ላይ በበረከት ገብሬ አማካኝነት አድርገው ድንቅ ሆኖ የዋለው ግብ ጠባቂው ቢኒያም አድኖበታል፡፡አጋማሹ ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩ ጥቃት ወደ መሰንዘር የተሸጋገሩት አቃቂዎች በጭማሪ ደቂቃ ላይ ጉልላት ተሾመ ከሳጥን ውጪ ባስቆጠራት ግሩም ጎል መሪ መሆን ችለዋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ተመሳሳይ የጨዋታ መንገድን የተከተሉት ሁለቱ ቡድኖች በመልሶ ማጥቃት አልፎ አልፎ ደግሞ በረጃጅሙ ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ለመጫወት ታትረዋል፡፡ 54ኛው ደቂቃ ላይ ሶዶ ከተማዎች ያገኙትን የቅጣት ምት የቀድሞው የወላይታ ድቻ ተጫዋች ፊኒያስ ተመስገን ከመረብ አሳርፎ ወደ 1ለ1 አሸጋግሯል፡፡ የመጨረሻዎቹን ሀያ ደቂቃዎች ቡድኖቹ በተሻለ መነቃቃት ለመጫወት በመሞከር ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥሩም ኳስን ከመረብ ማገናኘት ሳይችሉ ጨዋታው 1ለ1 ተደምድሟል፡፡

10፡00 ላይ የዛሬ ሦስተኛ መርሀ ግብር በቀድሞው የፕሪምየር ሊጉ ተካፋዮች ደቡብ ፖሊስ እና ጅማ አባ ቡና መካከል ተከናውኖ የዕለቱ መርሀግብር ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ብርቱ የሆነ የሜዳ ላይ ፉክክር በታየበት የቢጫ እና ሰማያዊ ለባሾቹ ጨዋታ ገና በጊዜ ጎልን አስመልክቶናል፡፡ 5ኛ ደቂቃ በረጅሙ ከተከላካይ ወደ አጥቂ ስፍራ የተጣለን ረጅም ኳስ የቀድሞው የአባጅፋር አጥቂ ብዙአየው እንዳሻው የደቡብ ፖሊስ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂው በቀለ ሽብሩ ስህተት ታክሎበት ማራኪ ግብን በማስቆጠር ክለቡን መሪ አድርጓል፡፡

ከግቧ በኋላ መልስ ለመስጠት በቶሎ ወደ ጨዋታ የገቡት ፖሊሶች በኤርሚያስ ደጀኔ እና ኤልያስ እንድሪያስ ፍፁም ያለቀለትን አጋጣሚ አግኝተው በሚያስቆጭ መልኩ አምክነውታል፡፡ ሆኖም 30ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባቡናው ግብ ጠባቂው ገመቹ በቀለ ከግብ ክልል ውጪ ኳስ በእጅ መንካቱን ተከትሎ በቀጥታ ቀይ ካርድ በመውጣቱ ግብ ጠባቂው በነካበት ቦታ ላይ የተሰጠውን የቅጣት ምት ብሩክ ዳንኤል በቀጥታ መትቶ ወደ ጎልነት በመለወጥ ፖሊስን አቻ አድርጓል፡፡

ከእረፍት ሲመለሱ ጨዋታው ቀጥሎ የተለየ ብልጫን ደቡብ ፖሊሶች ይወስዳሉ ተብሎ ቢጠበቅም በጎዶሎ ሲጫወቱ የነበሩት ጅማ አባጅፋሮች ብርቱ ፉክክርን አድርገዋል፡፡ ቡድኖቹ ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ የጣሩ ሲሆን በተለይ ደቡብ ፖሊሶች የመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ላይ ጫናን በማሳደር በተጋጣሚያቸው ላይ በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ማሸነፍ ሳይችሉ ጨዋታው 1ለ1 ተጠናቋል፡፡ ከጨወታው መጠናቀቅ በኋላ የደቡብ ፖሊስ አጥቂ ምንተስኖት ታምሬ ባሳየው ያልተገባ ባህሪ በቀይ ካርድ በእለቱ ዋና ዳኛ ተወግዷል፡፡