ከፍተኛ ሊግ | ቤንች ማጂ ቡና ሳይገመት በፕሪምየር ሊጉ መንገድ ላይ ተገኝቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዓመት ሊጠናቀቅ የቀሩት የ3 ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ ናቸው። ከየምድቡ አንድ ቡድን ብቻ በሚያልፍበት በዚህ ውድድር ላይ ከሦስቱ ምድቦች ዕድሉ ያላቸው ስምንት ቡድኖች አጠቃላይ የውድድር ዓመት ጉዞ እና ቀጣይ ተስፋዎችን በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ ተመርኩዘን በዚህ መልኩ ዳሰናቸዋል። በዚህ ፅሁፍም የምድብ ለ ተፎካካሪ የሆነው ቤንች ማጂ ቡናን እንመለከታለን።

[የፅሁፍ ቅደም ተከተሉ ቀጣይ ጨዋታዎችን የሚያደርጉበት ወቅትን ታሳቢ ያደረገ ነው]

ደረጃ፡ በ26 ነጥቦች 3ኛ (ከመሪው ለገጣፎ ለገዳዲ በሦስት ነጥቦች ዝቅ ብሏል)

የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች

16ኛ ሳምንት፡ ከ ቡታጅራ ከተማ
17ኛ ሳምንት፡ ከ ካፋ ቡና
18ኛ ሳምንት፡ ከ ኮልፌ ቀራኒዮ

የቤንች ማጂ የከፍተኛ ሊግ ታሪክ የሚጀምረው ከ2010 ጀምሮ ነው። በቀደመው ዓመት ምድቡን በበላይነት በማጠናቀቅ ከአንደኛ ሊጉ ወደ ከፍተኛ ሊጉ የተቀላቀለው ቤንች ማጂ ቡና በአንደኛ ሊጉ ይጠቀምት የነበረውን ሚዛን አማን ከተማ ስያሜ ሲቀይር በአደረጃጀትም ሆነ በቡድን ግንባታ መልክ የመያዝ ሙከራን የጀመረው ሊጉን በተቀላቀለበት ዓመት ነበር። ቡድኑ በተከታታይ ዓመታት ተፎካካሪ ቡድን ባይሆንም በሊጉ ተሳታፊነቱን አስጠብቆ ቆይቷል።

ዐምና የምድብ ለ ፉክክርን በበላይነት ከተወጣው አዲስ አበባ ከተማ በ27 ነጥቦች ዝቅ ብሎ 7ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ቤንች ማጂ ቡና ከሊግ ታሪኩ አንፃር ዘንድሮም ከተሳትፎ የዘለለ ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ፉክክር ውስጥ ይገባል ብለው የጠበቁ ጥቂቶች ነበሩ። እንኳን ውድድሩ ሳይጀመር ውድድሩ እየገፋ በሄደበት ወቅት እንኳን ኋላ የቀረው ቤንች ማጂ ቡናን ጉዳዬ ያለው አልነበረም። ሆኖም በቅፅበት ነገሮች በሚለዋወጡበት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ያልተገመተው ቤንች ማጂ ቡና አሁን ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ዕድል ካላቸው ክለቦች ተርታ ተሰልፏል።

ባለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ ቡድኑን በተቀላቀሉት አሰልጣኝ አረጋዊ ወንድሙ እየተመራ ከ11 በላይ ተጫዋቾችን በማስፈረም የውድድር ዓመቱን የጀመረው ቤንች ማጂ ቡና አሁን እየተፎካከረው ከሚገኘው ቡራዩ ከተማ ጋር 1-1 በመለያየት ነበር የጀመረው። በመቀጠል በተደረጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ ፣ መሸነፍ እና አቻ መውጣትን እያፈራረቀ የተጓዘው ክለቡ አንደኛውን ዙር ያጠናቀቀው ከመሪው ቡራዩ ከተማ በ9 ነጥቦች ርቆ 12 ነጥቦች ብቻ በመያዝ ነበር።

የአንደኛ ዙር ድክመትን አሻሽሎ ለሁለተኛው ዙር በመቅረብ ረገድ ዘንድሮ የቤንች ማጂን ያህል የተሳካላቸው ጥቂቶች ናቸው። የክለቡ የመጀመርያ እርምጃ የሆነውም አሰልጣኝ መሐመድ ኑር ንማን በአሰልጣኝነት መሾም ነበር። በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ እጅግ የተዋጣ ሥራ በመስራት በትንሽ በጀት ክለቡን ለፕሪምየር ሊግ ለማብቃት ከጫፍ ደርሰው የነበሩት ወጣቱ አሰልጣኝ መሐመድኑር ንማ በእርግጥም የቤንች ማጂ መሻሻል ምስጢር ሆነዋል። መሪው ቡራዩን 1-0 በማሸነፍ ሥራቸውን የጀመሩት ” አቦሎቹ ” በአሰልጣኙ መሪነት ከስድስት ጨዋታ አራቱን በድል በመወጣት ሁለቱን አቻ ተለያይተው ማግኘት ከሚገባቸው 18 ነጥቦች 14 በማሳካት ከወዲሁ በአንደኛ ዙር የሰበሰቡትን ነጥብ በልጠው ከመሪውም ያላቸውን ርቀት ወደ 3 ብቻ አጥብበው ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የቡድኑ አሰልጣኝ መሐመድኑር ንማ ቡድኑን በሁለተኛው ዙር ከተረከቡ በኋላ የመጣው ለውጥ ሂደት ምን እንደሚመስል ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት ሀሳብ የሚከተለውን ብለዋል። ” በመጀመሪያ ወደ ቡድኑ እንዳመራሁ የቡድኑ ተጫዋቾች ያላቸውን ነገር ነበር ለመመልከት የሞከርኩት። ከዚያም በመጀመሪያው ዙር ቡድኑ ውጤት ያጣበትን መንገድ የመገምገም እና በቀጣይ በሁለተኛው ዙር ምን መስራት እና ማስተካል ይኖርብኛል የሚለውን ጉዳይ ከአሰልጣኝ ቡድን አባላት እና ከክለቡ አመራሮች ጋር በመነጋገር ወደ ስራ ገብተናል። ጉድለት አለብን ብለን ባመንባቸው ቦታዎች አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን በማዘዋወር እና አንድ አዲስ ወጣት ተጫዋችን ወደ ዋናው ቡድን ስናሳድግ የነበሩትን ተጫዋቾች ደግሞ አዕምሯቸው ላይ ያላቸውን ነገር ሜዳ ላይ ማሳየት ከቻሉ የመሰለፍ ዕድል እንደሚያገኙ በመነጋገር ይህንንም ተጫዋቾች ላይ ዕምነት አሳድረን በተግባር በማሳየት መስራት ችለናል። በዋነኝነት የተጫዋቾች አዕምሮ ላይ መጫወት እንደሚችሉ እና አቅም እንዳላቸው በመንገር ይህን ውጤት ልናመጣ ችለናል። ለውጤታችን ማማርም በእኔ አምነው ወደ ክለቡ ያመጡኝ ስራ አስኪያጁን እና የክለቡን የበላይ ጠባቂ እንዲሁም ሀሳቤን ወደ መሬት በማውረድ ረገድ እየረዱኝ ለሚገኙት ተጫዋቾቼ እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ምስጋናዬን አቀርባለሁ።”

ቤንች ማጂ ቡና በቅርብ ጨዋታዎች ያስመዘገበው ውጤት ”ቀደም ባሉት ጨዋታዎች ላይም ነጥብ ሰብስበን ቢሆን ኖሮ” የሚል ቁጭት በቡድኑ ላይ መፍጠሩ አይቀርም። ”እውነት ነው ክለቡ አካባቢ ያሉ ሰዎች ላይ ይህ የቁጭት ስሜት ይነበባል።” የሚሉት አሰልጣኝ መሐመድ ኑር ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ ያመጡትን ለውጥ በመጥቀስ በጉዞው ደስተኛ ስለመሆናቸው ይናገራሉ። ” ከሰሞኑ ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር ከጣልነው ነጥብ ውጪ ያስመዘገብነው ውጤት አሪፍ የሚባል ነው። በአብዛኛዎቹ ጨዋታዎች ተጋጣሚያችን ላይ ብልጫ ወስደን ተንቀሳቅሰን ውጤት በማግኘታችን ደስተኛ ነኝ።” በማለት በቡድኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ነገ 8፡00 ላይ ቡታጅራ ከተማን የሚገጥምበት ጨዋታን ጨምሮ ሦስት ጨዋታዎች ከፊቱ የሚጠብቁት ቤንች ማጂ ቡና ወደ ፕሪምየር ሊጉ የማደግ እድሉን በራሱ መወሰን የማይችል ቢሆንም የተፎካካሪዎቻቸውን ውጤት በጎን እየተመለከቱ የራሳቸውን የቤት ስራ መስራት አላማቸው መሆኑን የሚገልፁት አሰልጣኝ መሐመድ ” ሦስቱን ጨዋታ ከፈጣሪ ጋር ለማሸነፍ እና ተጋጣሚዎቻችን በሚፈጥሩት ነገር ወደምንፈልገው ውጤት ለመሻገር እየተዘጋጀን እንገኛለን። “በግሌ ሦስቱን ጨዋታዎች እንደምናሸንፍ ይሰማኛል ፤ ከከፋ ቡና ጋር ጎረቤቶቻችንም ስለሆኑ የደርቤ ስሜት ያለው ጨዋታ ይጠብቀናል። መጨረሻ ላይም የቀድሞ ክለቤን ኮልፌ ቀራዮን እንገጥማለን ሁለቱ ጨዋታዎች በተለይ የደርቢነት ስሜት ያላቸው ቢሆኑም እንወጣዋለን ብዬ አምናለሁ። ጨዋታዎቹን በእርግጠኝነት 100% አሸንፈን ለማለፍ የተሻለ ሞራል እና ስሜት ላይ እንገኛለን።” ሲሉ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

በእርግጥ ቡድኑ በለገጣፎ እና ቡራዩ ላይ የተንጠለጠለ የማለፍ እድልን የያዘ ቢሆንም የነገ ረፋድ ጨዋታውን ማሸነፍ 10፡00 ላይ እርስ በእርስ ጨዋታ የሚያደርጉት ሁለቱ ተፎካካሪዎች የሚያስመዘግቡት ውጤት ቤንች ማጂን ተጠቃሚ ሊያደርገው ይችላል። አሰልጣኝ መሐመድም የሁለቱ መገናኘት ” በመጠኑ የሚሰጠን ተጠቃሚነት ሊኖር ይችላል።” ብለው የሚያምኑ ሲሆን” ከውጤት አንፃር አቻ ቢወጡ የተሻለ ሊሆን ይችላል ልትል ትችላለህ። ነገር ግን በእኔ ዕምነት የራስህን የቤት ስራ መወጣት መቻሉ ዋናው ነው። ምክንያቱም እኛ ነጥብ መያዝ ካልቻልን የእነሱ መጣጣል እና አቻ መውጣት ትርጉም አይኖረውም ስለዚህ የራሳችን የቤት ሥራ ተወጥተን በእነሱ የነጥብ መጣጣል የምናገኘውን ዕድል መጠቀም እንችላለን።” በማለት ይበልጥ ትኩረት የሚሰጡት ለራሳቸው ቡድን መሆኑንም ያሰምሩበታል።

ከላይ የተጠቀሱት የቡድኑ ያለፉት ዓመታት የተፎካካሪነት ታሪኮች እና የዘንድሮው አጀማመሩ ብሎም በዚህ ደረጃ የመፎካከር ልምድ የሌለው መሆኑ ጫና በሚበዛባቸው የመጨረሻ ጨዋታዎች ከተጋጣሚዎቹ ልቆ ፕሪምየር ሊጉን ይቀላቀላል ወይ የሚለው ጥያቄ የሚያጭር ቢሆንም አሰልጣኝ መሐመድ ኑር ግን ቡድናቸው በውጫዊ ጫና ከመንገድ ካልቀረ በቀር እንደሚያሳኩት መተማመንን አሳይተዋል። ” አሁን ባለው ሁኔታ የምናሳካው ይመስለኛል ፤ በተቀሩት ጨዋታዎች የመላቀቅ አዝማሚያ ከሌለ እንዲሁም የዳኝነቱ ሂደት በሚፈለገው መልኩ መሄድ የሚችል ከሆነ ከተቀናቃኞቻችን አንፃር በቀሩት መርሐግብሮች መነሻነት እኛ የተሻለ ዕድል አለን። ነገር ግን ከሜዳ ውጪ የሚደረጉ አንዳንድ አዝማሚያዎች ግን ስጋትን ፈጥረውብናል። ሁሉም ክለቦች በዕኩል መታየት ይኖርባቸዋል። ሁሉም ክለቦች ከማህበረሰቡ ላይ ተቆርሶ በሚሰጥ በጀት የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች እንደመሆናቸው ይህ ሁሉ ወጪ የሚወጣው ለፍትሃዊ ፉክክር መሆን አለበት። የአንድ ክልል ክለብ ስትሆን የመላቀቅ አዝማሚያዎች ስለመኖራቸው ጭምጭምታዎችን እየሰማን እንገኛለን። በፌደሬሽኑ በኩል ከሰሞኑ ውይይቶች ስለመደረጋቸው ሰምተናል ጨዋታዎቹ በካሜራ መቀረፅ እንደሚኖርባቸው እና በችሎታ እና በችሎታ ብቻ ቡድኖች ውጤታማ የሚሆኑበት እና አቅማቸውን የሚያሳዩበት መንገድ መፈጠር ይኖርበታል። በመሆኑም ፌደሬሽኑ ሆነ የሚድያ አካላት ለእነዚህ ውድድሮች ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።”

ዐምና ኮልፌ ቀራኒዮ ሳይጠበቅ የምድብ ሐ ላይ ተፎካካሪ ሆኖ በአርባምንጭ ተበልጦ ሁለተኛ በመጨረስ የትግራይ ክልል ክለቦችን አለመሳተፍ ተከትሎ ከፕሪምየር ሊጉ ወርደው በነበሩ ክለቦች እና የከፍተኛ ሊግን በሁለተኝነት ባጠናቀቁ ቡድኖች መካከል በተደረገው የመለያ ጨዋታ ላይ ምርጥ ቡድን ይዞ በመቅረብ ለማለፍ ከጫፍ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል። ያኔ የቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ መሐመድ ኑር ዘንድሮ ደግሞ በቤንች ማጂ ቡናም ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ተገኝተዋል። አሰልጣኙ ግን ሁለቱ አጋጣሚዎች የተለያየ መልክ ያላቸው ስለመሆኑ ይናገራሉ። ” ከአምናው ዘንድሮ የተሻለ ነገር ላይ እንገኛለን። አምና በመጨረሻው ምዕራፍ ፕሪምየር ሊግ የነበሩ ከእኛ የተሻለ ልምድ የነበራቸውን ቡድኖችን ነበር ያገኘነው። ዘንድሮ ግን ከዛ አንፃር የተሻለ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። በተጨማሪም አሁን ላይ ከአምናው የተማርናቸው ነገሮች አሉ። ይህም ተጫዋቾች በዚህ ወቅት እንዴት መያዝ እንዳለብን ተጫዋቾችን እንዴት ማነሳሳት እንደምንችል እና ሌሎች ከአምና ልምዳችን ያገኘናቸው ትምህርቶች ያግዙናል ብዬ አስባለሁ ከፈጣሪ ጋር ዘንድሮ የሚሳካ ይመስለኛል። ” ሲሉም ሁለተኛ ሙከራቸው እንደሚሳካ እምነታቸውን በመግለፅ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።

ወጥ ካልሆነ አቋም ውጤቱን አሻሽሎ ሳይጠበቅ በመስፈንጠር ወደ ተፎካካሪነት የተሸጋገረው ቤንች ማጂ ቡና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ማለፍ ይችል ይሆን ?