የከፍተኛ ሊጉ የምድብ ሀ ወሳኝ ጨዋታዎች የሰዓት ለውጥ ተደረጎባቸዋል

አጓጊ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ የ17ኛ ሳምንት ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ሰዓታቸው ተቀይሯል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥር የሚደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በሦስት ምድቦች ተከፋፍሎ የመጨረሻ ምዕራፍ ውድድር ላይ የሚገኝ ሲሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማለፍ እና ወደ አንደኛ ሊግ ላለመውረድ እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ እየተደረበት ይገኛል። ባህር ዳር ላይ የሚደረገው የምድብ ሀ ጨዋታም በ17ኛ ሳምንት ወሳኝ መርሐ-ግብሮች ይስተናገዱበታል። ከአምስቱ መርሐ-ግብሮች መካከል ደግሞ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ጌዲኦ ዲላ እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ገላን ከተማ የሚደርጉት ጨዋታ በዕኩል ሰዓት በተለያየ ሜዳ እንዲከናወን መወሰኑን አውቀናል።

ጌዲኦ ዲላ እና ገላን ከተማ ከወራጅ ቀጠናው ለማምለጥ እንዲሁም ደግሞ ንግድ ባንክ እና ኤሌክትሪክ ወደ ዋናው የሊግ እርከን ለማደግ የሚደርጉት ፍጥጫ እጅግ አጓጊ ነው። አንዱ መርሐ-ግብር አንደኛው ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር በሚል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ገላን ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፖሊ ካምፓስ ሜዳ እንዲሁም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ጌዲኦ ዲላ በአፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም በተመሳሳይ 4:00 ሰዓት እንዲደረጉ አወዳዳሪው አካል በዕጣ ሜዳውን ለይቷል።