ኢትዮጵያ ቡና የመለያ ትውውቅ እና የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ሊፈፅም ነው

ከስፖንሰርሺፕ ጋር በተያያዘ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በቀጣይ ሳምንት የተለያዩ ስምምነቶችን ሊፈፅም ነው።

ኢትዮጵያ ቡና የፋይናንስ አቅሙን ለማጠናከር ባለፉት ሁለት ዓመታት ከቤቲካ ፣ ከቡና ኢንተናሽናል ባንክ ፣ ከሀበሻ ቢራ እና ከሀ እስከ ፐ ጋር የተለያዩ የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶችን መፈፀሙ ይታወሳል። በቀጣይ ሳምንት ደግሞ በተከታታይ ቀናት የክለቡ አዲስ መለያ ትውውቅ እና ከአንድ ተቋም ጋር የሚደረግ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ይፈፅማል ተብሎ ይጠበቃል።

የመጀመርያው ማክሰኞ በ09:00 ላይ በሳፋሪ ሆቴል የተዘጋጀ መድረክ ነው። በመድረኩ ኢትዮጵያ ቡና ከሀ እስከ ፐ ጋር አስቀድሞ በገባው ስምምነት መሠረት ክለቡ በቀጣይ ውድድር የሚያደርጋቸውን ከውጭ ሀገር ተመርተው የመጡ መለያዎችን ያስተዋወቃል። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ቡና ለረጅም ዓመታት ከሜዳው ውጪ እና በሜዳው ሲጫወት ይጠቀምበት ከነበረው ቡኒ እና ቢጫ መለያው በተጨማሪ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስተኛ አዲስ መለያ የሚያስተዋውቅ እንደሆነም ስምተናል።

በማስከተል በዕለተ ረቡዕ ረፋድ 03:30 ላይ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀ መድረክ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ለዓመታት የሚቆይ ለጊዜው የተቋሙ ስም ካልተገለፀ ድርጅት ጋር የመለያ ላይ ስፖንሰርሺፕ ስምምነት በይፋ የሚፈፅም ይሆናል። ክለቡን ወደ ሌላ ምዕራፍ ያሻግራሉ ተብለው በታመነባቸው በእነዚህ ሁለት ዝግጅቶች ላይ የክለቡ አመራሮች ዝርዝር መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።