የኢትዮጵያ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች የሙያ ማኅበር የምክክር መድረክ አከናወነ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]


በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች የሙያ ማኅበር የምክክር መድረክ ከአዲስ አበባ 78 ኪሎ ሜትሮችን ርቆ በሚገኘው አዳማ ከተማ አከናውኗል።

2009 ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች የሙያ ማኅበር በዛሬው ዕለት የጠቅላላ ጉባኤው አባላት በተገኙበት የምክክር መድረክ አዳማ ላይ አድርጓል። ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ በማፊ ሬስቶራንት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገው የምክክር መድረክ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እና የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው በክብር እንግድነት ተገኝተው በማኅበሩ በኩል የተነሱ ጥያቄዎችን ምላሽ ሰጥተዋል።

በቅድሚያም አቶ ባህሩ “ዳኞቻችን አቅማቸውን አጎልብተው ሜዳ ላይ እንዲገኙ እንፈልጋለን። በዳኞች ውስጥ አለ የሚባለውን መከፋፈል ማፅዳት ይገባል። ከዚህ ውጪ በየክልሎቹ ተወርዶ ሌሎች ዳኛ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች እንዲያበቁ ሁላችንም መጣር አለብን።” ብለዋል። በማስከተል ከዳኞች ክፍያ እና ከአደጋ ኢንሹራንስ ጋር በተያያዘ ማኅበሩ ያቀረበውን ጥያቄ በሚከተለው መልኩ መልሰውታል።

“ከክፍያ ጋር በተያያዘ መዘግየቶች የሚፈጠሩት ከፋይናንስ እና ከውድድሩ ቅርፅ ጋር ተያይዞ ሪፖርቶች በቶሎ ስለማይደርሱ ነው። በዋናነት ከአንደኛ ሊግ ጋር ተያይዞ ክፍያው እንደዘገየ እናውቃለን። ግን አሁን ክፍያው የባንክ ሂደት ላይ እንዳለ አውቃለው። ከኢንሹራንስ ጋር ተያይዞ የተነሳውን ጥያቄም ልክ ነው። ግን በምን አይነት መንገድ ነው የሚሆነው የሚለውን ለፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅርበን ምላሽ እንዲሰጥ እናደርጋለን።” በማለት መልሰዋል። ከመድረኩ የቀረቡት ሁለት አይነት ጥያቄዎች በአጭሩ ምላሽ ካገኙ በኋላ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ለዳኞች እንዴት ሽፋን መሰጠት አለበት፣ የክፍያ ጉዳይ በምን መልኩ መፈፀም ይገባዋል፣ ዳኞችን የማብቃት ስልጠናን እንዴት ይከወን፣ ዳኞች ላይ እየተላለፈ ያለው ውሳኔ በምን መልኩ ይታያል የሚለውን እና ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ጋር ስላለ ግንኙነት በተመለከተ ጥያቄዎች ቀርበው ሁለቱ አካላት ምላሾችን ሰጥተዋል።

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ጋር ስላለ ግንኙነት…?

“ውድድሩ (የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ) እውነት ነው ከእጃችን ወጥቷል። ክለቦች የራሳቸውን ውድድር እንዲመሩ አድርገናል። ነገርግን የዳኝነት አገልግሎቱን እኛ ነው የምንሰጠው። እኛ የማንክደው ነገር ውስንነት አለብን። ግን መነሳት ያለበት ከእኛ የሚመደቡ ዳኞች ናቸው ወይስ ከአክሲዮን ማኅበሩ የሚመደቡ ታዛቢዎች ናቸው ልዩነቶችን የሚያመጡት የሚለው ነው። በቀጣይም እኛ የዳኝነት ጥራቱን መጠበቅ እንዳለብን በማመን ሥራዎችን እንሰራለን።

“የተወሰኑ የጨዋታ ታዛቢዎች ለብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ እና ለፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የሚልኩት ሪፖርት የተለያየ ነው። በዚህ መሐል የሆነ አካልን ለማስደሰት በሚደረግ ጉዞ ዳኞቻችንን እየተጎዱ ነው። ይህንን የሚያደርጉት ሁሉም ሳይሆኑ አንዳንዶቹ ኮሚሽነሮች ናቸው ነገ እንዲመደቡ እና የሆነን አካል ለማስደሰት ለእኛ እና ለአክሲዮን ማኅበሩ የተለያየ ሪፖርት የሚያቀርቡት። ይህ ትልቅ ክፍተት ነው። ምናልባት አሰሰሮች ቢኖሩ ጥሩ ነው። እኛም ግን ያለብንን ነገር እናስተካክላለን።” አቶ ባህሩ ጥላሁን

“በሌሎች ሀገሮችም ሊግ በክለቦች ይመራል። ፊፋ ባስቀመጠው መሰረት ደግሞ የዳኞች ምደባን በተመለከተ ፌዴሬሽኑ ነው የሚሰራለው። ካምፓኒው በራሳቸው ማረግ ፍላጎት ነበራቸው ግን ይህ አይቻልም። በአንዳንድ ሀገራት የዳኞች ማኅበር በዳኞች ኮሚቴ ቦታ አለው።” አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው

ከዳኞች ክፍያ ጋር በተያያዘ…?
“የውሎ አበል አይዘገይም። የሚዘገየው የሙያ አበል ነው። ይህም ቢሆን መዘግየት የለበትም። እኛ ራሳችን ጋር ያለውን ክፍተት ለማሻሻል እንሞክራለን። ይህ ግን እኛ ጋር ብቻ ሳይሆን ካፍ እና ፊፋም ጋር ክፍያዎች ሊዘገዩ ይችላሉ። ግን እናስተካክላለን።” አቶ ባህቱ ጥላሁን

ከዳኞች ቅጣት ጋር ተያይዞ…?

“ቅጣት የተላለፈባቸው ዳኞችን ቅጣቱ እንዲከለስ እና ቅጣቱ እንዲቀል አድርገናል። ስህተት ቢኖርም በተለያዩ መንገዶች እንዲታረሙ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ከካፍ የመጡ ኢንስትራክተሮች ነግረውናል።” አቶ ባህሩ ጥላሁን

“ባለፈው የመጀመሪያው ዙር ውድድር ግምገማ ላይ የተነሱት ነገሮች የተለዩ ናቸው። ከ5ኛ ክፍል እየመጡ ዳኝነትን እየተቀላቀሉ ነው ተብሏል። በመቶ አለቃ እድሜ ካልሆነ በስተቀር በእኛ እድሜ ከ5ኛ ክፍል ዳኞች መድበን አናውቅም።

“በእያንዳንዱ ጨዋታ ውጤት ቀያሪ ስህተቶች ተፈፀሙ ተብሎ ቅጣቶች መተላለፍ የለባቸውም። የውጤት ልዩነቱ ሰፊ በሆነበት ጨዋታ ላይም ውጤት ቀያሪ ስህተት ፈፅሟል በሚል የፃፈ ኮሚሽነር አለ። አንዳንድ ኮሚሽነሮች በቀጣይ ጨዋታ እንዲመደቡ ወደ አንድ አካል አድልተው ሪፖርት ይፅፋሉ።” አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው

ጥያቄዎች ምላሽ ካገኙ በኋላ የክብር እንግዶቹ ተሸኝተው በማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ትግል ግዛው፣ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሚካኤሌ አርያ እና ዋና ፀሐፊው አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ መሪነት የክልል እና ከተማ አስተዳደር የሙያ ማኅበራት የሥራ ሪፖርት በየተራ እንዲያቀርቡ ተደርጓል።

በማስከተል ኢ/ር ጌታቸው የማነብርሃን ዳኞች እና ኮሚሽነሮችን በተመለከተ መሻሻል ስላለባቸው ጉዳዮች 17 ዋና ዋና ነጥቦችን ገለፃ አድርገው ሰፊ ጥናት ከተጠና በኋላ ለሚመለከተው አካል በቀጣዩ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። በመጨረሻም የማኅበሩ የሥራ-አስፈፃሚ አባላት ሀሳቦችን ከመድረክ ማንሸራሸር ይዘዋል። በዋናነትም ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ሚካኤሌ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በበላይነት የሚመራው አክሲዮን ማኅበር የመጀመሪያውን ዙር ውድድር በሚገመግምበት ወቅት ለማኅበሩ ጥሪ አለማቅረቡን ሲኮንኑ ተደምጠዋል። በመድረኩ ለደጋፊ ማኅበራት ጥሪ መቅረቡ ጥሩ ሆኖ ሳለ በጨዋታዎቹ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ዳኞች የሚገኙበት የዳኞች ማኅበር አለመጠራቱ ይበልጥ እንዳናደዳቸው ስሜታዊ ሆነው ሲናገሩ አስተውለናል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም የዳኞችን ችግር ለማወቅ በየክልሉ የሚገኙ ዳኞችን ወርዶ ማነጋገር እና ሁሉን አቀፍ ምክክር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

በመጨረሻም ዋና ፕሬዝዳንቱ አቶ ትግል ዳኞች የሚያነሱትን የትጥቅ ችግር ለመፍታት ከግዙፉ ሀገር በቀል ተቋም ጎፈሬ ጋር ክፍተቱን ለመድፈን ቅድመ ስምምነት እንደተደረገ አመላክተዋል። በዚህም በሁለቱም ፆታዎች በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ፣ አንደኛ ሊግ እንዲሁም የወጣቶች ውድድሮችን የሚያጫውቱ ዳኞች ከ2015 ጀምሮ አንድ አይነት ትጥቅ እንዲያደርጉ ሥራዎች እየተገባደዱ እንደሆነ አመላክተዋል። አያይዘውም ዮናስ ጉተማ ከተባለ ድርጅት ጋርም ስፖንሰር ለማምጣት ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ እና በፕሪምየር ሊጉ የሚያጫውቱ ዳኞች የሚያረጉት ትጥቅ ላይ የአጋር ድርጅቶች አርማ ተደርጎ ገቢ እንዲገኝ ከትላልቅ ተቋማት ጋር ንግግር መጀመሩን ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። መድረኩም ረጅም ውይይቶች ተደርገውበት 10 ሰዓት ሲል ተገባዷል።