አንጋፋው አጥቂ ሲዳማ ቡናን ተቀላቀለ

ሲዳማ ቡና ሳላሀዲን ሰዒድን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ የቅርብ ዓመታት ታሪክ ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱ ተጫዋቾች መካከል ዋነኛው የሆነው አንጋፋው አጥቂ ሳላሀዲን ሰዒድ በዛሬው ዕለት ሲዳማ ቡናን ስለ መቀላቀሉ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ከሙገር ሲሚንቶ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ ረጅም ዓመታትን ያሳለፈው አጥቂው በግብፅ እና በቤልጂየም ክለብ ውስጥ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምርጥ ጊዜያትን አሳልፏል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከተለያየ በኋላ ያለፉትን ስድስት ወራት ያለክለብ አሳልፎ የነበረው ተጫዋቹ ለቀጣዩ አንድ ዓመት የአሰለጣኝ ገብረመድህን ኃይሌውን ክለብ ለማገልገል ተፈራርሟል፡፡

ተጫዋቹ ክለቡን ቢቀላቀልም ሲዳማ ቡና ከቀድሞ ወጌሻው ጋር ተያይዞ የተወሰነበትን ክፍያ ከፍሎ እስኪያጠናቅቅ እገዳ የተጣለበት በመሆኑ ክለቡ ይህን እስኪፈፅም ድረስ የሳላዲን ፊርማ በፌዴሬሽን ተቀባይነት ቢኖረውም ቴሴራው በመያዙ ሜዳ ገብቶ ግልጋሎት መስጠት እንደማይችል ለማወቅ ችለናል።