አዳማ ከተማ ሦስት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች ከከፍተኛ ሊጉ የሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅመዋል፡፡

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛውን ዙር ጨዋታ ከወልቂጤ ከተማ ጋር 1ለ1 በመውጣት የጀመረው አዳማ ከተማ ለቀጣዮቹ ጨዋታዎች ቡድኑን ለማጠናከር የሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር በውሰት ውል ከከፍተኛ ሊጉ መፈፀሙን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

አጥቂው ወሰኑ ዓሊ ከስድስት ወራት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚመልሰውን ዝውውር ፈፅሟል፡፡ በባህርዳር ከተማ በመጫወት በብዙሀኑ ዘንድ የሚታወቀው ይህ ተጫዋች በያዝነው የውድድር አመት መጀመሪያ ላይ የከፍተኛ ሊጉን ክለብ ቡታጅራ ከተማን ተቀላቅሎ አንደኛውን ዙር የተጫወተ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ በንግድ ባንክ አሳልፎ የአመቱ ሦስተኛ ክለቡን ከቀድሞው አሰልጣኙ ፋሲል ተካልኝ ጋር ለማሳለፍ አዳማ ደርሷል።

ፀጋአብ ዮሴፍም ዳግም ወደ ሊጉ ብቅ ብሏል፡፡ ከሀዋሳ ከተማ ታዳጊ ቡድን ከተገኘ በኋላ በዋናው ቡድን እንዲሁም በፋሲል ከነማም ጭምር ተጫውቶ ያሳለፈው የመሀል ሜዳው አማካይ በሀምበሪቾ ዱራሜ እንዲሁም የዘንድሮውን የውድድር አመት በስልጤ ወራቤ በከፍተኛ ሊጉ ሲጫወት አሳልፎ ከሦስት አመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሷል፡፡

ውብሸት ጭላሎ ደግሞ ወደ ልጅነት ክለቡ የተመለሰበትን ዝውውር አገባዷል፡፡ ከዚህ ቀደም በአሰልጣኝ ዳዊት ታደለ በሚሰለጥነው የአዳማ ተስፋ ቡድን ተጫዋች የነበረው እና ዘንድሮም ከአሰልጣኙ ጋር በገላን ከተማ ቆይታን ማድረግ የቻለው ግብ ጠባቂው አዳማ ከተማን በውሰት የተቀላቀለው ሦስተኛው ተጫዋች ሆኗል፡፡