የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

ፕሪሚየር ሊጉ ከዕረፍት ተመልሷል ፤ በ16ኛ የጨዋታ ሳምንት የተመለከናቸው ትኩረት የሳቡ ክለብ ነክ ጉዳዩችን በመጀመሪያው ድህረ ፅሁፋችን ተዳሰዋል።

👉 ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቆመበት ቀጥሏል

የመጀመሪያውን ዙር በመሪነት ያጠናቀቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛው ዙር ጅማሮም ሰበታ ከተማን በመርታት መሪነቱን ማስቀጠል ችሏል።

እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ሽንፈት ያላስተናገደው ጊዮርጊስ በ34 ነጥብ ሊጉን እየመራ የሚገኝ ሲሆን በደጋፊዎችም ሆነ በቡድኑ አባላት ላይ የሚታየው የራስ መተማመን ስሜት ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ያለው ቁርጠኝነት ማሳያ ነው። ለወትሮው በጨዋታ ዕለት በስታዲየም ብዙም የማንመለከታቸው የክለቡ የበላይ ጠባቂ የሆኑት አቶ አብነት ገ/መስቀልም ክለቡ በተጓዘበት ሁሉ እየተጓዙ ቡድናቸውን እያበረታቱ ይገኛሉ። ይህም ከላይ ለጠቀስነው በክለቡ ሰዎች ዘንድ ላለው ቁርጠኝነት ዓይነተኛ መገለጫ ነው።

ከዚህም ባለፈ በቀደመ ብቃታቸው ሲመጡ ብዙ የተጠበቀባቸው ነገርግን በተለያዩ ምክንያቶች ቡድኑን በሚፈለገው ደረጃ ለማገልገል ተቸግረው የነበሩ ተጫዋቾች አሁን ላይ ግን ወደ ቀደመው ብቃታቸው የመመለስ ፍንጭን እያሳዩ ይገኛሉ። ለአብነትም በጉዳት ተቸግሮ የነበረው አዲስ ግደይ በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር መቻሉ ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በጨዋታዎች ተፅዕኖ በሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች ላይ ይበልጥ ተሳታፊ እየሆነ መምጣቱ ፣ የቡድኑ አምበል የሆነው ሀይደር ሸረፋ ወደ ቀደመ ብቃቱ የመመለሱ ጉዳይ በቀጣይ ቡድኑ ለሚያደርገው ጉዞ ከፍ ያለ ድርሻን ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአጨዋወት አንፃርም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥተኝነት ጨምሮ ጨዋታዎችን እያሸነፈ ከመምጣቱ ባሻገር ሁለቱንም አጋማሾች በተለየ ጉልበት የሚጀምርበት አኳኋን እየጠቀመው ይገኛል። በተለይም እንደዚህ ሳምንቱ ተጋጣሚው ሰበታ ከተማ ኳስ መስርተው በሂደት ለማጥቃት የሚያስቡ ቡድኖችን ሲያገኝ በጨዋታው ቀዳሚ ደቂቃዎች የሚሰነዝራቸው ፈጣን ጥቃቶች ባላጋራዎቹ ኋላቸውን ሳያዘጋጁ ተደጋጋሚ ዕድሎችን ሲፈጥርለት በጥሩ አጨራረስ ታጅበው ጎሎችን ሲያመጡለትም እየተስተዋለ ይገኛል።

በሚቀጥለው ሳምንት በተጠባቂው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን የሚገጥመው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁሉም ረገድ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከተከታዩ ወላይታ ድቻ ያለውን የሦስት ነጥብ ልዩነት አሁንም አስጠብቆ ቀጥሏል።

👉 ሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ መሪውን መከተላቸውን ቀጥለዋል

ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሦስት እና አራት ነጥብ ልዩነት 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ጨዋታቸውን በድል በመወጣት መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል።

በጨዋታ ሳምንቱ ጅማሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰበታ ከተማን ከረታበት ጨዋታ ውጪ በመሸናነፍ የተጠናቀቁ ጨዋታዎች በተራበው የጨዋታ ሳምንት በመጨረሻው የጨዋታ ዕለት ድሬዳዋ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋርን የገጠሙት ቡድኖቹ ወላይታ ድቻ በቃልኪዳን ዘላለም ግብ ድሬን ሲረታ ሀዋሳ በበኩሉ በብሩክ በየነ እና ተባረክ ሄፋሞ ግቦች ጅማን በማሸነፍ ሁለቱም በሁለተኛው ዙር ተፎካካሪ ሆነው እንደሚቀጥሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ በነጥብ ስብስባቸው ላይ ተጨማሪ ሦስት ይደምሩ እንጂ አሁንም በፉክክሩ ለመቀጠል በተለይ በማጥቃቱ ረገድ መሻሻል እንደሚገባቸው የተመለከትንበት የጨዋታ ሳምንት ነበር።

ወላይታ ድቻዎች አለመሸነፍን ቅድሚያ በመስጠት ከፍ ያለ ትኩረትን ለመከላከል የሚሰጥ ነገር ግን የማጥቃት ሀሳቡ ከመከላከሉ ጋር ያልተመጣጠነ ቡድን ሆኖ የተመለከት ነው። በተወሰኑ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሙከራዎችን የሚያደርገው ቡድኑ አብዛኛው የማጥቃት አቅሙ የቆሙ ኳሶች ላይ የተንጠለጠለ ሲሆን ይታያል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በትናንቱ ጨዋታ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ዕድሎች እና የማሸነፊያ ግቡም የያሬድ ዳዊትን የቆሙ ኳሶች የፈለጉ መሆናቸውን ነበር። ከዚህ ባለፈ ግን ወላይታ ድቻ በእጁ የገባውን ውጤት የማስጠበቅ አቅሙ የተጋጣሚውን የማጥቃት ጥረት ምንም በማድረግ እና በትኩረት እስከፍፃሜው በመጓዝ መታጀቡ በመልካምነቱ የሚነሳ ነው።

ሀዋሳ ከተማም በተመሳሳይ ለተጋጣሚው ጅማ አባ ጅፋር ኳሱን ለቆ በመልሶ ማጥቃት የመጫወት ፍላጎት የነበረው ሲሆን በዚህም በሁለተኛው አጋማሽ በተለየም በጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በተሻለ ሁኔታ ዕድሎችን ፈጥሯል። ነገርግን ጅማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫቸውን ተጠቅመው ተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠር ችለው የነበረ ሲሆን በዚህ አጋጣሚ ግብ ማስቆጠር ቢችሉ አጠቃላይ የጨዋታው መንፈስ በተቀየረ ነበር። ይህም ልምምድ ሳያሟላ ለሰነበተው ጅማ በዚህ መጠን ነፃነት መስጠቱ በሀዋሳ በኩል በድክመት የሚነሳ ነበር።

የሆነ ሆኖ ሁለቱ ቡድኖች ተፈላጊውን ድል በማሳካት በጨዋታ ሳምንቱን በርከት ብለው በአዳማ ለተገኙ ደጋፊዎቻቸው ሀሴት የፈጠሩ ሲሆን ይህንን ውጤታማነት ይዞ ለመዝለቅ ግን የማጥቃት አጨዋወታቸውን ይበልጥ ለማሻሻል መትጋት እንዳለባቸው መናገር ይቻላል።

👉 የሜዳ ውጪ ስኬቶቹን ወደ ሜዳ ማምጣት የተቸገረው ኢትዮጵያ ቡና

ከሜዳ ውጪ ባሉ ጉዳዮች በተለይም የፋይናንስ አቅሙን ከማጠናከር አንፃር የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶችን በመፈፀም ረገድ እንደ ክለብ የሚያደርገው ጥረት እየተሳኩለት የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡና ይህን ጠንካራ ጎን ወደ ሜዳ በማውረድ ረገድ ግን ሰፊ ሥራዎች እንደሚጠብቁት እየተመለከትን እንገኛለን። ገና ከወዲሁ ቡድኑ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአስራ ሦስት ነጥቦች ርቆ በሰንጠረዡ አጋማሽ መገኘቱ ብዙሀኑን ደጋፊ ስጋት ውስጥ የከተተ ነው።

ክለቡን በፋይናስ ለማጠናከር መጠነ ሰፊ ሥራዎችን እየሰራ የሚገኘው የክለቡ አመራር በአሁኑ ወቅት በቡድኑ መለያ ላይ የትጥቅ አቅራቢውን ከ”ሀ እስከ ፐ” ሳይጨምር አራት ተቋማትን እያስተዋወቀ ይገኛል ፤ ይህም በሊጉ ከሚገኙ ክለቦች በሙሉ በበርካታ ተቋማት ጋር የመለያ ላይ ስፖንሰርሺፕ ስምምነቶቾን የፈፀመው ክለብ ያደርገዋል።

በመለያው የፊት ለፊት ክፍል ላይ ካለፉት አስር ዓመታት አንስቶ የክለቡ ዋነኛ አጋር የሆነው “ሀበሻ ቢራ” በቅርቡ በታደሰው የአምስት ዓመት ውል ስምምነት መሰረት ለክለቡ በዓመት 18 ሚሊየን ብር የሚያስገኝለት ሲሆን ሌሎቹ የደረት ላይ ስፖንሰር ከሆኑት “ቤቲካ” ጋር ለአምስት ዓመት የሚቆይ ስምምነት ሲፈፅም በዚህም በዓመት 6 ሚሊየን ብር እንዲሁም በቅርቡ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ከክለቡ ጋር አብሮ መስራቱን የቀጠለው “ቡና ባንክ” ስምምነት ደግሞ በዓመት 5 ሚሊየን ብር የሚያስገኝለት ነው።

በቅርቡ በሚደረግ ይፋዊ ሥነ-ስርዓት የሚበሰረው ከ”ራይድ” የትራንስፖርት አገልግሎት የሚገኘውን የገንዘብ መጠን ሳይጨምር ኢትዮጵያ ቡና ከስፖንሰር አድራጊዎች ብቻ 29 ሚሊየን ብር በዓመት የሚያገኝ ይሆናል። ተቋማት ክለቦችን ከመርዳት ባለፈ በምላሹ ምንም አያገኙበትም በሚባለው የሀገራችን እግርኳስ መሰል የገንዘብ መጠን ማሳካት በራሱ የክለቡን አመራሮች በትልቁ የሚያስመሰግን ነው። እርግጥ ከክለቡ ዓመታዊ በጀት አንፃር በስፖንሰርሺፕ የሚሸፈነው ንፃሬው አሁንም ይበልጥ ማደግ የሚገባው ቢሆንም ጅምሩ ግን ይበል የሚያሰኝ ነው።

ይህ ከሜዳ ውጪ ያለ ስኬት እንዳለ ሆኖ ቡድኑ አሁንም ሜዳ ላይ በደጋፊው ጥበቃ ልክ በሚፈለገው ደረጃ ተፎካካሪ ቡድን መሆን አልቻለም። ዘንድሮም ከወዲሁ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ13 ነጥቦች ርቆ በሊጉ በ8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሊጉ በአዲስ መልክ በ1990 ከተጀመረ በኋላ ብቸኛውን ዋንጫ ካነሳ አስራ አንድ ዓመታትን ያስቆጠረው ቡና በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ ዳግም በአፍሪካ ውድድሮች ላይ ተካፋይ ሆኖ እንደመመልከታችን ዘንድሮ ደግሞ የተሻለ ውጤት ያስመዘግባል የሚል ዕምነት በብዙዎች ዘንድ ነበር። ነገር ግን አሁናዊ ውጤቱ ከግምቱ ጋር የተራራቀ እና ደጋፊዎችን የሚያስደስት አልሆነም። ከክረምት አንስቶ ‘ክለቡ አሰልጣኙን በዝውውር ገበያው የሚፈልገውን ተጫዋች እንዲያቆይም ሆነ እንዲያመጣ በቂ ድጋፍ አላደረገለትም’ የሚል ሀሳብ በስፋት ሲነገር ቢቆይም በአጋማሹ የዝውውር ገበያም ብዙ የተለወጠ ነገር ያለ አይመስልም።

እርግጥ ኢትዮጵያ ቡና በዝውውር መስኮቱ በተወሰነ መልኩ ከሌሎች ክለቦች ለየት ያለ መንገድ እንደመከተል በገበያው ተጫዋቾችን ለማስፈረም በመጠኑም ቢሆን ተግዳሮች ሊገጥመው እንደሚችል ቢገመትም የተሄደው ርቀት ተሂዶ የደጋፊዎቹንም ሆነ የክለቡን ውጥን የሚመጥኑ ተጫዋቾች እንደ “ትልቅ ቡድን” ከተፎካካሪዎቹ ተገዳድሮ ማምጣት አስካልቻለ ድረስ ወደ ሊጉ ክብር ለመጠጋት ቀሪውን መንገድ ለመጓዝ ፈታኝ እንደሚሆንበት የቡድኑ የዘንድሮ እንቅስቃሴ እማኝ ነው።

በመሆኑም ክለብ የሚባለው ተቋም የሜዳም ከሜዳ ውጪም ያሉ ስኬቶቹን በመሰረታዊነት የሚለኩት በዋናው ቡድን ደረጃ በሚመዘገቡ ውጤቶች እንደመሆኑ ክለቡ ስኬቶቹን ሁሉንዓቀፍ ለማድረግ ጠንካራ ሥራዎችን መስራት ይኖርበታል።

👉 ብዙ የተጠበቀበት ነገርግን በሚፈለገው ደረጃ መሆን የተቸገረው ባህር ዳር ከተማ

የውድድር ዘመኑ ሲጀመር በብዙዎች ዘንድ በሰንጠረዡ አናት ለሚደረገው ፉክክር ከታጩ ክለቦች መካከል የነበረው ባህር ዳር ከተማ በውድድሩ እስካሁን ያስመዘገበው ውጤት አመርቂ የሚባል አልሆነም።

የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩበትን ጨምሮ በመጨረሻ አራት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲለያዩ በአንፃሩ ካሸነፏቸው ጨዋታዎች ብዛት (5) በቁጥር በሚስተካከሉ ጨዋታዎች ሽንፈትን በማስተናገድ በ21 ነጥቦች ከመሪው በ13 ነጥቦች ርቀው በ7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በማጥቃት ጨዋታ በተለይም የቡድኑ ሁነኛ አጥቂ የነበረው ኦሲ ማውሊ መጎዳትን ተከትሎ አጠቃላይ የቡድኑ የማጥቃት መዋቅር ተፋልሶ የተመለከትን ሲሆን ፍፁም ዓለሙ በግሉ ነገሮችን መፍጠር ካልቻለ ባህር ዳር ምን ያህል እንደሚቸገር እያስዋልን እንገኛለን። በተቃራኒው በመከላከሉ ደግሞ በርከት ያሉ ለጎል ምክንያት የሆኑ ግለሰባዊ ስህተቶች መፈፀማቸውን የቀጠሉ ሲሆን እነዚህ ጉዳዮች ቡድኑ በሰንጠረዡ ሽቅብ ለመጓዙ ማነቆ ሆኖውበታል። በመሆኑም በስብስብ ጥራት ደረጃ የተሻለ የሆነው ባህር ዳር ሁለቱን መሰረታዊ ተግዳሮቶቹን ተሻግሮ በፍጥነት ወደ ውጤታማነት መንገድ የመምጣቱ ነገር በቀጣይ ይጠበቃል።