የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በ16ኛ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች የሦስተኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 ብቻቸውን ቡድን እየመሩ የሚገኙት ብርሃኑ ደበሌ

በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው መሪነት የውድድር ዘመኑን የጀመረው ሰበታ ከተማ በመጀመሪያው ዙር እጅግ ያልተረጋጋ የሚባል የውድድር አጋማሽን አሳልፏል። አሁን ላይ በጊዜያዊ አሰልጣኝ እየሰለጠነ የሚገኘው ቡድኑ ሁለተኛውን ዙር ከበርካታ አስተዳደራዊ ችግሮች ጋር እየተጋለ ዙሩን በሽንፈት ጀምሯል።

ሰበታ በ13ኛ የጨዋታ ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ ያልተጠበቀን የ5-1 ሽንፈትን ማስተናገዱን ተከትሎ ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር መለያየቱን ይታወሳል። በዚህም ምክንያት ከ14ኛው የጨዋታ ሳምንት አንስቶ ምክትላቸው በነበሩት ብርሃኑ ደበሌ እየተመሩ ይገኛሉ። ታድያ የእሳቸውን ሥራ ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ያለ ረዳት አሰልጣኝ እየሰሩ የመገኘታቸው ጉዳይ ነው።

ሌላኛው ቡድኑን በረዳት አሰልጣኝነት ያገለግል የነበረው ኢንስትራክተር ዳንኤል ገ/ማርያም የዋና አሰልጣኙን መልቀቅ ተከትሎ በተመሳሳይ ከክለቡ መለያየቱን ተከትሎ አሰልጣኝ ብርሃኑ ደበሌ ያለረዳት ልምምድ የማሰራቱን ፣ የልምምድ ምልክቶችን የማስቀመጥም ሆነ በጨዋታ ወቅት ቡድን የመምራት እንዲሁም ሌሎች ሥራዎችን ለብቻቸው እየከወኑ ይገኛሉ።

ከአስር ለሚልቁ ዓመታት በክለቡ ውስጥ ከምስረታው አንስቶ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲያገልግሉ የቆዩት አሰልጣኝ ብርሃኑ ደበሌ በበርካታ አስተዳደራዊ ጉዳዮች እየታመሰ የሚገኘውን ቡድን ለአራት ቀናት ብቻ በማዘጋጀት የቅዱስ ጊዮርጊሱን ጨዋታ ቢያደርጉም ሜዳ ላይ ይዘውት የገቡት ቡድን ግን ከቡድኑ አሁናዊ ሁኔታ አንፃር መጥፎ የሚባል ባይሆንም እጅግ አስፈላጊውን ሦስት ነጥብ ማሳካት ሳይችሉ ቀርተዋል።

በጨዋታው አሰልጣኝ ብርሃኑ በከፍተኛ ስሜት ውስጥ ሆነው ቡድናቸውን ሲመሩ የነበረበት እንዲሁም በጣም በበዙ አጋጣሚዎች ስሜታዊ ሆነው ለአሰልጣኞች ከተፈቀደው አካባቢ (Technical Area) ውጪ ርቀው በመሄድ ልጆቻቸውን ለማበረታት ሲጥሩ የተመለከትንበት መንገድ አስገራሚ ነበር።

በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ የድጋፍ መልዕክት ያዘሉ ፅሁፎች በጨዋታው ወቅት ያስመለከቱን አሰልጣኙ ለረጅም ዓመታት የሰሩበትን ክለብ በሊጉ የማቆየት ትልቅ የቤት ስራ ተጥሎባቸዋል። ታድያ ይህን እጅግ ፈታኝ የሚመስለውን የቤት ሥራ ተወጥተው የሚያከብራቸውን ደጋፊ ይክሱ ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 ዒላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎች እና የካሳዬ ዕይታ

ከዚህ ቀደም በነበረው አካሄድ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በጨዋታ ዙርያ የግል ምልከታዎችን ከማስቀመጥ ባለፈ ሀሳብን የሚደግፉ ቁጥራዊ መረጃዎችን ማግኘት እንደ ብርቅ የሚቆጠርበት ዘመን የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነበር። ታድያ ቁጥራዊ መረጃዎች እና የሀገራችን እግርኳስ ተራርቀው ቢቆዩም ምስጋና ለዲኤስቲቪ ይሁንና መሰረታዊ የሆኑ ቁጥራዊ መረጃዎችን በጨዋታ ወቅት እና ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ማግኘት ተችሏል።

በዋነኝነት በተለይም የኳስ ቁጥጥር ድርሻ እና የግብ ሙከራዎች በተመለከተ የሚመዘገቡ ቁጥሮች ከጨዋታ በኋላ በሚኖሩ የሀሳብ ልውውጦች ላይ ማጠንጠኛ ሲሆኑ ተመልክተናል። ለአብነትም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ለአሰልጣኝ ካሳዬ ከቀረቡለት ጥያቄዎች አንዱ ቡድኑ በጨዋታው አንድ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ስለማድረጉ ነበር አሰልጣኙም ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

“ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ የሚባለው በረኛውን ሲመልሰው ነው ምናልባቴ ትርጉም የሌለው ኳስ መተህ በረኛው ቢይዘው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ተብሎ ይመዘገባል ይሄ ለእኔ ትርጉም የለውም። ዒላማውን ጠብቆ ወደ ጎል መቀየር የሚችልም ኳስ መሆን አለበት ምናልባት በረኛው የማይመልሳቸው ለጥቂት ወደ ውጪ የሚወጡ ኳሶችን በተወሰነ መልኩ ቢስተካከሉ ጎል የሚሆኑ ኳሶችም ከግምት ሊገቡ ይገባል ከዚህም መነሻነት ይህኛው ስሌት ለእኔ ብዙም ስሜት አይሰጠኝም።”

“አጠቃላይ ብዙ የግብ ዕድሎችን አልፈጠርንም ግን ይሄ ዒላማውን የጠበቀ ያልጠበቀ የሚለው ጉዳይ አንዳንድ ጊዜ ጎል መሆን የማይችሉ ኳሶችን ወደ ጎል መተህ ዒላማውን የጠበቀ ተብሎ ይመዘገባል ይሄ ብዙ ትርጉም የለውም። እንደ አጠቃላይ ግን ዕይታው ሊቀየር ይገባል ዒላማውን ከመጠበቅ ባለፈ ወደ ጎል የሚቀየር ኳስ ነው ወይ በረኛው በቀላሉ የሚይዘው 50 ኳስ መምታት ይቻላል ይሄ ዒላማውን የጠበቀ ተብሎ ቢቆጠር ብዙ ትርጉም የለውም።”

የካሳዬ አራጌን አስተያየት በሀገራችን መሰል ቁጥራዊ መረጃዎችን በተመለከተ ያለውን የአረዳድ ችግር ለማረም በሚረዳ መልኩ የተቀመጠ ማብራሪያ ነው። በተዘዋዋሪም የቡድኖች የማጥቃት አፈፃፀም የመጨረሻ መዳኛው ግቦች ቢሆኑም ከዛ ባለፈ ግን ጥቅል ሂደቱን ለመረዳት የዓለም እግርኳስ Expected Goal (xG) የሚል በርካታ ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባ ቀመር ጥቅም ላይ ማዋል ጀምሯል። የካሳዬ ሀሳብም በተዘዋዋሪ ይህን የሚያስረዳ ነው።

ይህሞ ቀመር ሙከራ በሚደረግበት ወቅት ሙከራውን በሚያደርገው ተጫዋች ላይ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ያሰደሩበትን ጫና ፣ ከግቡ አፋፍ አንፃር ሙከራው ሲደረግ የነበረው ግልፅነት ፣ የግብ ጠባቂው መነሻ አቋቋም እና መሰል ዝርዝር ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት እያንዳንዱ የግብ ዕድል ከእነዚህ መነሻነት ዋጋ ተሰጥቷቸው ከተመዘኑ በኋላ የጨዋታው ድምር ውጤት ቡድኑ በጨዋታ ስለፈጠራቸው ዕድሎች ጥራት መመዘኛ ሆኖ መቅረብ ከጀመረ አስር ዓመታት ተቆጥረዋል።

በተመሳሳይ ከኳስ ቁጥጥር ጋር ተያይዞም የኳስ ቁጥጥር (Possession) ቁጥር ቅብብሎቹ የትኛው የሜዳ ክፍል ላይ እንደተደረጉ አለመግለፃቸውን ተከትሎ የሚፈጠረውን ብዥታ ለመቅረፍ ፈረንጆቹ Field Tilt የተሰኘ አዲስ ቀመርን አስተዋውቀዋል። ይህም በጨዋታው በሁለቱም የማጥቂያው ሲሶ የተደረጉትን አጠቃላይ ቅብብሎች ውስጥ የሁለቱ ቡድኖች ድርሻን በመቶኛ በማስላት የትኛውም ቡድን የኳስ ቁጥጥሩን ወደ ማጥቂያ ወረዳ አድርሷል ስለሚለው በተወሰነ መልኩ ምላሽ የሚሰጥ ቀመር ነው።

እርግጥ በእኛ ሀገር እግርኳስ ከላይ ስለጠቀስናቸው እንዲሁም ሌሎች መሰል ቁጥሮች ማሰብ አሁን ላይ ቅንጦት ቢመስልም የግብ ሙከራዎች ዒላማቸውን የጠበቁ በመሆን ባለመሆን ላይ የተመሰረቱ ምልከታዎች በራሳቸው አጠቃላይ ምስል ላይሰጡ ስለሚችል በተወሰነ መልኩ በዓውድ መመልከት ካልተቻለ ድምዳሜውን ለስህተት ሊዳርግ ይችላል።

👉 አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ወደ ሥራ ተመልሰዋል

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ክለቦች በረዳትነት እንዲሁም በዋና አሰልጣኝነት ደግሞ በሐረር ቢራ ፣ ዳሽን ቢራ እና ስሁል ሽረ የሰሩት አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ከአንድ ዓመት ለሚልቅ ጊዜ ከሥልጠና ርቀው ቢቆዩም አሁን ላይ ግን ዳግም ወደ ሥራ ተመልሰዋል።

በተለይ የመጨረሻ በነበራቸው የስሁል ሽረ ቆይታ የመውረድ ስጋት ተደቅኖበት የነበረውን ቡድን በፍጥነት ውጤቱን በማሻሻል በሊጉ እንዲቆይ ያስቻሉት አሰልጣኙ አሁን ላይ የተረከቡት ድሬዳዋ ከተማም ተመሳሳይ ስጋት የተደገነበት እንደመሆኑ አሰልጣኙ ይህን ቡድን በማሻሻል በሊጉ የተረጋጋ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ማስቻል ይኖርባቸዋል።

በዝውውር መስኮቱ እስካሁን ሦስት ተጫዋቾች በማስፈረም ቡድኑን እያጠናከሩ የሚገኙት አሰልጣኙ በአዲስ ከተዋቀረው የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ጋር በመሆን በውጤት ረገድ እያሽቆለቆለ የሚገኘውን ቡድን የመታደግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።