ሀድያ ሆሳዕና ሦስት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል

በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመራው ሀድያ ሆሳዕና የሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛውን ዙር ጨዋታ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ በመጋራት የጀመሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ቡድኑን ለማጠናከር ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን በይፋ ወደ ስብስባቸው መቀላቀላቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ግርማ በቀለ በተጫዋችነት ዘመኑ በሀዋሳ ከተማ ቤት አብሮት መጫወት ችሎ ከነበረው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ጋር ያገናኘውን ዝውውር ፈፅሟል፡፡ ከሀዋሳ ከተማ የታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው በተጨማሪነትም በኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ያለፉት አራት ዓመታት በአንፃሩ በሲዳማ ቡና በመጫወት ያሳለፈው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ቀሪ የስድስት ወራት ውል በሲዳማ ቤት ቢኖረውም በስምምነት በመለያየት ሀድያ ሆሳዕና መዳረሻው ሆኗል፡፡

ራምኬል ሎክ ሌላኛው የክለቡ አዲሱ ተጫዋች ሆኗል፡፡ ተጫዋቹ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ፋሲል ከነማ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ወልዋሎ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በአጥቂ ስፍራ ላይ በመጫወት አሳልፏፋ። ባለፈው የውድድር ዓመት በሀምበሪቾ ዱራሜ ጅምሩን ካደረገ በኋላ ወደ አርባምንጭ ተጉዞ ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማሳደግ እስከ አንደኛው የዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ድረስ በአዞዎቹ ቤት አሳልፎ በስምምነት ውል እያለው ከቀናት በፊት በመለያየት ሀድያ ሆሳዕናን መዳረሻው አድርጓል፡፡

አጥቂው ልደቱ ለማም ሌላኛው የቡድኑ አዲሱ ተጫዋች ነው፡፡ በለገጣፎ ለገዳዲ ረጅም ዓመታት ያሳለፈው እና ዘንድሮ ወደ ፕሪምየር ሊግ ክለቡን በማሳደጉ ረገድ ጉልህ ድርሻ ከነበራቸው መሀል የነበረው ይህ ተጫዋች በባህርዳር ከተማ ከዚህ ቀደም መጫወት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ በውሰት ከለገጣፎ ሆሳዕና ደርሷል፡፡

ሀዲያ ሆሳዕና ከቀድሞው አሰልጣኙ አሸናፊ በቀለ ጋር በተያያዘ በዕግድ ላይ ይገኝ የነበረ ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻ ባለጉዳዮቹ ክፍያ እንደተፈፀመላቸው በመግለፃቸው ዛሬ ወይም ነገ ዕግዱ ተነስቶ የሦስቱ ተጫዋቾች ውል በይፋ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል።

ከዚህ በተጨማሪ ክለቡ ነጋሽ ታደሰ የተባለን አጥቂ ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ማሳደጉንም ሰምተናል።