ኢትዮጵያ የሴካፋን ውድድር እንደምታስተናግድ ይፋ ሆነ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በሴካፋ ስር ከሚደረጉ ውድድሮች መካከል አንዱን እንደምታስተናግድ ይፋ ሆኗል።

በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የተዋቀረው ሴካፋ ባለንበት የፈረንጆች ዓመት በስሩ የሚደረጉ 7 ውድድሮችን የሚያስተናግዱ ሀገራትን ከደቂቃዎች በፊት ይፋ አድርጓል። የሴካፋ ዋና ዳይሬክተር አውካ ጌቼዮ በገለፁት መሠረት ባሳለፍነው ወር ውድድሮቹን እናዘጋጅ ያሉ ሀገራት ያቀረቡትን ጥያቄ በትናንትናው ዕለት በዙም ስብሰባ የተመለከተው የሥራ-አስፈፃሚም ውሳኔዎችን ወስኗል።

በውሳኔውም መሠረት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ተደርጎ የሚወሰደውን የዞኑን ውድድር እንደምታስተናግድ ተመላክቷል። ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ዩጋንዳ የዋና የሴቶች የሴካፋ እና የዞኑን የፓን አፍሪካ የማጣሪያ ውድድርን፣ ለረጅም ዓመታት የሴካፋ ውድድሮችን አሰናድታ የማታውቀው ሱዳን ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ፍልሚያን እንዲሁም ታንዛኒያ የሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ፣ የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ውድድር ማጣሪያ እና የሴካፋ ካጋሜ ካፕን እንደሚያዘጋጁ ተመላክቷል።

ሴካፋ ባወጣው መረጃ የውድድር ቀናቱም በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ተጠቁሟል።