ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ17ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት በተደረጉት ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ብቃት አሳይተዋል ያልናቸውን ተጫዋቾች እና ዋና አሰልጣኝ በማካተት ተከታዩን ምርጥ ቡድን አዘጋጅተናል።

አሰላለፍ 4-3-3


ግብ ጠባቂ

ፍሬው ጌታሁን – ድሬዳዋ ከተማ

በ17ኛው የጨዋታ ሳምንት በርካታ ግብ ጠባቂዎች ጥሩ አቋም አሳይተዋል። ሳምሶን አሰፋ ፣ ያሬድ በቀለ ፣ አላዛር ማርቆስ በዚህ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆኑ በጨዋታው ላይ በነበረው የትኩረት ደረጃ ፣ በቁጥር ከሌሎቹ የላቁ ለጎል የቀረቡ ያለቀላቸው ኳሶችን በማዳን እንዲሁም መረቡን ሳያስደፍር በመውጣት ድሬዳዋ ከተማ በሰፊ ጎል ከመሸነፍ ድኖ አንድ ነጥብ እንዲያሳካ ያስቻለው ፍሬው ጌታሁን ምርጫችን ሆኗል።


ተከላካዮች

ሙና በቀለ – አርባምንጭ ከተማ

በመስመር ተከላካይ እና አማካይ ሚና አዞዎቹን እያገለገለ የሚገኘው ሙና ቀጥተኛ ተኮር በሆነው የአሠልጣኝ መሳይ አጨዋወት ዋነኛ መሠረት ነው። አይደክሜው ተጫዋች የሜዳውን ስፋት በመጠቀም ለቡድኑ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ወደ ሳጥን ሲልክ ይታያል። በዚህም ሁለት ጎል የሆኑ ኳሶችን ከመዓዘን ምት እና ከክፍት ጨዋታ ከቀኝ አቅጣጫ አስገኝቶ ቡድኑ አሸናፊ እንዲሆን አድርጓል።

ፍሬዘር ካሣ – ሀዲያ ሆሳዕና

እስካሁን ብዙ ደቂቃ ለቡድኑ ግልጋሎት በመስጠት ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቀላጣፋው ተከላካይ ሀዲያ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ እንዲገኝ በሁለቱም የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ዋጋው ከፍ ያለ አበርክቶ ሰጥቷል። በአየር ላይ ኳስ አጠቃቀሙ ድንቅ የሆነው ፍሬዘር ብቸኛዋን የማሸናፊያ ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ባህር ዳር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲያደርግ የነበረውን የማጥቃት አጨዋወት በመቆጣጠር እና ግቡን ባለማስደፈር የሚደነቅ ተግባር ፈፅሞ ወጥቷል።

ያኩቡ መሀመድ – ሲዳማ ቡና

ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ ካለው ጊት ጋትኩት ጋር የሲዳማን የመሀል ተከላካይ ጥምረት የመሰረተው ያኩቡ ወጥ አቋም በማሳየቱ ገፍቶበታል። ሲዳማ ቡና ግብ ሳያስተናግድ በወጣበት የድሬዳዋው ጨዋታ በወትሮው ከፍ ያለ ትኩረት ላይ የነበረው ጋናዊው ተከላካይ የተጋጣሚን ጥቃቶች በማቋረጥ ኃላፊነቱን ተወጥቷል። ተጫዋቹ በተለይም በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ቀድሞ ይወስናቸው የነበሩ ውሳኔዎች ለድሬዳዋ ከተማ አጥቂዎች ዕድል የሚሰጡ አልነበሩም።

ፀጋዬ አበራ – አርባምንጭ ከተማ

ፀጋዬ በአዲስ አበባው ጨዋታ ወረቀት ላይ በግራ መስመር ቢሰለፍም እንደ አማራጭ የተጋጣሚ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ያለ ከልካይ እየገባ አደገኛ ቦታዎችን ለመጠቀም ሲጥር አስተውለናል። በተለይ ተሻጋሪ እና የቆሙ ኳሶችን ለማሸነፍ የነበረው ጥረት ዋጋ አስገኝቶት የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ጎሎቹን አግኝቷል። ፀጋዬ ቡድኑ ወሳኝ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ በማጥቃቱ ብቻ ሳይሆን በመከላከሉም በከፍተኛ መታተር ወደኋላ እየተመለሰ ድጋፍ ሲያደርግ ነበር።


አማካዮች

አስጨናቂ ፀጋዬ – ጅማ አባ ጅፋር

ከግብ ጠባቂዎች በተለየ በጨዋታ ሳምንቱ ከተከላካዮች መስመር ፊት ባለው ቦታ ላይ በብዙ ርቀት ጎልቶ የወጣ ተጫዋች አልነበረም። በመጨረሻው የጨዋታ ዕለት በጅማ በዚህ ቦታ ላይ የተሰለፈው የቡድኑ አዲስ ተጫዋች ብቃት ግን በርካታ ተጫዋቾችን ለሞከሩት አሰልጣኝ አሸናፊ እፎይታ የሚሰጥ ይመስላል። ከቡድን ጓደኞቹ ጋር በፍጥነት የተግባባው አስጨናቂ የተጋጣሚን ጥቃት በማቋረጡ እና በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ጅማሮ ላይ በመሳተፍ ጥሩ የጨዋታ ዕለት አሳልፏል።

አብዱልከሪም ወርቁ – ወልቂጤ ከተማ

በአምናው ብቃቱ ልክ እየተንቀሳቀሰ ያልነበረው አቡዱልከሪም በፋሲል ከነማው ጨዋታ አሁንም የወልቂጤ እጅግ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን አሳይቷል። መሀል ሜዳ ላይ ከኳስ ጋር ተጫዋቾችን በመቀነስ እና ለአጥቂዎቹ ቅርብ ሆኖ ቅብብሎችን በአግባቡ ሲከውን የነበረው አብዱልከሪም የወልቂጤ ከተማ ጥቃቶች ምንጭ ነበር። በዚህም የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር ባለፈ በሳማኬ የተመለሰው የእሱ ኳስ ለጫላ ጎል መገኘት ምክንያት ነበር።

የአብስራ ተስፋዬ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ በከፍተኛ መታተር ሲጫወት የነበረው የአብስራ ከሁለቱ አማካዮች በተለየ ወደ ተጋጣሚ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ተጠግቶ እንዲጫወት ተደርጎ ነበር። የተሰጠውን ይህንን ሚናም በሚገባ በመወጣት ከኳስ ውጪ የቡና ተጫዋቾችን የኳስ ምስረታ በማጨናገፍ ከኳስ ጋር ደግሞ የመጨረሻ ኳሶችን ለአጥቂ መስመሩ በማድረስ እና ሙከራዎችን በማድረግ የተዋጣለት ነበር።


አጥቂዎች

አቤል ያለው – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣን ጥቃት ፈፃሚ ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አቤል በቡናው ጨዋታ ከኳስ ውጪም ተከላካዮች ላይ ጫና በመፍጠር ኳሶች እንዲባክኑ በማድረጉ በኩል የነበረው አብርክቶ የላቀ ነበር። ከዚህ ባለፈ ቡድኑ በፈጣን ሽግግር ወደ ቡና ሳጥን ሲያመራ ቀጥተኛ ሩጫዎቹ ለተጋጣሚ ከባድ ሆነው ሲውሉ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችውን ጎል ያስቆጠረበትም መንገድ የተጫዋቹን የቴክኒክ ብቃት ያሳየ ነበር።

ቸርነት ጉግሳ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈረሰኞቹ ድንቅ በነበሩበት ጨዋታ ብቻ ሳይሆን በሳምንቱ ደምቆ የታየው ተጫዋች ቸርነት ጉግሳ ነው። እስካሁን ለ800 ደቂቃዎች በተለያዩ ሚናዎች ግልጋሎት የሰጠው ቸርነት በታላቁ የደርቢ ጨዋታ ጠንካራ እና ታጋይ ነበር። ተጫዋቹ በ48ኛው ደቂቃ ድንቅ ግብ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ አቤል የመክፈቻውን ጎል እንዲያገኝ የሚደነቅ ጥረት አድርጓል። ተጫዋቹ የቡናን ተከላካዮች ሲፈትን የነበረበትን ጥረት ታሳቢ በማድረግም በምርጥ ቡድናችን አካተነዋል።

ጫላ ተሺታ – ወልቂጤ ከተማ

ወልቂጤ ፋሲል ከነማ ላይ ያሳካው ድል የቀድሞውን ጫላን አስመልክቶናል። ከኳስ ጋር በሚገናኝባቸው አጋጣሚዎች ፋሲሎችን ሲረብሽ የዋለው ጫላ በቀጥታ ወደ ግብ ሙከራዎችን ለማድረግም ሆነ ቅብብሎችን ለመከውን የነበረው በራስ መተማመን ወልቂጤ ከፊት ለፈጣን ጥቃት የሚሆን በቂ ኃይል እንዳለው የሚጠቁም ነበር። ጫላ በማጥቃት ውስጥ የነበረውን ንቃት በሚያሳይ መልኩ ትክክለኛው ቦታ ላይ በመገኘት ያስቆጠረው ጎልም ለቡድኑ ሙሉ ውጤት መሳካት ወሳኝ ነበር።


አሠልጣኝ

ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በጨዋታ ሳምንቱ በሰፊ ውጤት የተጠናቀቀውን ተጠባቂ መርሐ-ግብር የመሩት አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ምርጥ ቡድናችንንም እንዲመሩ መርጠናል። እስካሁን በጊዜያዊ አሠልጣኝነት እየሰሩ የሚገኙት አሠልጣኙ የተዋጣለት የጨዋታ እቅድ በመንደፍ ጨዋታውን በመቅረብ እና በነበሩ ክፍተቶች ላይ ትክክለኛ የተጫዋቾች እና የአጨዋወት መንገድ ለውጦችን አድርገው ቡድናቸው የሊጉን መሪነት በአስተማማኝ ሁኔታ አጠናክሮ እንዲቀጥል ያደረጉበት መንገድ በሳምንቱ ቡድናቸው ድል እንዲያደርግ ከጣሩ አራት አሠልጣኞች በላይ ነጥብ እንዲያገኙ አስችሏል።


ተጠባባቂዎች

ሳምሶን አሰፋ – አርባምንጭ ከተማ
ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ኃይለሚካኤል አደፍርስ – ሰበታ ከተማ
ሀይደር ሸረፋ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ተስፋዬ አለባቸው – ሀዲያ ሆሳዕና
ጌታነህ ከበደ – ወልቂጤ ከተማ
ብሩክ በየነ – ሀዋሳ ከተማ