የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 1-2 ፋሲል ከነማ

ፋሲል ከነማ በመጨረሻ ደቂቃ ጅማ አባ ጅፋርን ከረታበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ጥሩ የመሸናነፍ ትግል የታየበት ነው። እንደ እግርኳስ በሁለታችንም በኩል ጥሩ የኳስ ፍሰት የታየበት ነው።

ውጤት ስላጡበት ምክንያት

“ቀይ ካርዱ ለታክቲካል ዲስፕሊን እና ካሰብነው አጨዋወት ስልት እንድንወጣ መንገድ ከፍቷል። ያ ነገር ትልቅ ዋጋ አስከፍሎናል።

ስለተጫዋቾች የመጫወቻ ቦታ መቀያየር

“የሚገጥሙ ክፍተቶች እንደዛ እንድትጠቀም ያደርጉሀል። ቦና ፊት ሲያጠቃ ጥሩ ነው። የተሻለ ሰው ከሌለ መንዝሮ ተጫዋቾችን መጠቀም አንደኛው መንገዴ ነው። አስጨናቂ ከመሀል ተከላካይነት ወጥቶ የተከላካይ አማካይ ሆኗል። ይህ የሆነው በሙሴ መውጣት ምክንያት ነው። አንዳንዴ ከአቅምህ በላይ ነገሮች በሚሆኑበት ጊዜ ለማስተካከል የሚደረጉ ሂደቶች ናቸው።

አቻ ይገባናል ብለው ስለማሰባቸው

” ማሸነፍን እንፈልጋለን ፤ ለማሸነፍም ነው ሜዳ የገባነው። ፋሲል ጠንካራ ቡድን ነው ፤ ጠንካራ መሆኑን እናውቃለን። ያንን ተቋቁመን የማሸነፍ አቅም አለን ብለን ኳሱን በአግባቡ ተቆጣጥረን ነው የተጫወትነው። ኳስ በመያዙ ምንያህል በልጠናል የሚለው መረጃው ባይኖረኝም የምንፈልገውን የኳስ ፈሰት በአግባቡ አካሂደናል አቻ በቂያችን ነበር ብዬ አስባለሁ።”

አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ

ስለጨዋታው

“በጣም ፈታኝ ነበር። ሦስት ነጥቡ አስፈላጊ ስለነበር ልጆቹም ጭንቀት ውስጥ ስለነበሩ በጣም አስቸጋሪ ነበር።

ስለቅያሪዎች

“የምናስበው ማሸነፍ ነው ፤ ሦስት ነጥብ ስለሆነ የግድ ተጭነን መጫወት ስለነበረብን ሁለት አጥቂዎችን ጨምረን የተሻለ ወደ ጎል በማድረስ ጎሎችን አስቆጥረን ለማሸነፍ በቅተናል።

ጨዋታው የሚፈልጉትን ቡድን ስለማሳየቱ

“ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ መቻኮሎች ነበሩ። በሁለተኛው ግን ያ ነገር ተሻሽሎ ኳስ ይዘው ለመጫወት ሞክረዋል። ወደፊት ደግሞ የተሻለ ነገር ይዘን እንመጣለን ብዬ አስባለሁ።

ስለጅማ ፈታኝነት

“በጣም ፈታኝ ነበር። በፊት የምናውቀው ጅማ አይደለም ፤ ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን ነው ፤ አስቸጋሪ ነበር።

ከመሪው ጋር ስላላቸው የነጥብ ልዩነት

” እሱ እኛን አያሳስበንም ። ላይ ስላሉት ሳይሆን የምናስበው ስለራሳችን ነው። እንዴት ነው ማሸነፍ የምንችለው የሚለውን እንጂ ስለሌሎች አናስብም።

ስለዋና አሰልጣኝነት ስሜት

” ዋና አሰልጣኝነትም ምክትል አሰልጣኝነትም ሚናው ያው ነው ፤ ልዩነት የለውም ብዬ ነው የማስበው። በፊት የነበረውን ማስቀጠል ነው። ቀስ እያልን ደግሞ የተሻለ ነገር ለመስራት እንሞክራለን።”