የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ8ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቦ ወደ ሦስተኝነት ከፍ ሲል ባህር ዳር ከተማ ደረጃውን ያሻሻለበትን ድል አግኝቷል።

በቶማስ ቦጋለ

ባህርዳር ከተማ ከአራት ጨዋታ በኋላ ሦስት ነጥብ አሳክቷል

አቃቂ ቃሊቲዎች በ7ኛ ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ በሰፊ የግብ ልዩነት ከተሸነፉበት አሰላለፍ የስድስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ሔለን ሙሉጌታ ፣ ፍቅርተ ብርሃኑ ፣ አበዛሽ ሚግሶ ፣ ሒሩት ደምሴ ፣ እየሩስ ታደሠ ፣ በሬዱ በቀለን በልዩወርቅ መንበረ ፣ ሔለን አባተ ፣ ቅድስት ባደግ ፣ ሩት ሚሊዮን ፣ ምሕረት ታፈሰ ፣ ፍሬሕይወት በድሉ ተተክተዋል። በባህርዳር ከተማ በኩል በ 7ኛ ሳምንት በድሬዳዋ በሰርካለም ባሳ ብቸኛ ግብ አንድ ለምንም ከተረቱበት ጨዋታ የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ ሲያደርጉ ገነት ገብረማርያም ቤዛዊት መንግሥቴን ተክታ ገብታለች።

በቀዝቃዛ ፣ ነፋሻማ እና ለጨዋታ ምቹ በሆነ አየር ሁኔታ የተደረገው የመጀመሪያው ጨዋታ ብዙም ፉክክር ያልታየበት ደካማ እንቅስቃሴ የነበረበት ሆኖ አልፏል። 12ኛው ደቂቃ ላይ የባህርዳሯ ቃልኪዳን ተስፋዬ ኳስ በእጅ በመንካቷ የተሰጠውን ቅጣት ምት የአቃቂዋ ዓይናለም መኮንን ወደ ግብ ስትሞክር በግንባሬ ገጭቼ አወጣለሁ ያለችው አዳነች ጌታቸው በራሷ መረብ ላይ በማሳረፍ አቃቂዎች መሪ የሆኑበትን ግብ አስገኝታለች። በምስር ኢብራሂም የግብ ዕድል ለመፍጠር የሞከሩት የጣና ሞገደኞቹ ተደጋጋሚ ጊዜ ወደግብ ቢደርሱም የመጨረሻ ኳሳቸው እየተበላሸ ሲቸገሩ ታይተዋል። 

30ኛው ደቂቃ ላይ ሊዲያ ጌትነት ከትዕግሥት ወርቄ የተቀበለችውን ኳስ በአግባቡ ተጠቅማ ግብ በማስቆጠር ሞገደኞቹን አቻ አድርጋለች። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ከግራ መስመር ከ ሊዲያ ጌትነት ጥሩ ኳስ የተቀበለችው ትዕግሥት ወርቄ ትልቅ የግብ አጋጣሚ ብታገኝም ሳትጠቀምበት ቀርታለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት በሊዲያ ጌትነት ምስር ኢብራሂም እና መንደሪን ታደሰ የግብ ዕድል ለመፍጠር የሞከሩት ባህር ዳሮች ሳይሳካላቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ብዙም የግብ ሙከራዎች ባልታዩበት ሁለተኛ አጋማሽ በትዕግሥት ወርቄ እና ምስር ኢብራሂም ተደጋጋሚ የግብ ዕድል ለመፍጠር የሞከሩት ባህር ዳሮች ውጤታማ አልነበሩም። ሆኖም ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩ ምስር ኢብራሂም ከረጅም ርቀት ድንቅ ግብ አስቆጥራ ሞገደኞቹን መሪ አድርጋለች። ከግቡ መቆጠር በኋላ ከጨዋታው ነጥብ ይዘው ለመውጣት አቃቂዎች በዐይናለም መኮንን እና ሔለን አባተ የግብ ዕድል መፍጠር ቢችሉም ውጤቱን መቀየር አልቻሉም።

ጨዋታውን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማዎች ከአራት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ሲያገኙ አቃቂ ቃሊቲዎች ለተከታታይ አምስተኛ ጊዜ ተሸንፈዋል። በደረጃ ሰንጠረዡም ባሉበት ባህርዳር በ12ኛ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመመራት በመነሳት መከላከያን ረቷል

መከላከያዎች በ7ኛ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን በሰፊ የግብ ልዩነት ካሸነፉበት ስብስብ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ሲያደርጉ ህድአት ካሱ ሥራ ይርዳውን ተክታ ገብታለች። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው አቃቂ ቃሊቲን በሰፊ የግብ ልዩነት ከረቱበት ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ገብተዋል።

ጨዋታው ብዙ የግብ ሙከራዎች እና አዝናኝ ትዕይንቶች የታዩበት ነበር። በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች በመከላከያ በኩል መሳይ ተመስገን ኤሌክትሪኮች በምንትዋብ ዮሐንስ እና በሀብታም እሸቱ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ 10ኛው ደቂቃ ላይ ከዓይናለም አሳምነው ስህተት የተገኘውን እና ሴናፍ ዋቁማ አመቻችታ ያቀበላችትን ኳስ መሳይ ተመስገን በጥሩ ሁኔታ አስቆጥራ መከላከያን መሪ አድርጋለች። ከጎሏ መቆጠር በኋላ ተጭነው የተጫወቱት ኤሌክትሪኮች 12ኛው ደቂቃ ላይ ዓይናለም አሳምነው በመከላከያ ተከላካዮች ስህተት ጥሩ የግብ ማግባት ዕድል ብታገኝም ሳትጠቀምበት ቀርታለች። 

ምንትዋብ ዮሐንስ እና ንቦኝ የን በተደጋጋሚ ከቅጣት ምት ወደ ግብ ቢሞክሩም በግብ ጠባቂዋ ጥረት ሳይሳካላቸው ቀርቷል። 18ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም አስረሳኸኝ ከማዕዘን ያሻማችውን ኳስ አረጋሽ ፀጋ በግንባር በመግጨት አስቆጥራ ቡድናን አቻ አድርጋለች። 28ኛው ደቂቃ ላይ ዙሌካ ጁሃር ወደግብ ሞክራ ግብ ጠባቂዋ የመለሰችውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረችው ጥሩ እንቅስቃሴ ስታደርግ የነበረችው ምንትዋብ ዮሐንስ በቀላሉ አስቆጥራ ቡድኗ ከኋላ ተነስቶ የመጀመሪያውን አጋማሽ መርቶ እንዲወጣ አስችላለች።

ከዕረፍት መልስም ጥሩ የጨዋታ ብልጫውን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሲወስዱ 50ኛው ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪኳ ዓይናለም አሳምነው ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ብታደርግም ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም። በሁለት ደቂቃ ልዩነት የመከላከያዋ መሳይ ተመስገን ከግራ መስመር ወደግብ የሞከረችው ቅጣት ምት የቀኙን የግቡ ቋሚ ታክኮ የወጣባት አጋጣሚ መከላከያዎችን ያስቆጨች ነበረች። 68ኛው ደቂቃ ላይ ዓይናለም አደራ ምንትዋብ ዮሐንስ ላይ በሰራችው ጥፋት የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ንቦኝ የን አስቆጥራ የኤሌክትሪክን መሪነት አጠናክራለች።

63ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ ከቅጣት ምት ወደጎል የሞከረችውን እና ኤሌክትሪክ ተከላካዮች በግሩም ሁኔታ የፀዳው ኳስም ለመከላከያዎች ሌላው አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። ኤሌክትሪኮች ልዩነቱን ይበልጥ ሊያሰፉ ይችሉበት በነበረው ሌላ አጋጣሚ 68ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ከ ምንትዋብ ዮሐንስ የተሻማውን የቅጣት ምት ኳስ ነፃ ሆና በግንባር የሚገጭ ኳስ ያገኘችው ንቦኝ የን ኳሱን ሳታገኘው ቀርታ ወርቃማ እድል አምክናለች። በመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ አጥቅተው የተጫወቱት መከላከያዎች በሴናፍ ዋቁማ እና በመሳይ ተመስገን የግብ ዕድል መፍጠር ቢችሉም ሊጠቀሙበት ባለመቻላቸው ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥቡን 15 በማድረስ ሦስተኛ ደረጃን ሲይዝ መከላከያ በ11 ነጥቦች 6ኛ ላይ ተቀምጧል።

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

ጌዴኦ ዲላዎች በ7ኛ ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 2 አቻ ከተለያየው ስብስባቸው የሁለት ተጫዋች ለውጥ ሲያደርጉ ማማየ ዘገየ እና ጽዮን ማንጁራ በ አልማዝ ብርሃኔ እና ጤናየ ወመሴ ተተክተዋል። አርባምንጮች በበኩላቸው በ 7ኛ ሳምንት ከመከላከያ ጋር በሰፊ የግብ ልዩነት ከተሸነፉበት ጨዋታ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ከባቴ ከታለ ፣ ወርቅነሽ ሚልሜላ ፣ መሠረት ወርቅነህ ፣ ጺዮን ሳህሌ በምሕረት ተሰማ ፣ ደራ ጎሣ ፣ ወርቅነሽ መሰለ ፣ እና ሜሮን ዘሪሁን ተተክተው ገብተዋል።

በመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ፍፁም የበላይ የነበሩት አርባምንጮች ወደ ተጋጣሚ ክልል ቀርቦ የግብ ዕድል ለመፍጠር የጌዴኦ ዲላዎችን ጥቅጥቅ ያለ መከላከል ማለፍ ሲቸገሩ ተስተውለዋል። የማጥቃት መስመራቸውን በወርቅነሽ ሚልሜላ ያደረጉት አዞዎቹ 22ኛው ደቂቃ ላይ ወርቅነሽ ከግራ መስመር የመታችው ቅጣት ምት የግራ የግቡን ቋሚ ታክኮ የወጣ ሲሆን ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ኢላማውን መጠበቅ ባይችልም ግሩም የግብ ማግባት ሙከራ አድርጋለች።

 ተከላክለው ኳስ ለመንጠቅ እና ከቆመ ኳስ መጠቀም የፈለጉት ጌዴኦ ዲላዎች በማርያም ታደሠ እና በዝናቧ ሽፈራው የግብ ዕድል ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። 36ኛው ደቂቃ ላይ ወርቅነሽ ሚልሜላ ከቀኝ መስመር ከሳጥኑ አጠገብ ያገኘችውን ቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ብትሞክርም ግብ ጠባቂዋ አድናባታለች። በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ሙከራ 38ኛው ደቂቃ ላይ መሠረት ወርቅነህ ከ ወርቅነሽ ሚልሜላ የተቀበለችውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ አታልላ በማለፍ ወደ ቀኝ መስመር ገፍታ የሞከረችው ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ግብ ጠባቂዋ በሚያስደንቅ ብቃት ይዛዋለች።

ከዕረፍት መልስ አሰልቺ እና ለተመልካች የማይስብ ጨዋታ ያየንበት ሲሆን 46ኛው ደቂቃ ላይ አዞዎቹ ጥሩ ስትንቀሳቀስ በነበረችው ወርቅነሽ ሚልሜላ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ቢያደርጉም በግብ ጠባቂዋ ጥረት ሳይሳካላቸው ቀርቷል። 56ኛው ደቂቃ መሠረት ወርቅነህ ከድንቅነሽ በቀለ ጥሩ በግንባር የሚገጭ የተሻማ ኳስ ብታገኝም ሳትጠቀምበት ቀርታለች። በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ቡድን መድረስ የቻሉት አዞዎቹ በወርቅነሽ ሚልሜላ እና በ ትዝታ ኃይለማርያም የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በሁለተኛው አጋማሽም ከቆመ ኳስ እና ከመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለማግኘት የመረጡት ጌዴኦ ዲላዎች በመቅደስ ተሾመ እና ማርያም ታደሠ አማካኝነት የግብ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካለቸው ቀርቶ ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎም አርባምንጭ በአስር ነጥቦች 7ኛ ጌዲዮ ዲላ ደግሞ በአራት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።