የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-0 ወልቂጤ ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ዕለት የመጀመሪያ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱ አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“ጠንካራ ጨዋታ ነበር። አንደኛ እኛ ከሽንፈት ስለመጣን ውጤቱን ለመያዝ በጥንቃቄ ነበር የተጫወትነው። በተለይ ግቧን ካገኘን ወዲህ ታክቲካሊ ቆመው እንዲከላከሉ ነበር የፈለግነው። ያንንም በትክክል አድርገዋል ዞሮ ዞሮ እንደሌላው ጊዜ ጫና ፈጥረን መጫወት ባንችልም የምንፈልገውን ነገር ይዘን ወጥተናል።

ስለ ወንድማገኝ እና ብሩክ ጥምረት

“የእነሱ የመሀል ተከላካዮች የመስመር ተከላካዮቻቸው የሚተውትን ቦታ ለመሸፈን ወደ መስመር ይወጡ ስለነበር እነሱ ተጠጋግተው ሲጫወቱ ያንን በአንድ ሁለት ቅብብል ማስከፈት እንደሚችሉ በልምምድ ላይም ሰርተን ስለመጣን እንዲሁም በቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ስለተነጋገርን ያንን ነበር ተግባራዊ ያደረጉት።

ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ስለማለታቸው

“የዛሬ ሦስት ነጥብ ጥሩ መነሳሻ ይሆነናል ብዬ አስባለሁ። ቀጣይ ሁለት ጠንካራ ጨዋታዎች ይጠብቁናል። ቀጣይ እነዚህን ማሸነፍ ከቻልን ከመሪው ያለንን ልዩነት ማጥበብ ስለምንችል በዚያ ልክ ነው ከዚህ በኋላ የምንመጣው።”

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ሙሉ ለሙሉ ጥሩ ነው ብሎ ለመውሰድ ይከብዳል። እኛ ሙሉ ለሙሉ ኳሱን ተቆጣጥረን ለመጫወት ጥረት አድርገናል። ነገርግን ተጋጣሚያችን ጨዋታው በተደጋጋሚ እንዲቆራረጥ ስለሚያደርግ በምንፈልገው ቅኝት መጫወት አልቻልንም።”

ብዙ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ስላመቻላቸው

“ከዚህ በፊት በነበሩ ጨዋታዎች ተጋጣሚዎች ጌታነህ ላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ ጫላ ይህን ክፍተት በመጠቀም ረገድ ይረዳን ነበር። ነገርግን ዛሬ ጫላ ከጤንነት ጋር በተያያዘ ጉዳይ ሙሉ ዝግጁ ስላልነበር ይህን መጠቀም ሳንችል ቀርተናል።”

የመጀመሪያ ሽንፈት ስለማስተናገዱ

“ሽንፈት ሁሌም አስደሳች አይደለም። ነገር ግን የምትማራቸው ነገሮች ይኖራሉ በዚህም ለቀጣይ ለሦስት እራት ጨዋታዎች የሚሆንህን ትምህርት ታገኛለህ።”