ሪፖርት | የወንድማገኝ ኃይሉ ብቸኛ ግብ ሀዋሳን አሸናፊ አድርጋለች

በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ወልቂጤ ከተማን በመርታት ደረጃ እና ነጥቡን አሻሽሏል።

ባሳለፍነው ሳምንት በሲዳማ ቡና 3ለ1 የተረቱት ሀዋሳ ከተማዎች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ አራት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም አዲስዓለም ተስፋዬ፣ ዳንኤል ደርቤ፣ መስፍን ታፈሠ እና አብዱልባሲጥ ከማል አርፈው አዲሱ ተጫዋቻቸው ካሎንጂ ሞንዲያ፣ ወንድማገኝ ኃይሉ፣ ዳዊት ታደሠ እና ተባረክ ሔፋሞ አሰላለፍ ውስጥ ገብተዋል። በተቃራኒው ወልቂጤ ከተማዎች በጨዋታ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ሁለት አቻ ወጥተው ቀይረው ወደ ሜዳ ባስገቧቸው የተጫዋቾች ተገቢት ጉዳይ ክስ ቀርቦባቸው ፎርፌ ከተሰጠባቸው ፍልሚያ የግብ ዘቡ ሰዒድ ሀብታሙን በሮበርት ኦዶንካራ እንዲሁም ዮናስ በርታን በረመዳን የሱፍ፣ ሐብታሙ ሸዋለምን በሀይሉ ተሻገር እና አክሊሉ ዋለልኝን በያሬድ ታደሠ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የግብ ሙከራዎች እምብዛም አልነበሩበትም። ቡድኖቹም የተቆራረጠ የኳስ ቅብብል የነበራቸው ሲሆን በአንፃራዊነት ወልቂጤ ከተማ የተሻለ የኳስ ፍሰት ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ቀጥተኝነት የተስተዋለበት አጨዋወት ሲተገብሩ ነበር። ጨዋታውም የጠራ ባይሆንም የመጀመሪያ የግብ ማግባት ዕድል የተፈጠረበት በ23ኛው ደቂቃ ነበር።

በዚህም ከወደ ቀኝ ባደላ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት በመጠቀም ወልቂጤ ቀዳሚ ለመሆን ጥሯል። ወልቂጤዎች ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ሌላ የሰላ አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። በዚህም ተስፋዬ ነጋሽ ከቀኝ መስመር የላከውን ኳስ ለወትሮ ከሚሰለፍበት የግራ ተከላካይ ቦታ ወደ ግራ መስመር አማካኝ ተለውጦ ሲጫወት የነበረው ረመዳን ናስር እና ጫላ ተሺታ ለጥቂት አምልጧቸዋል።

ሙከራ አልባው ጨዋታ በ38ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ዒላማውን በጠበቀ ጥቃት ግብ አስተናግዶ መሪ አግኝቷል። በዚህም ከመልስ ውርወራ የተነሳውን የመጨረሻ ኳስ ራሱን ነፃ አድርጎ በግራ የሳጥኑ ክፍል ያገኘው ብሩክ በየነ አድናቆት በሚያስችረው ሁኔታ የራስ ወዳድነት ስሜት ሳይታይበት ለወንድማገኝ ኃይሉ አቀብሎት ወንድማገኝ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳ ቀዳሚ ሆኗል።

የያዙትን የኳስ ቁጥጥር ፍሬያማ ማረግ የተሳናቸው ወልቂጤዎች አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት አበባው ቡጣቆ እና ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት አከታትለው በሞከሯቸው ኳሶች አቻ ለመሆን ጥረው መክኖባቸዋል። አጋማሹን በሀዋሳ አንድ ለምንም መሪነት ተገባዷል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ በሁለተኛው አጋማሽ መጣር የያዙት ወልቂጤዎች በ48ኛው ደቂቃ በአብዱልከሪም ወርቁ አማካኝነት ጥሩ ዕድል ፈጥረው ተመልሰዋል። በ57ኛው ደቂቃም አበባው ከግራ መስመር ረጅም ኳስ ልኮ የዳግምን መረብ ለማግኘት ዳድቷል።

ከደቂቃ በኋላም ይሁ ተጫዋች ጥሩ የቅጣት ምት አሻምቶ ዋሀብ አዳምስ በግንባሩ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ተንቀሳቅሶ ዒላማውን ስቶበታል። የሚፈልጉትን ያገኙት ሀዋሳዎች የማጥቃት ሀይላቸውን ቀነስ አድርገው ጨዋታ መቆጣጠር ላይ ትኩረት በመስጠት መጫወትን መርጠዋል።

ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል በክፍት ጨዋታ መፍጠር የተሳናቸው ወልቂጤዎች በዋናነት ከአበባው የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶችን እና የቅጣት ምቶችን ለመጠቀሚ ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ጨዋታውም ብቸኛ የተገኘውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ወደ ግብነት ቀይረው በወጡት ሀዋሳ ከተማዎች አሸናፊነት ተገባዷል።

በውጤቱ መሠረትም ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 34 በማድረስ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሽንፈት ያስተናገደው ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በግብ ዕዳ ከነበረበት ዘጠነኛ ደረጃ ሸርተት ብሎ አስረኛ ቦታን በ24 ነጥቦች ተቆናጧል።