“እኔ እግርኳስን በጣም ነው የምወደው ፤ ለዚህም ሁሉን ነገሬን የምሰጠው ለእሱ ነው” ሳላዲን ሰዒድ

ታሪካዊው አጥቂ በሐት-ትሪክ ከደመቀበት የጨዋታ ሳምንት ወጣት ተጫዋቾች ምን መማር እንዳለባቸው የሚጠቁም ቆይታ አድርገናል።

ከትናንት በስቲያ በቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊጉ የ19ኛ ሳምንት ጨዋታ ሰበታ ከተማን 3-0 በረታው የሲዳማ ቡና የቡድን ስብስብ ውስጥ አንበል በመሆን የገባው ሳላዲን ሰዒድ ለሲዳማ ቡና የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ጎሉን ከማስቆጠሩ ባሻገር ሐት ሐትሪክ መስራት ችሏል።

የኢትዮጵያን እግርኳስ በቅርብ ለሚከታተል ሰው ስለሳላዲን ሰዒድ የተጫዋችነት ህይወት ስኬቶች መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው። ነገር ግን የቀደመ ስሙ ከተመልካቹ ሀሳብ ውስጥ እየተዘነጋ ሄዶ ብሎም ለግማሽ የውድድር ዓመት ከጨዋታ ርቆ ሲመለስ አሁንም እርሱነቱን በሚገልፀው የብቃት ደረጃ ላይ ሆኖ መታየቱ አስገራሚ ነው። እርግጥ ነው አንጋፋ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን ማስቀጠላቸው ሲታይ ‘የሊጉን ድክመት ያሳብቃል’ የሚል አስተያየት ቢያስነሳም ሌላውን ጎን መመልከትም ግን ተገቢ ነው።

አሁናዊ ወጣት ተጫዋቾቻችን በግል እና በስራ ህይወታቸው የሚያሳዩት ቸልተኝነት አለፍ ሲልም በአደባባይ የሚታሙበት የሥነምግባር ችግር ብቅ ጥልቅ ከሚል አቋም አልፈው የእምቅ ችሎታቸውን ያህል መድመቅ እያቃታቸው እንደ ሳላዲን ዓይነቱን ተጫዋች ስኬት የሊጉን ደረጃ መለኪያ ከማድረግ ይልቅ ለሌሎች ምሳሌ አድርጎ ማስቀመጡ ተገቢ ይሆናል።

በሳላዲን የእግርኳስ ህይወት ወጣቶች የሚማሩት ቀዳሚው ጉዳይ ሥነምግባር እና ሙያዊ ክብርን ነው። ለረጅም ዓመታት ራሱን ጠብቆ በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የደመቀው ተጫዋቹ የሙያ ክብሩ ለእግርኳስ ካለው ፍቅር ጋር በቀጥታ እንደሚገናኝ ይጠቁማል። “እኔ እግርኳስን መጫወት የጀመርኩት በ12 ዓመቴ በፕሮጀክት ታቅፌ በመጫወት ጀምሮ ነው ፤ ይህ በጣም ጠቅሞኛል። ሌላው እኔ እግርኳስን በጣም ነው የምወደው ፤ ለዚህም ሁሉን ነገሬን የምሰጠው ለእሱ ነው። ጎን ለጎን ገቢህ የምታገኝበት ሆኖ ቤተሰብን ታስተዳድርበታለህ። ስለዚህ ሙያውን አክብሬ ፣ ዲሲፒሊንድ ሆኜ ፣ ለእግርኳሱ ታማኝ ሆኜ ፣ ራሴን ጠብቄ በመስራቴ ይመስለኛል ረጅም ጊዜ ለመጫወት የቻልኩት። አንዳንዴ ጉዳቶች ይፈትኑኛል ይህም እንዳለ ሆኖ የምፈልገው ደረጃ ደርሻለው ባልልም። ከፈጣሪ ጋር የምችለውን ነገር እያደረኩኝ እገኛለው።”

ራስን ከመጠበቅ ባለፈ ደግሞ ብዙ ጊዜ ተጫዋቾች በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች ከሜዳ ሲርቁ በአካል ብቃትና በሥነ ልቦናው ዝግጁ ካለመሆን ጋር ተያይዞ ቀድሞ ከነበራቸው ብቃት ወርደው ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። በዚህ ረገድ ሳላዲን ሰዒድ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ሜዳ ሲመለስ በጥሩ አቋም የመመለሱ ምክንያት ያለማቋረጥ መስራት መሆኑን ይናገራል። “አንደኛ ስዘጋጅ ነው የቆየሁት አልተቀመጥኩም ፤ ማረፍም ፈልጌ አይደለም። እሰከ መጨረሻው ድረስ ጅማዎች እንዲያስተካክሉ የነገርኳቸው ነገሮች ባለመስተካከሉ ነው አንደኛውን ዙር ያልተጫወትኩት። እኔ ግን ስሰራ ነበር የቆየሁት ከፈጣሪ ጋር የምፈልገውን እያገኘሁ ነው።”

የሳላዲን እግርኳሳዊ ሥነምግባር እና ከሜዳ ርቆ በቆየበት ጊዜ እንኳን ሥራን አለማቋረጡ ራሱን ሆኖ እንዲቀጥል ሲያስችለው ፍሬውን ጎል በማግባቱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ላይ በሚያሳደረው ተፅዕኖም መመልከት እንችላለን። ይህም በአዲሱ ቡድኑ ውስጥ በተጨዋቾች ይሁንታ የአንበልነት ኃላፊነት የተሰጠው በመሆኑ ይገለፃል። የቡድን አጋሮቹ በዚህ መጠን ስላከበሩት የሚያመሰግነው አጥቂው ቀጥሎ የሰጠው አስተያየት ከተጫዋችነት ክህሎቱ ባለፈ ስለምን በዚህ መጠን ተቀባይነት እንዳገኘ ይጠቁማል። “በእግርኳስ በጣም ዲሲፒሊንድ መሆን አለብህ። ይሄን ከተገበርክ እና ትኩረትህ እግርኳስ ላይ ካደረክ እንደዚህ ረጅም ጊዜ መጫወት ትችላለህ። ዲሲፒሊን ሲባል ብዙ ነገር ያካትታል ፤ ራስን መጠበቅ እና ልምምድን በአግባቡ መስራት። ይሄንን በተገቢው መንገድ ከሰራህው የምትፈልገው ደረጃ ትደርሳለህ።”

ሳላዲን በክለብ ህይወቱ መነሻውን ከሙገር አድርጎ በቅዱስ ጊዮርጊስ የከፍታ ጊዜያትን በማሳለፍ በሰሜን አፍሪካ እና በቤልጄም ተጫውቶ አሳልፏል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ምልሰቱ ዓምና ከተቋጨ በኋላ ከ1999 ወዲህ ከፈረሰኞቹ መለያ ወጪ በጅማ አባ ጅፋር ልንመለከተው ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ያ ሳይሳካ ከሲዳማ ጋር በሁለተኛው ዙር ተመልሷል።

ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት የልዩነት ፈጣሪነት ፍንጭ ያሳየው አንጋፋው አጥቂ በወንድማማቾች ደርቢ በቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ ስንመለከተው በዚህ ሳምንት ደግሞ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ በመግባት ሰበታ ላይ ሦስት ግቦችን አስቆጥሯል ፤ ክስተቱ የፈጠረበትን ስሜት እንዲህ ይገልፃል። “ዋናው ነገር ቡድኔ ከእኔ የሚፈልገው ነገር ይኖራል። እንዳዲስ ተጫዋች ደግሞ ግንባር ላይ ነህ መጀመርያ ከአጥቂ የሚጠበቀው ጎል ማግባት ነው። ጎል በማግባቴ ሐት-ትሪክ በመስራቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ዋናው ቡድኔ ሦስት ነጥብ ማግኘቱ ነው።”

እስከ ውድድር ዓመቱ መጠናቀቅ ድረስ ከሲዳማ ቡና ጋር ቆይታ የሚኖረው ሳላዲን ከተከታታይ ጨዋታ ማሸነፋቸው ለቀጣይ ጨዋታዎች መነሳሳት እንደሚፈጥርላቸው በመግለፅ ቡድኑ የሚፈልገውን ውጤት ከጓደኞቹ ጋር ለማሳካት ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል።