የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

በጨዋታ ሳምንቱ የታዘብናቸው ዓበይት ክለቦች ላይ ያተኮሩ ሀሳቦች እንደሚከተለው ይነበባሉ።

👉 ዕድለኛ ያልነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች

በጨዋታ ሳምንቱ የመጀመሪያ በነበረው ጨዋታ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ መከላከያን አስተናግዶ ጨዋታቸው ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ አንጋፋዎቹን ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 29 ጨዋታዎች 15 ያህል ጨዋታዎች በአቻ ውጤት መጠናቀቃቸው ጦሩ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ምን ያህል ፈታኝ ቡድን እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን በዚህኛው ጨዋታም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በብዙ መንገዶች የበላይ የነበሩ ቢሆንም አሸንፈው መውጣት ግን ሳይችሉ ቀርተዋል።

በሁለቱም አጋማሾች የፈረሰኞቹን የበላይነት በተመለከትንበት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንደ ነበራቸው የጨዋታ የበላይነት ሆነ የፈጠሯቸው ዕድሎች ብዛት ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው በወጡ ነበር። ነገር ግን ጋናዊው የመከላከያ ግብ ጠባቂ ክሌመንት ቦዬ የግብ አግዳሚ ፈረሰኞች እና ሙሉ ሦስት ነጥብ ነጣጥለዋል።

ከአራት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ አቻ የተለያዩት ጊዮርጊሶች አሁንም በ41 ነጥብ ሊጉን መምራታቸውን ሲቀጠሉት በቀጣይ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት በሊጉ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን በመያዝ እየተፎካከሩት ከሚገኙት ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ጋር እጅግ ወሳኝ ሁለት ጨዋታዎች ይጠብቋቸዋል። ቡድኑ እነዚህን ፈተናዎች በድል መወጣት የሚችል ከሆነ ለሊጉ ክብር ስለመቃረቡ ይበልጥ ማረጋገጫ የሚያገኝባቸው ጨዋታዎች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

👉 እጅግ ደካማው የሰበታ መከላከል

በሊጉ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ በበርካታ አስተዳደራዊ ችግሮች ተተብትቦ የሚገኘው ቡድኑ በሜዳ ላይ ያለው እንቅስቃሴ የተወሰነ ተስፋ ቢፈነጥቅም አሁንም በመከላከሉ ያሉበት ችግሮች በሊጉ የመቆየት ተስፋው ላይ ማነቆ ሆኖበታል።

ሰበታ ከተማ በሲዳማ ቡና በተረታበት ጨዋታ የተቆጠሩት ሦስት ግቦች አጠቃላይ የቡድኑን የመከላከል አደረጃጀት ድክመት በግልፅ የሚያሳዩ ነበሩ። የመጀመሪያውን ግብ ገና በማለዳ ያስተናገደው ቡድኑ ግቧ ስተቆጠር አንተነህ ተስፋዬ ከቡድን አጋሩ በኃይሉ ግርማ የደረሰውን ኳስ ለማቀበልም ሆነ ለማራቅ በቂ ጊዜ የነበረው ቢሆንም ከልክ በላይ በማሰብ ሂደቱን በማዘግየቱ የተነሳ ተቀምቶ የተቆጠረ ሲሆን ሁለተኛዋ ግብ ስትቆጠር ደግሞ የግራ መስመር ተከተላካያቸው በመከላከሉ ወቅት ሊገኝበት በሚገባው ቦታ ላይ ባለመገኘቱ የተነሳ የተከላካይ መስመሩ ወደ ቀኝ እንዲሳብ የተገደደ ሲሆን እንዲሁም ኳሱ ከሳጥኑ ጠርዝ ወደ ውስጥ ሲሻማም ግቡን ያስቆጠረው ሳላዲን ሰዒድን ፍፁም በነፃነት ኳሷን እንዲጠቀምበት ፈቅደውለት አስተውለናል።

በሦስተኛው ግብ ወቅትም ኳሱ ገና ከጅምሩ ወደ ሰበታ አጋማሽ ሲደርስ የነበረው ፍፁም ያልተደራጀ የመከላከል ቅርፅን የተመለከትን ሲሆን በግቧ ሂደት ውስጥ ዳዊት ተፈራ የተገኘበትን አደገኛ ቀጠና ለመከላከል ያልቻሉ አልቻሉም። በዚህም በአንድ ኳስ መላው የቡድኑ ተጫዋቾች የተቆረጡበት እና ሳጥኑን የሚከላከል ተጫዋች ያለመኖሩ ጉዳይ ለግቡ መቆጠር ዓይነተኛ ምክንያት ነበር።

በሊጉ የአስካሁኑ ጉዞ እጅግ ደካማው የመከላከል ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው ቡድን በጨዋታ በአማካይ 1.73 ግቦችን በጥቅሉ በሊጉ ደግሞ 33 ግቦችን አስተናግዷል። ታድያ በሊጉ ስለመቆየት የሚያስብ ቡድኑ ቢያንስ እንኳን ጨዋታዎችን ማሸነፍ ባይችል በቀላሉ ግቦች ባለማስተናገድ ሳይሸነፍ መውጣት የግድ በሚልበት በዚህ ወቅት ሰበታ ከተማ በዚህ መልኩ ግቦችን እያስተናገደ በሊጉ ይቆያል ብሎ ማሰብ በጣም አስቸጋሪ ይመስላል።

👉 ድሬ ወደ ድል ተመልሷል

በሊጉ በየዓመቱ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ የማይጠፋው ድሬዳዋ ከተማም ዘንድሮም እንዲሁ በዚህ ትግል ውስጥ ይገኛል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ድሬዳዋ ከተማዎች ከስምንት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ የመጀመሪያ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

ጥር 23 በ10ኛ የጨዋታ ሳምንት የድሬዳዋ የሊጉ ቆይታ የመጀመሪያ በነበረው ጨዋታ መከላከያን በአብዱረህማን ሙባረክ ብቸኛ ግብ ከረቱበት ጨዋታ በኋላ በነበራቸው የጨዋታ ሳምንታት ስምንት ጨዋታዎችን ያደረጉ ሲሆን በአምስቱ ጨዋታ ሽንፈትን አስተናግደዋል። ታድያ ይበልጥ ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው በአራቱ ጨዋታዎች ሦስት እና ከዚያ በላይ ግቦችን አስተናግደው የመሸነፋቸው ጉዳይ እንዲሁም በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ግብ ሳያስቆጥሩ በአቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ስለነበረባቸው ችግር ማሳያ የነበሩ የጨዋታ ሳምንታት ነበሩ።

በውድድር ዘመኑ የቡድኑ ሦስተኛ አሰልጣኝ በሆኑት ሳምሶን አየለ እየተመራ የሚገኘው ድሬዳዋ በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ የመከላከል አወቃቀር ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ሲሆን በዚህም ረገድ አውንታዊ መሻሻሎችን እየተመለከትንበት ነው። በማጥቃቱ ረገድ ግን ከጨዋታ ጨዋታ የአደራደርም ሆነ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ትክክለኛውን ጥምረት ለማግኘት ገና ሙከራዎች ላይ ይገኛሉ።

ጅማ አባ ጅፋርን በረቱበት ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ በተጋጣሚያቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስድባቸውም ለግባቸው ቀርበው በመከላከል ተጋጣሚን አደጋ እንዳይፈጥር በማድረግ ረገድ የተዋጣላቸው የነበሩ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ግን ለውጦችን በማድረግ የተወሰደባቸውን ብልጫ አስመልሰው ሁለት ግቦችን አስቆጥረው ማሸነፍ ችለዋል።

የውድድር ዘመኑን አምስተኛ ድላቸውን ያስመዘገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በቀጣይ ይህን ድል እንደ መነሳሻ ተጠቅመው ውጤታቸውን ያሻሽሉ ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 በእንቅስቃሴ የተሻለው ነገር ግን ውጤት የራቀው ጅማ አባ ጅፋር

በሰንጠረዡ ግርጌ በ12 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ከሰሞኑ ባደረጋቸው ጨዋታዎች በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻለ ነገርን መመልከት ብንችልም ቡድኑ አሁንም ይህን ሂደት በውጤት ለማጀብ ተቸግሯል።

በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ ሲለያይ እንዲሁም በፋሲል ከነማ እና በድሬዳዋ ከተማ በተሸነፈባቸው ጨዋታዎች በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ድርሻን በመውሰድ ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። በተለይ በሁለቱም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት በቀጠሉባቸው የጨዋታ ደቂቃዎች አሸንፈው ለመውጣት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም መጠቀም ባለመቻላቸው ጨዋታዎችን ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ከመጀመሪያው ዙር አንፃር በስብስብ ረገድ በሁለተኛው ዙር በዝውውሮች የተሻለ አማራጮችን የፈጠረው ጅማ በተለይ የአዳዲስ ፈራሚዎቹ ተጫዋቾች ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘው ቡድኑ በእንቅስቃሴ ረገድ ያሳየውን መሻሻል በውጤት ማጀብ ካልቻለ ምናልባት የሊጉ አሳዛኝ ተሰናባች እንዳይሆን ያሰጋል።

👉 አዳማ ከተማ አሁንም ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል

በሜዳው እና በደጋፊው ፊት እየተጫወተ የሚገኘው አዳማ ከተማ አሁንም ለአራተኛ ተከታታይ ጨዋታ ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል። በሦስቱ ጨዋታዎች አቻ የተለያየው አዳማ ከተማ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በሀዲያ ሆሳዕና ተሸንፏል።

ቡድኑ ከፍተኛ ቁጥር ባለው ደጋፊው ታጎዞ የተሻለ ውጤት ይይዝባቸዋል ተብለው በተጠበቁት የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ጨዋታዎች እስካሁን ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥቦች ሦስቱን ብቻ ማሳካቱ ለደጋፊዎቹ የሚዋጥ ውጤት አይደለም።

ለወትሮው የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ነገር እምብዛም ችግሮች ያልነበሩበት ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ አብዲሳ ጀማል ካመከናት ግሩም አጋጣሚ ውጪ በጨዋታው ተጠቃሽ ሙከራዎችን ለማድረግ ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን በተቃራኒው በመከላከሉ ረገድ ቡድኑ ያለ ወትሮው ተደጋጋሚ ስህተቶችን ሲፈፅም የተመለከትንበት ጨዋታ ነበር።

ዑመድ ኡኩሪ ያስቆጠራት የመጀመሪያ ግብን ጨምሮ በግብ ጠባቂ እና በተከላካይ ተጫዋቾች ተደጋጋሚ ስህተት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ቀላል ቁጥር የሌላቸው ዕድሎችን ሲያገኙ ተመልክተናል።

በ24 ነጥቦች ወደ 10ኛ ደረጃ የተንሸራተተው ቡድኑ በቀጣይ የሊጉ የአዳማ ቆይታ የመጨረሻ በሆነው እና አዲስ አበባ ከተማን በሚገጥምበት የቀትር ጨዋታ ደጋፊዎቹን በደስታ የሚሰናበትበት የመጨረሻ ዕድል ይጠቀምበት ይሆን ?

👉 ሀዋሳ ከተማ ራሱን ወደ ፉክክሩ መልሷል

በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ እና በሲዳማ ቡና ሽንፈትን አስተናግዶ በተወሰነ መልኩ ከዋንጫ ፉክክሩ የራቀ የመሰለው ሀዋሳ ከተማ በዚህኛው ሳምንት ድል በማስመዝገብ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል።

በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመቆየት የግድ ሦስት ነጥብ ያስፈልገው የነበረው ቡድኑ በጨዋታው አስፈላጊ የነበረውን ነጥብ ማሳካት ችሏል። ገና ከጅምሩ በጥንቃቄ ሲጫወቱ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ 38ኛው ደቂቃ ላይ ወንድማገኝ ኃይሉ ቀዳሚ የሆኑባትን ግን ካስገኘ ወዲህ በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ አሳልፈው ላለመስጠት እጅግ አስደናቂ የመከላከል ትጋት አስመልክተውናል።

በሁለተኛው አጋማሽ በተለይ ቡድኑ ከኳስ ውጪ ሁሉንም ተጫዋቾች በማሰለፍ እና ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በጥልቀት ተሰብስበው እንዲጫወቱ በማድረግ እንና የጫዋቾች በተደጋጋሚ የጨዋታውን እንቅስቃሴ እንዲያቋርጡ በማድረግ ተጋጣሚያቸውን በአዕምሮ ረገድ እንዲዝል ማድረግን ችለዋል።

በዚህም መነሻነት ወልቂጤ ከተማዎች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው ቢሆንም በቁጥር በዝተው ይከላከሉ የነበሩትን የሀዋሳ ተጫዋቾች አጥር ለማለፍ የተቸገሩ ሲሆን በአጋማሹም በተነፃፃሪነት ከቆመ ኳስ ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል።

በአስደናቂ የመከላከል ትጋት እና ጥንቃቄ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ያሳኩት ሀዋሳ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 34 በማሳደግ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰባት ነጥብ ርቀው በሁለተኝነት ለመቀመጥ በቅተዋል።